Get Mystery Box with random crypto!

ተወዳጆች ብሌን ማሞና አዲስዓለም ጌታሁን፣ 'የትንፋሽዋ ጎንደር' አቀንቃኙ አስቻለው ፈጠነ፣ አባ ስ | Tadele Tibebu - ታደለ ጥበቡ

ተወዳጆች ብሌን ማሞና አዲስዓለም ጌታሁን፣ "የትንፋሽዋ ጎንደር" አቀንቃኙ አስቻለው ፈጠነ፣ አባ ስበር ዳኘ ዋለ፣ የእረኛዬ ድራማ ተዋናይቷ ድርብዬ (እማማ ቸርነት)፣ ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ፣ ተዋናይ ተስፋሁን ከበደ፣ ያያ ዘልደታ፣ የቲክቶኳ ዝነኛ መማር፣ ተወዳጇ ተዋናይት ሜላት ነብዩ...እና ሌሎችም በባለድንጋይ ንጣፎቹ የጎንደር ከተማ ጎዳናዎች ላይ ሽር ብትን እያሉበት ነው ይመቻችሁ የሀገሬ ልጆች። የሀገር ልጅ እንዲህ ሲጫወት፣ ሲደሰት፣ እንደማዬት አስደሳች ነገር የለም።

እውነት ለመናገር እንደዘንድሮ ጥምቀት ጎንደርን እንደዚህ አድርጓት አያውቅም። ትናት ጥምቀተ ባህሩ ሲቀደስ የከተማዋ ድባብ ወደ ልዩ ከፍታ ተሸጋግሮ ነበር። የልጆቹ ፈገግታ የወጣቶቹ ዝማሬ እና የአዛውንቶቹ ፉከራ እንደተጠና የተውኔት ድግስ፤ እንደተቀመረ ሙዚቃ፤ በራሱ ዘዬ ኮለል እያለ ሲፈስ ነው የዋለው። ካህናቱ "ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ" "ሰማያዊው በመሬታዊው እጅ ተጠመቀ" የሚል ያሬዳዊ ዝማሬ ሲያስተጋቡ፣ ወጣቶች፤ ባለ ጥለት ሴቶች፣ ፍልቅልቅ ህጻናቶች ደግሞ፣

"እዩት ወሮ ሲመለስ
መድኃኔዓለም በፈረስ
ወሮ ሲመለስ
የሚካኤል አንበሳ
ሎሌው ሲያገሳ፡፡" እያሉ ይዘምሩ ነበር።

ጎንደር ላይ፣ ብዙ ሰው ከነ አያሌ ቀለሙ ይታያል የቀሳውስቱ ጥላ፣ የታቦታቱ አልባሳት፤ የቅዱሳን ስዕላት። ብዙ ድምጽ ከነ ውህደቱ ይሰማል መዝሙሩ፣ ሆያ ሆየው፣ እልልታው። ብዙ አካል ይነካካል የዘመድ ጉንጭ፣ የመስቀል፣ የእምነት አመድ። ብዙ ሽታ ያውዳል የእጣን፣ የሽቶ፣ የናፍቆት። ብዙ ነገር ከነ ጥፍጥናው ይቀመሳል ጸበል፣ ጠላ፣ ዳቦ ወ.ዘ.ተ፡፡

እንደ አምፑላንስ መብራት ቦግ ያለ ቀይ ጥለት፤ እንደ ጤዛ የሚለሰልስ አረንጓዴ ጥለት፤ እንደ ሱፍ አበባ ከሩቅ የሚስብ ቢጫ ጥለት እዛም እዚህም ይውለበለባል፡፡ በየቀሚሱ፤ በየጃኖው እና በየአካባቢው ላይ ፈሶ የሚታየው የሀገር ምልክት ነው፤ የሀገር ፍቅር ነው፤ የሀገር ጌጥ ነው፡፡ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለም የሚዘንብ ነው የሚመስለው፡፡ ባጠቃላይ ጎንደር ላይ ጥምቀትን ሲያከብሩ ኢትዮጵያን እየሞሸሩ ያህል ነው ድብልቅልቅ ያለ ስሜት የሚሰማችሁ።