Get Mystery Box with random crypto!

#ሼር_ፖስት ሌላኛው የአዲስ አመት መምጣቱን የሚያበስረው እንግጫ ነቀላና ከሲኝ አጨዳ በዓላት ደግ | Tadele Tibebu - ታደለ ጥበቡ

#ሼር_ፖስት ሌላኛው የአዲስ አመት መምጣቱን የሚያበስረው እንግጫ ነቀላና ከሲኝ አጨዳ በዓላት ደግሞ ደረሰ። ይህ በዓል በጎጃም በየዓመቱ ከዻጉሜ 1 ቀን እስከ መስከረም 1 ቀን በድምቀት የሚከበር በዓል ሲሆን፣ ልጃገረዶችና ጎረምሶች የአዲስ ዓመት መግባትን ለማብሰር የሶሪት አበባ ፣ የአደይ አበባና የከሲኝ ቅጠል ለቤተዘመዶቻቸው በማበርከትና በመጨፈር መልካም ምኞታቸውን ጭምር የሚገልፀበት ባህላዊ ስነ ስርዓት ነው።

እንግጫ የሳር አይነት ነው። ልጃገረዶች ወንዝ ወርደው እንግጫ ይቆርጣሉ። በዚያው ቀን ማምሻ የቆረጡትን እንግጫ በአደይ እና በሶሪት አበባ ይጎነጉኑታል። ሲነጋ ሊጃገረዶቹ ከያሉበት ተጠራርተው በመሰባሰብ በየሰው ቤት እየዞሩ የተጎነጎነውን እንግጫ የቤቱ ምሰሶ ላይ በማሰር አዲሱን አመት ያበስራሉ። ስጦታውም ከቤተ ክርስቲያኑ አምድ ላይ ይታሰራል፡፡ ይህ ባህላዊ ክዋኔ በዜማና በጭፈራ የታጀበ ነው።

የቅዱስ ዮሀንስ ያልዘፈነች ቆንጆ
ቆማ ትቀራለች እንደ ሰፈር ጎጆ

እቴ አደይ አበባ ነሽ
ውብ ነሽ ውብ ነሽ

ይህንን ዜማ ልጃገረዶች እንግጫውን እየነቀሉ ያዜማሉ። ይህንን ዜማ ሲሰሙ የአካባቢው ጎረምሶች ወደ ልጃገረዶቹ ይመጣሉ። ይህኔ ታዲያ ዜማው ይቀየራል።

እንግጫችን ደነፋ፣
ጋሻውን ደፋ

እንግጫዬ ነሽ ወይ
እሰይ እሰይ

የቅዱስ ዮሀንስ የመስቀል የመስቀል
የላክልኝ ድሪ ሰላላ መላላ
መልሰህ ውሰደው ጉዳይም አይሞላ

ይህንን ዜማ ሲሰማ ለወደዳት ልጃገረድ ማተብ ያስርላታል።

ከእንግጫ ነቀላ በተጓዳኝ ከነሐሴ እኩሌታ ጀምሮ የሚከበረው በዓል ከሴ አጨዳ ነው፡፡ ከሴ ጥሩ ሽታ/መዓዛ ያለው ተክል ወይም ቁጥቋጦ መጠሪያ ስም ነው፡፡ የከሴ አጨዳ የፆመ ፍስለታን መፈታት ምክንያት በማድረግ ነሐሴ 16 ጀምሮ የተክሉን ቅርጫፎች በመቁረጥ ዝማሬ እያሰሙ ለቤተሰብ፣ ለጎረቤት እና ለቤተ ክርስቲያን እንኳን አደረሳችሁ በማለት ስጦታ የሚያበረክቱበት በዓል ነው፡፡ የበዓሉ ስያሜም ከተክሉ ስምና ነሐሴ 16 ላይ ካለው ክዋኔ ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነው፡፡ እንኳን አደረሳችሁ!