Get Mystery Box with random crypto!

የዐማራ ህዝብ ከልጆቹ የሚፈልገው ኑሮውን የሚኖሩለት፣ ችግሩን የሚያዳምጥለት፣ ፍኖተ-መርሁን የሚቀር | Tadele Tibebu - ታደለ ጥበቡ

የዐማራ ህዝብ ከልጆቹ የሚፈልገው ኑሮውን የሚኖሩለት፣ ችግሩን የሚያዳምጥለት፣ ፍኖተ-መርሁን የሚቀርፅለት፣ ከድህነት ይወጣ ዘንድ የሚያግዙትን ነው። የዐማራ ህዝብ የሚፈልገው እንደ ታምራት ላይኔ የሚሰድበውን፣ እንደ መላኩ ተፈራ የሚጨፈጭውን፣ እንደ ዋለልኝ መኮነን የሚከሰውን፣ እንደ ብአዴን ከሕወሓት ጉያ ተሸሽጎ የሚጨቁነውን፣ የሚዘርፈውንና የሚያዘርፈውን አይደለም።

የዐማራ ህዝብ የሚፈልገው፤ ድህነቱን የሚያስወግድ፣ ከአለበት ምጥ አውጥቶ እንደ ሙሴ የሚያሻግረውን ነው። ዐማራ የሚፈልገው እንደ ፕሮፌሰር አሥራት ክብሩን ለማስጠበቅ የሚታገሉትን፣ ትምህርት ቤት የሚገነቡለትን፣ መንገድ የሚሰሩለትን፣ ክሊኒክ የሚያንፁለትን ዐማሮችን ነው። በትግል ስም ገንዘቡን እየገፈፉ ቦርጫቸውን የሚያሰፉትን፤ ሀብት ንብረቱን ዘርፈው የሚያሸሹትን፣ ተሳድበው ለተሳዳቢ አሳልፈው የሚሰጡትን፣ ተሸማቀው የሚያሸማቅቁትን ዐማሮች አይደለም የሚሻው።

ዐማራ የሚፈልገው ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ህይወቱ
ሲያልፍ፣ መዐሕድን ወደ መኢአድ እንደቀየረው ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ያሉ ከሃዲዎች ሳይሆን፣ መዐሕድን አጠናክሮ ሊያስቀጥል የሚችል ፕሮፌሰር ነው።

ዐማራ የሚፈልገው ጎንደር፣ ጎጃም፣ ወሎና ሸዋ እያለ በጎጥ የሚከፋፍለው ሳይሆን፣ እንደ ደጃዝማች ፀሐዩ ዕንቁ ሥላሴ "የዐማራ አንገቱ አንድ ነው" በማለት አንድነቱን የሚያጠናክርለትን ነው። ዐማራን ለመበተን የትግሬው ስሁል ሚካኤል ዘመነ መሳፍንትን መርቆ ሲከፍት፣ ስሁል የበተነውን ሀገር መልሶ ለመሰብሰብ መሰዋእትነት እንደከፈለው ዐፄ ቴዎድሮስ ያለ ጀግና እንጂ የሚፈለገው እንደ ዘመነ መሳፍንት በጎጥ ከፋፍሎ የሚያናክስ ለዐማራ አያስፈልገውም። አብን ሲያጠፋ አርማው ላይ እንዳለው ንስር አድሶ ህይወት የሚዘራ ሰው እንጂ የጠፋው ሲሳደብ የሚውል አላጣንም። አሥራት ቴሌቪዥንን የሚያስቀጥል እንጂ አሥራትን አክስሞ የሚፎልል ሰው አላጣንም።

የዐማራ ህዝብ የዝነኛ ችግር የለበትም። ዝነኞች'ማ ሞልተውታል። በጥሊያን ጎዳና ቪቫ ምኒልክ፣ ቪቫ ጣይቱ የተባለላቸው ነገሥታቶች፣ እንደ ዶክተር መላኩ በያን ያሉ ፓን አፍሪካኒስቶች፣ እንደ አበበ ደምሴ ያሉ ዝነኛ ሩዋጮች፣ እንደ አክሊሉ ሀብተወልድ ያሉ የሊግ ኦፍ ኔሽን ተሟጋቾች፣ እንደ ሙሉጌታ ተስፋዬ ያሉ ባለቅኔዎች፣ እንደ ሀዲድ አለማየሁ ያሉ ብዕረኞች፣ እንደ ራስ አባተ ቧያለው ያሉ አነጣጣሪ መድፈኞች፣ እንደ ፊታውራሪ ገበየሁ ተክሌ ያሉ ምሽግ ሰባሪዎች፣ እንደ ፊታውራሪ ገብርዬ ያሉ ታማኞች፣ እንደ በላይ ዘለቀ ያሉ ጥሊያንን ያርበደበዱ አርበኞች፣ አንቱ የተባሉ ፕሮፈሰሮች፣ ባለፀጋዎች ሞልተውታል። እነዚህ ሁሉ ለኢትዮጵያ መልካም ሥራ ሰርተው ያለፉ ናቸው። ሊከበሩ ይገባል። አሁን በዚሁ ወቅት የሚያስፈልጉን ደግሞ የዐማራ ህዝብ ጥያቄ ሲነሳ ስለኢትዮጵያዊነት እና ስለአለማቀፋዊነት እየደሰኮሩ ራሳቸውን የሚያታልሉ ዐማሮች ሳይሆኑ፣ በቀጥታ እንደ ፕሮፌሰር አሥራት ህዝባቸውን ለመታደግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚደርጉ ፕሮፌሰሮች ናቸው።