Get Mystery Box with random crypto!

አማራ ባንክ ከባንክ ባሻገር ብዙ ትምህርት አግኝተንበታል። ከዚህ በፊት ያልሞከርነው የለም ግን በተ | Tadele Tibebu - ታደለ ጥበቡ

አማራ ባንክ ከባንክ ባሻገር ብዙ ትምህርት አግኝተንበታል። ከዚህ በፊት ያልሞከርነው የለም ግን በተለያዩ ምክንያቶች ከሽፏል፤ ያልጀመርነው የለም ግን ወደፊት መራመድ ሳንችል ቀርተን ረግረግ ውስጥ እንደሰጠመች እህያ ገብተን ቀርተናል፤ የተጀመረው ትግል ቶሎ ያበበ ይመስልና ሳያፈራ ቶሎ ደርቋል፤ ደርቆ አልቀረም፤ ሻግቷል፤ ሻግቶ አልቀረም፤ በስብሷል፤ በስብሶ ፈራርሷል። በዐማራ ታሪክ ትግል ውስጥ እንዲህ ያለ የመክሸፍ ታሪክ ለብዙ ምዕተ ዓመታት ግዙፍ ቦታ የያዘ ይመስለኛል። ዛሬ ይሄን የመክሸፍ ታሪክ የሰበረው አማራ ባንክ ብቻ ነው። የሩቁን ትተን ከቅርቡ ስንነሳ መዐሕድ ከሽፏል፤ አሥራት ቴሌቪዥን ከሽፏል፤ አብን'ም የመክሸፍ መንገድ ላይ ይገኛል.....

ዐማራ ይጀምራል ይከሽፍበታል። የ1953ቱ የመንፈቅለ መንግሥት ሙከራ ያደረጉት መንግሥቱ ነዋይ፣ ገርማሜ ነዋይና ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ ሦስቱም ዐማሮች ናቸው። ግን ሙከራቸው ከሽፏል። የፀጥታ ሀላፊው ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ ራሳቸውን አጠፉ፡፡ ገርማሜ ራሳቸውን አጠፉ፡፡ መንግሥቱ ነዋይ ልክ እንደ በላይ ዘለቀ በስቅላት እንዲቀጡ ተፈረደበት፡፡

የጃንሆይን መንበር ያነቃነው የጎጃም የገበሬዎች ዐመፅ ነበር። ከታኅሣሡ የመንፈቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ የተማሪዎችን አብዮት የመሩት እንደ ተራራ የገዘፈ ታሪክ የነበራቸው የዐማራ ተማሪዎች ነበሩ። ምንም እንኳን ዐማራን ለማጥፋት በትር ሆነው ቢያገለግሉም በተማሪዎች የለውጥ እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና የነበራቸው እነዋለልኝ መኮንን፣ ጎንደር ፋሲለደስ ትምህርት ቤት፣ ደሴ የወይዘሮ ስሂን ትምህርት ቤት ዘውዳዊው ሥርዓት እንዲገረሰስ የትግል ማዕከል ሆነው አገልግለዋል።

ነገርግን ትግላቸው ገና ከጅምሩ መስመሩን ስለሳተ ከሸፈ፤ ይባስ ብሎ፣ "ማርክስ እንዳለው …፣ ኤንግልስ እንዳለው…፣ ሌኒን እንዳለው …፣ ማኦ እንዳለው …፣ ቼጉቬራ እንዳለው…፣ ሆቺሚኒ እንዳለው…፣ እስታሊን እንዳለው…፣ " ወዘተ እያሉ ዐማራ ሆነው በፀነሱት ትግል መልሰው ዐማራውን ከሰሱት። በዚህ የታሪክ ክሽፈት ውስጥ ሀገሪቱ በደርግ እጅ ወደቀች።

ለ17 ዓመት በአብዮት ስም የቀጠለው ደርግ በዐማራው ላይ የደረሰው እልቂት፣ እሥራት፣ ስደት፣ ውርደት፣ ጉስቁልና፣ የአእምሮ ጉዳት፣ የአካል ስንኩልነት፣ በአገር ሀብት ላይ፣ በእጽዋት፣ በእንስሳት፣ በአዕዋፍም ላይ የተፈፀመው ውድመት መቼም የማይረሳ፣ በዐማራ ሕዝብ መስተልይ ተቀርጾ ያለ ጉዳይ ነው።
በእብሪት፣ በድንቁርናና ስካር ናላቸው ያዞረው የደርግ አለቆች የዐማራ ልጆችን ረሸኑ። ሕግና ሥርዓት የአብዮቱን ግለት የሚያቀዘቅዙ ሂደቱንም የሚያደናቅፉ የቡርዥዋ መሣሪያ ናቸው እየተባለ ሕግ ተሽሮ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ነፃ እርምጃ ተፈቀደ። ዐማራ ልጆቹ በቀይ ሽብር እንደ ቅጠል እረገፉበት።

