Get Mystery Box with random crypto!

ከወንዞች ማዶ ያለች ቅዱስ ምድር...#ባህርዳር። ታዋቂው ዓለም አቀፍ አሳሽ፣ የቀድሞው የአሜሪካ መ | Tadele Tibebu - ታደለ ጥበቡ

ከወንዞች ማዶ ያለች ቅዱስ ምድር...#ባህርዳር። ታዋቂው ዓለም አቀፍ አሳሽ፣ የቀድሞው የአሜሪካ መርማሪ ፖሊስ፣ አሜሪካዊው ሮበርት ኮርኑክ በ1994 ዓ.ም. "The Lost Ark of The Covenant" ወይም "የጠፋው የቃልኪዳኑ ታቦት" የሚል መጽሐፍ አሳትሟል።

በዚሁ መጽሐፍ፣ "ከወንዞች ማዶ ያለች ቅዱስ ምድር" በሚል ንዑስ ስር ስለባህርዳር ከተማ፣ ስለጃካራንዳ ወኪል አስጎብኚ ምሥጋና ገናነው፣ በአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ይሰራ ስለነበረው ገበየሁ ወጋየሁ፣ ስለጭስ አባይ፣ ስለጣና ደሴቶች... በዝርዝር ጽፏል።

በዚሁ አንቀጽ ባህርዳርን እንዲህ ይገልጻታል። "የወደብ ከተማ የምትመስል፣ ንፁህና በእፅዋት የተሞላች"

ጢስ አባይን ደግሞ ፣ " ቦታው ከ1950ዎቹ የታርባን ፊልም ጋር ተመሳሳይ ነው። ወደ ፏፏቴው ስንቃረብ መሬቱ ሲርገበግብ ተሰማን፡፡ ትንሽ ከፍ ስንል በዳመና የተሸፈነ ቦታ ደረስን፡፡ ግዙፉ ፏፏቴ ወርዶ ከድንጋይ ጋር ሲላተም የሚፈጥረው ደመናማ ውርጭ ሸለቆውን ሞልቶ ዳገቱ ድረስ ይመጣል፡፡ እኔና ጆቢ (ጓደኛው) በአድናቆት ፈዘዝን፡፡ ከፏፏቴው በመቀጠል ሰፊውን የአባይ ወንዝ በጀልባ ሆነን አየነው። የግብፅና ሱዳን የህይወት ደም ስር የሆነው ይህ ወንዝ ከቀደምት ዘመን ጋር በምናባችን አገናኘን፡፡ የምንገኝበት የኢትዮጵያ ምድር በመፅሃፍ ቅዱስ የተጠቀሰው መሆኑ ታወሰኝ፡፡ 'ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚማልዱኝ የተበተኑ ሴት ልጆቼ ቁርባኔን ያመጡልኛል" (ትንቢተ ሶፎንያስ 3፤10)፡፡ ዙሪያዬን ቃኘሁ፡፡ በወንዞች የተከፋፈለውን ለም ምድር ስመለከት ነበር የመፅሀፍ ቅዱሷን የኢትዮጵያ ምድር መርገጤ የተሰማኝ፡፡" ይላል።

ሮበርት ኮርኑክ "ቅዱስ ሃይቅ፤ ንፅህት ደሴት" በሚል አንቀጽ ስለ ጣና ደሴትም ጽፏል።

" በአረንጓዴው የጣና ውሃ መሃል ከርቀት የምትታየው ደሴት በረግረግ ስፍራ ፀሃይ ለመሞቅ የተኛ ግዙፍ ኣዞ ትመስላለች። ...የሃይቁን ስፋትና ከምድር መነጠል ስመለከት ታቦቷን ለመደበቅ ተመራጭ ስፍራ በማለት ለራሴ አድናቆቴን ገለፅኩ። በሰፊው ሃይቅ ላይ ከ45 የሚበልጡ ደሴቶች እንዳሉ ተነገረኝ። በዚያ ላይ ሃይቁን የከበበው የተራሮች ሰንሰለት በደን የተሸፈነ ነው፡፡ ከዚህ አቀማመጡ የተነሳ ታቦቷን ፍለጋ ለሚመጣ ማንኛውም ሃይል ፈታኝ መሆኑ ይታያል፡፡...."

