Get Mystery Box with random crypto!

፨እንዴት በሀይማኖቴ ተደስቸ ልኑር? ፨ ፨፨፨ 1) ምስጋና ባለህ ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን አመስግን | መንፈሳዊ ግጥሞች

፨እንዴት በሀይማኖቴ ተደስቸ ልኑር? ፨
፨፨፨
1) ምስጋና
ባለህ ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን አመስግን።
ምንም ባይኖርህ እንኳን ወደ በጎው ሁሉ እንዲመራህ እየጸለይክ አመስግን ። ያንተን ያህል  ጤና ያንተን ያህል ከጎንህ የሚሆኑ ቤተሰቦች ፣ ስራ ካለህ ያንተን ያህል ስራ የሌላቸው ብዙዎች ናቸው፣
እግዚአብሔር ያደረገልህን ውለታ (ተዓምር ሊሆን ይችላል) አስታውስ በርሱ ደስ ይበልህ አመስግነውም።እግዚአብሔር ከመፈጠራችን ጀምሮ እስከ እድገታችን እኛ ባናስተውለውም ያደረገልን ተዓምር ብዙ ነው።
• ለምሳሌ እኛ እኮ የተወለድነው በየቦታው እንደአሁኑ ክሊኒክም ሆነ  የጨቅላ ህፃናት ህክምና ባልነበረበት ዘመን ነው።
• ብዙዎቻችን ክትባት ባንከተብም ከተለያዩ የልጅነት በሽታዎች ተርፈን አድገናል።
•  ብዙዎቻችን የውሀ እጦት ቢያሰቃየንም ከትራኮማ አምልጠናል
• ብዙዎቻችን ስንት ጊዜ ነው ከመኪና አደጋ የተረፍነው
•  ብዙዎቻችን በየሀገሩ ከነበሩ አለመረጋጋቶች ከጥይትና ከቦንብ ፍንዳታ አምልጠናል።
እንዲህም አመስግነው መድሀኒታችን  ሆይ ምን ውለታ  መመለስ ይቻለኛል? ላንተ እዘምራለሁ እንጅ


2) ሰዎችን አትውቀስ
ሰዎች ሁሌም በሁሉም መልኩ ፍፁም አይደሉም ጥሩ ነገር እንዳላቸው ሁሉ አንተ ክፉ የምትለው(ለእነርሱ እንደ ጥሩ የሆነ) ባህሪም ሊኖራቸው ይችላል
ሰዎች መልካም እንደሆኑ አስብ ዓሉታዊነትን አስወግድ

3) መልካም መልካሙን ማሰብ
ስለራስህም ሆነ ሌሎች በአዕምሮህ መልካም ነገር አስብ
የስበት ህግ በሁሉም ቦታ ይሰራል አንተ ስለራስህ የምታስበውን ነው የምትሆነው በራስህ ደስተኛ መሆን አለብህ። እኔ መልካም አይደለሁም ከሚለው ሐሳብ ይልቅ እራስክን መልካም ለማድረግ መጣር ላይ አተኩር።ጥሩ አርአያ ይኑርህ የእነርሱን ለመከተል ወስነህ ተጓዝ ነገር ግን ለምን እርሱን አልሆንኩም ብለህ ራስክን አትውቀስ አታወዳድርም። አርአያህ ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ሆነ አስተውል እርሱ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተም እኔን ምሰሉ እንዳለን።

4) መዝሙርና የመዝሙር መሣሪያ
መዝሙር ያሬዳዊ የሆኑ ዜማውችን ማዳመጥ ልብን ይመስጣል እግዚአብሔርን አመስጋኝ ያደርጋሉ።
የመዝሙር መሣሪያን መለማመድም ሆነ መተግበር በሀይማኖትህ ከምትደሰትበት አንዱ ነው።