"ቀይ ሽብር ሞኝ ነው ጠላቱን አይለይም፣
ያገኘውን ሁሉ ያጋድማል የትም።" የተባለው በዚህ ዘመን ነው።

አሁንም ዐማራው ለውጥ በመፈለግ ትግል ጀመረ። ደርግን በመቃወም፣ መሳሪያ አንስቶ በመታገል ቀዳሚው የዐማራ ህዝብ ነበር።ለምሳሌ፣ በ1970'ዎቹ በምድረ ጎጃም ሞጣና ብቸና እነ ባምላኩ አየለ፣ የሺዋስ አያሌው፣ ውባለ ተገኑና ምቹ ውድነህ ለሕዝባቸው መብት መከበር በመምራትና በማጠናከር ረገድ የተጫወቱት ሚና ቀላል አልነበረም። ከዋና ዋናዎቹ የጎጃምን አመፅ ከመሩት ሰዎች መካከል የብቸናው ባምላኩ አየለ አንድ አይና ጀግና መሪ ስለነበር፣

"በአምላኩ አባ ጊዮን የበረሃው መናኝ
በአንድ አይኑ ፀዳቂ በሌላው ተኮናኝ" ተብሎ ተወድሷል።

ነገርግን በዐማራ ውድ ልጆች ከፍተኛ መስዋዕትነትና በሌሎችም ሕዝቦች ተጋድሎ ደርግ ቢገረሰስም ቀጥሎ በመጣው የህወሓት ሥርዓት ዐማራ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጨቋኝ፣ ተሳዳጅና የትም የሚገደል ሆነ።

እንደገና የህወሓት/ኢሕአዴግ ሥርዓትን በመጣል የዐማራ ህዝብ ቀዳሚ ነው። በ2008 ዓ.ም. የገነፈለው የዐማራ ህዝብ አመፅ ለህወሓት መውደቅ ከፍተኛ ሚና ነበረው። ነገርግን ዐማራ መስዋዕትነት የከፈለለት ትግል አሁንም ሃዲዱን ስቶ ቁልቁለት ላይ ይገኛል....

ዐማራ ትግል ይጀምራል፤ ተቋም ለመመሥረትም ይጥራል ግን ይከሽፍበታል። ዐማራ እንደዚህ ያሉ የመክሸፍ ብዙ ታሪኮች አሉት። በተጨባጭና በሚዳሰስ መልኩ ይሄን የመክሸፍ ታሪክ የሰበረው አማራ ባንክ ብቻ ነው።

አማራ ባንክንም ቢሆን ገና ከፅንሱ ለማጨናገፍ ያልተሄደበት ሙከራ የለም፤ የባንኩን ፕሮሰስ የሚያስኬዱትን ሰዎች ሳይቀር የፌስቡክ ዘመቻ ተከፍቶባቸው ብዙ ተብለዋል፤ ታምተዋል፤ ነገርግን ሰዎቹ የዋዛ ስላልነበሩ መሰናክሉን ሁሉ በጣጥሰው በአንድ ቀን ብቻ 72 ቅርንጫፎችን በመክፈት ታሪክ ሰርተዋል።

ከዚህ ባንክ የምንመራው ብዙ ቁምነገር አለ። ትግስት፣ የዓላማ ፅናት፣ እውቀት፣ ብልሃት፣ እልህ፣ ቁጭት፣ አይበገሬነት፣ ታማኝነት፣ መተባበር፣ መደጋገፍ፣ መደማመጥ፣ በመጨረሻም አሸናፊ ሆኖ መውጣት የአማራ ባንክ መገለጫዎች ናቸው።

ከዐማራ ባንክ እኩል ታቅደው የነበሩት የ" እኛ ለእኛ በእኛ" የመቶ ፕሮጀክቶች ለምሳሌ፣

1 ጣና ፔትሮሊየም
2. ዳግማዊ ምኒልክ ዩኒቨርስቲ
3.ዛግዌ የሕክምና አገልግሎቶች ማዕከል
4.ጃኖ ባንክ አክሲዮን ማህበር
5.አምደ ወርቅ ሲሚንቶ ፋብሪካና ሌሎችም ከአማራ ባንክ ልምድ ቀስመው የሀሳቡ ባለቤቶች ቢያንቀሳቅሱት እና የክሽፈትን ታሪክ ተረት ቢያደርጉት
ትውልድ ይኮራ ነበር።

ለሀሳብ ለአስተያየት በዚህ ሊንክ @Tadeletibebut