ይቀጥልና ስለጣና ቂርቆስ፣ በገዳሙ ስለሚኖሩ መናኞች፣ ክብ ሆነው ስለተደረደሩ የመነኮሳቱ ደሳሳ ጎጆዎች፣ ስለገዳሙ አትክልትና ፍራፍሬ በዝርዝር ያትታል። በጣም ትኩረቴን የሳበው ይህ ገለጻው ነው።

"መነኮሳት ፀሐይ ስትገባ ወደ ማደሪያቸው በመግባት ሌሊት ለፀሎት ይወጣሉ። ከጓደኛዬ ጆቢ ጋር የደሴቷ ተራራ ጫፍ ላይ ድንኳን ጣልን። የአፍሪካ ጨረቃና ከዋክብት ከሰፊው ሃይቅ ጋር የሚፈጥሩትን ህብር በአድናቆት እያየን አረፍን። በገዳሙ የሚኖሩ ህፃናቱ [የቆሎ ተማሪዎች ናቸው] መጥተው ከበቡን። ምሽቱን ከኛ ጋር ሲጫወቱ አሳለፉ። ከዚያ ምሽት በፊት ለ2500 ዓመታት ጣና ቂርቆስ ፍፁም ፀጥታ የነገሰባት የፀሎትና የፅሞና ሥፍራ ነበረች። በዚህ ምሽት ግን የገዳሟን ፀጥታ የህፃናቶች ፍንደቃ ቀየረው። በጨረቃዋ ብርሃን እየተሯሯጡ ሲጫወቱና ሲሳሳቁ አየናቸው።"

ሮበርት ኮርኑክ ይቀጥላል። "ከሌሊቱ 10፡30 ሰዓት የደውል ድምፅ ሰማንና ተነሳን። የማለዳውን ሥርዓተ-ፀሎት ለመታደም ከድንኳናችን ወጣን። የምሽቱ የህፃናት ጨዋታ የሚያስታውሱ የቸኮሌት ላስቲኮች በየቦታው ተበታትነዋል። ራዲዮኖቻችን ከመነፀሩ ጋር አስቀምጠውልን ሄደዋል። ልጆቹ ከኛ ጋር ሲሳሳቁ ቢቆዩም አንድ መነኩሴ ነበር በቁጣ ያባረራቸው። ልጆቹ ወደማደሪያቸው ሲገቡ የደሴቷ ፀጥታ ሌሊቱን ተረከበ።"

ሮበርት ኮርኑክ በጣና ቂርቆስ ገዳም ስለሙሴ ታቦት፣ በኩባያ ቅርፅ ስለተፈለፈሉት መሰዊያዎች፣ አይሁዳውያን ከታቦቷ ጋር ይዘውት ስለመጡት የመሰዋዕት ማቅረቢያ...ወዘተ ከመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ጋር እያነጻጸረ ለመጻፍ ሞክሯል። የቆሙበት ሥፍራ የታቦቷ ማደሪ እንደነበር ድምዳሜ ላይ ደርሷል። መጽሐፉ የጻፈው ከአክሱም እስከ ላሊበላ ከጣና ሐይቅ እስከ ግብፅ ኤሌፋንታይን ደሴት፣ እየሩሳሌምን ጭምር በማሰስ ነበር። በመጨረሻም መጽሐፉን እንዲህ በማለት ነበር ያጠናቀቀው፣

"ኦ - ኢትዮጵያ!..ልዩ አገር!.. ልዩ ህዝብ ..ልዩ ባህል!... ቃላት የማይገልፁት ድህነት ያየለባት ሆኖም ግን የሰብአዊ ደግነት ባለፀጋ አገር ናት፡፡ ምስጢራዊቷ ምድር ውስጤ የደበቀችውን ታላቅ ምስጢር ከህዝቦቿ ጋር ለመቶ አመታት ብኖር እንኳን ልረዳው አልችልም፡፡"

viva Maki Coffee - ማኪ ቡና