Get Mystery Box with random crypto!

ገዳመ ወንያት አቡነ ሐራ ድንግል በጣም ይደንቀኛል። በፍፁም አምኖ የሄደ ሰው ድኖ ይመለሳል፣ እኔ | Tadele Tibebu - ታደለ ጥበቡ

ገዳመ ወንያት አቡነ ሐራ ድንግል በጣም ይደንቀኛል። በፍፁም አምኖ የሄደ ሰው ድኖ ይመለሳል፣ እኔ ራሴ 'ሳይነስ' እያስቸገረኝ ለዓመታት ቆይቶ ነበር። እንደ መፍትሄ የምወስደው የእስፖርት እንቅስቃሴና 'አልመታሚን' የሚባል መድሀኒትን ነበር። አንድ ቀን የሆነች ልጅ "ታዴ እኔን የተሻለኝ አቡነ ሐራ ድንግል ፀበል ተጠምቄ ነው ሂድና ተጠመቅ" አለችኝ። ከዛም ሄድኩኝ። ፀበሉን ጠጣሁ፣ እምነቱን ተቀባሁ። እግዚአብሔር ይመስገን ሳይነስና እኔ ከተለያዬን አንድ አመት አለፈኝ። የዛሬ 2 ወር አካባቢ አንድ ልማት ባንክ የሚሰራ ጓደኛዬ ምሳ ልንበላ ተቀጣጥረን ልክ እንደኔ እንደበፊቱ አይኑን እያሸው አየሁት። ምድነው ስለው "ሳይነስ አሰቃይቶ ሊገለኝ ነው" አለኝ። እንኳን መጥፎ ሽታ ከቤት ወጥ እየተሰራ ሲቸተኝ ይነሳብኛል፣ ሽቶ ስቀባ ከላይ ከላይ ያስነጥሰኛል፣ አይኔን ስለሚበላኝ እኔም ስለማሸው እንደምታየው ጠቁሯል፣ ወደጆሮ አልፎ ያሳክከኛል በጣም ነው የተቸገርኩት" አለኝ። እኔም ፈገግ ብዬ በፍፁም እምነት አቡነ ሐራ ድንግል ሂድና እምነቱን ቀባው ፀበሉን ጠጣ አልኩት። በሳምንቱ ሄደ። በወሩ "ታዴ ላገኝህ እፈልጋለሁ" ብሎ አገኘኝ። ከዛ ሳቅ...ሳቅ እያለ "ዳንኩኝ እኮ" አለኝ። "አንተ እንዳልከኝ አደረግሁ፣ ፀበሉን ጠጣሁ፣ እምነቱን ተቀባሁ በሳምንቱ ድራሹ ጠፋ። አሁን ምንም ቢሸተኝ አይነሳብኝም። ወር ሆነኝ" አለኝ። እኔም እንደሚፈወስ እርግጠኛ ነበርኩ። ወደዚህ ያመጣሁት የማታውቁ እንድታውቁ፣ የሰማችሁ እንድታሰሙ፣ በህመም የሚሰቃዩትን እንድትነግሯቸው ነው።

አቡነ ሐራ ድንግል ገዳም በፍፁም ልቡ አምኖ ሄዶ ሳይድን የተመለሰ ሰው አላውቅም። በ2004 ዓ.ም. ከ11 ዓመት በላይ ዓይነስውር ዲዳ የነበረ ሰው ዓይኑ እንደበራለት፣ አንደበቱ እንደተከፈተለት አውቃለሁ። በወቅቱ መነጋገሪያ ሆኖ መጽሔትና ጋዜጦች የሰውየውን ምስል ይዘው ወጥተው ነበር። ፎቶውን ከስር አስቀምጬዋለሁ።

አቡነ ሐራ ድንግል ገዳም ከባህር ዳር ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ 17 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ ላጉና ቀበሌ ይገኛል። ገዳሙ የተመሰረተው በ1574 ዓ.ም በፃድቁ በአቡነ ሐራ ድንግል ነው። በቦታውም ፃድቁ አቡነ ሐራ ለ49 አመታት ያህል ሲፀልዩበት ኑረዋል፡፡ በ1626 ዓ.ም በዐፄ ሱስኒዮስ ዘመነ መንግስት የኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን በዐፄ ፋሲል እና በፃድቅ በአቡነ ሐራ በቦታው ላይ ተተክላለች፡፡ በትግራዩ ዐፄ ዮሐንስ አራተኛም አቡነ ሐራ ድንግል መቃብር ላይ ለፃድቁ ለአቡነ ሐራ ድንግል መታሰቢያ ሲባል የራሳቸው የፃድቁ ቤተ ክርስቲያን ተመስርቷል፡፡ ንጉሱ ዐፄ ዮሐንስ በራሳቸው ላይ ነቀርሳ ወጦባቸው ሲታመሙ በአካባቢው የሚፈወስ ቦታ አለ ተብለው ሰለተነገሩ ቦታውን በማፈላለግ መጥተው በፀበሉ ተጠምቀው በእምነቱ ቢቀቡ ሰለዳኑ የፃድቁን ቤተክርስቲያን እንደ አሰሩ ይነገራል፡፡

በዚህ ገዳም በየአመቱ ጥር 11 ቀን የአቡነ ሐራ ድንግልን የእረፍት ቀን፣ የካቲት 16 ቀን የእመቤታችን ማርያምን የቃል ኪዳን ቀን፣ ግንቦት 11 ቀን የአቡነ ሐራ ፀበል ተባርኮ አገልግሎት መስጠት የጀመረበት ቀንን እና ጥቅምት 19 ቀን የፃድቁ አቡነ ሐራን የልደታ ቀን ምክንያት በማድረግ ብዙ ህዝብ ከተለያየ አካባቢ ይሰበሰባል፡፡

ማንኛውንም ሀሳብና አስተያየት በዚህ ሊንክ መላክ ይችላሉ @Tadeletibebut