5) ግዕዝን ማወቅ
የኢኦተቤ ከግዕዝ ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላት ግዕዝን ማወቅ እጅግ ደስታን ይሰጣል ቅዳሴዋ ውዳሴዋ ቅኔዋ  አብዛኛው በግዕዝ ነው ግዕዝን ለመማር ባትችል እንኳን በቀላሉ ለመረዳት የሚያስችሉ መጽሀፍት በሶፍት ኮፒም ይሁን በሀርድ ይገኛሉ። እነሱን በመጠቀም በቤክ ውስጥ ሲዘመር ሲቀደስ ማህሌት ሲቆም ላለመደናገር ቀደም ብሎ ሊዘመሩና ሊቀደሱ የሚችሉ ዜማዎችን እስከ ትርጉሙ አውቆ እየገቡ መሳተፍ፤ እነግርሃለሁ ከዚህ ዓለም ውጪ የሆነ ነገር ነው የሚሰማህ ደስታ።

6) ጸሎት
ከልጅነትህ ጀምሮ እየተንከባከበ ካሳደገህ ከሚሳሳልህ ከስጋ አባትህ ጋር ስታወራ ደስ ይልሃል።
ጸሎት ደግሞ ከሰማዩ አባትህ ጋር በኑሮህ ሁሉ ከሚረዳህ ሰላምን ከሚሰጥህ፣ ቸርነትን ከሚያደርግልህ ምንም ስትሆን አባ አባት ብለህ እንድትጠራው የልጅነትን መንፈስ ከሰጠህ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ስትነጋገር እንዴት ደስ አይልህ። በጸሎት ከጻድቃን ቅዱሳን ማህበር ከመላአክት ጋር ስትነጋገር እንዴት ደስ አይልህ።
በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴህ እግዚአብሔር እንዲረዳህ ፀሎት አድርግ እንደሚረዳህም እየተገነዘብክ ደስ ይበልህ
በጸሎት አንተ የምትፈልገውን አስበህ መጠየቅ ነው ሚጠበቅብህ ሐሳብህን እግዚአብሔር ላይ ተማምነህ መጣል ነው ስራህን እግዚአብሔር ያከናውንልሀል ደስ አይልም።

7) መጽሐፍትን አንበብ
ቅዱሳን መጽሐፍት የነፍስ ምግብ ናቸው ያረጋጋሉ፣ ተስፋ ይሰጣሉ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያገናኛሉ፣ ወደ ንስሀ ይመራሉ።
8) ከሀጢአት መራቅ ንሰሀ መግባት
ብዙ ማብራሪያ መስጠት ይቻላል ባጭሩ ግን ሰውነትህ ቆሽሾ ሻወር ወስደህ ለስጋህ ምን እንደሚሰማህ አስበው የነፍስህንም ሀጢአት ሲወገድላት ስጋህ ይደሰታል ነፍስህ ሐሴት ታደርጋለች
9)  ተሰፋ
ከዚህ ሁሉ በላይ በተስፋ ደስ ይበልህ ተስፋችን መንግስተ ሰማያት ናት። በዚህ ዓለም ምንም መከራ ቢፈራረቅብን ኃላፊ ነው የዚህ ዓለም ደስታም እንደዚሁ አንተ ደግሞ በጠበቧ መንገድ ስለምትጓዝ በብዙ ፈተና መካከል እንኳን ደስ ይበልህ። በሚመጣው አለም የዘላለም ህይወት እንዳለህ እያሰብክ በክርስቶስ ደስ ይበልህ። እግዚአብሔር ለቅዱሳን በሰጠው ቃል ኪዳን ደስ ይበልህ። በሐሳብህ የመላአክትን ማህበር የጻድቃንን ማህበር እያየህ ደስ ይበልህ።
10) ስጋወ ደሙን መቀበል
የደስታ መጨረሻ ከክርስቶስ ጋር ህብረት መፍጠር ነው። ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉ ወደዚህ ማማ መድረሻዎች ናቸው እውነተኛ የደስታ ምንጭ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።
እነዚህና ሌሎች በሐይማኖት ተደስተን እንድንኖር ያስችለናል። ከዚህ በተጨማሪ አንተ ራስህ ምን እንደሚያስደስትህ በማሰብና በመመርመር ማግኘት ይቻላል።
@Spritualpoem
    @Spritualpoem
    @Spritualpoem