Get Mystery Box with random crypto!

ከደጋ ዳሞት 6000 ጦር ይዘው የዘመቱት አሥርግና አደገኛው የጎጃሙ ዐማራ ራስ መንገሻ አቲከም እ | Tadele Tibebu - ታደለ ጥበቡ

ከደጋ ዳሞት 6000 ጦር ይዘው የዘመቱት አሥርግና አደገኛው የጎጃሙ ዐማራ ራስ መንገሻ አቲከም እኒህ ናቸው።

እስከ ምሳ ሰዓት ድረስ የሜጀር ቶሴሊ የሚመራውን የጥልያን ጦር ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀሩ ድባቅ የመቱት ራስ መኮንን ከሐረር፣ ራስ ሚካኤል ከወሎ፣ ራስ ወሌ ከቤጌምድር፣ ራስ መንገሻ አቲከም ከጎጃም፣ ፊታውራሪ ገበየሁ ተክሌ ከሸዋ ዐማሮች ናቸው። በጥልያን በኩል ከተሰለፈው 2450 ውስጥ 200 ብቻ እስኪቀር ድባቅ የመቱት፣ ከ34 የጥልያን መኮንኖች የጦር መሪውን ቶሴሊ ጨምሮ 31'ዱን የገደላቸው ይህ ጥምር የዐማራ ሠራዊት ነው። የጦር ጀኔራሉን ማጆር ቶዚሊን የገደለው ፊታውራሪ አባ ውርጂ ናቸው። አርበኛው ከጀኔራል ማጆር ቶዞሊን ጋር ፊት ለፊት ተገናኙ። ሽጉጡን እስኪያወጣ ድረስ ውርጂ ጊዜ አልሰጠውም። ትግል ገጥመው ተያይዘው ገደል ገቡ። የሁለቱም የህይወት ፍጻሜ ሆነ። አላጌ ላይ ከፊታውራሪ አባ ውርጂ በተጨማሪ ሌላ የሞተ ጀግና የጦር መሪ አለ። እርሱም ጊድን ገብሬ የሚባል የላስታና የዋግ የጦር መሪ ነበር። እህቱም ጥይት በቀሚስ ጫፍ እየቋጠረች ስታቀብል አብራ ሞታለች። እነዚህ ሁለት ሰዎች እንዲህ ተሞግሰዋል፤

"ጊድን ገብሬ የባሕር አዞ
አሁን ይደርሳል ጥይቱን መዞ
ጊድን ገብሬ ጥቁሩ ዐንበሳ
የላስታው ውጋት የዋግ ነቀርሳ
የጊድን እህት ምጥን ወይዘሮ
ጥይት አቀባይ እንዳመልማሎ"
(ሥርገው፣ ዳግማዊ ምኒልክ፣ 229-230)

በዚያው ሰሞን ልጁም አዋቂውም ዐማራውም ትግሬውም ገበየሁ ገበየሁ ብሎ አነሣው። ጎበዝ አየሁ ብሎ ስም አወጣለት። ገጣሚም እንዲህ ሲል አሞግሷል፤

"የንጉሥ ፊታውራሪ የጎራው ገበየሁ
አላጌ በሩ ላይ ማልዶ ቢገጥማቸው
ለምሳም አልበቁት ቁርስ አደረጋቸው"
(ሥርገው፣ ዳግማዊ ምኒልክ፣ 230፣
ታሪክ ዘመን፣ 233-241)