Get Mystery Box with random crypto!

ሲያስተምሩ በመዋል ሲመሽ ወደ ሐይቁ በመግባት ሲጸልዩ ያድሩ ነበር፡፡ በሐይቅ እስጢፋኖስና በዙርያው | ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ)

ሲያስተምሩ በመዋል ሲመሽ ወደ ሐይቁ በመግባት ሲጸልዩ ያድሩ ነበር፡፡ በሐይቅ እስጢፋኖስና በዙርያው ለነበሩ አበው ማታ ማታ አንድ ብርሃን ወደ ሐይቁ ሲገባ ጠዋት ጠዋትም ሲወጣ ይታያቸው ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን በገዳሙ አባቶች ልመናና በልዑል እግዚአብሔር ትዕዛዝ ወደ ሐይቅ ገዳም ገብተው አበምኔት ሆኑ፡፡

ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ከደሴ 30 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ሲሆን የመሠረቱት ካልዕ ሰላማ የተባሉ ግብፃዊ ጻድቅ ናቸው፡፡ ሐይቅን አባ ሰላማ ካልዕና ዐፄ ድል ነአድ በ862 ዓ.ም ነው የቆረቆሩት። ገዳሙን ካቀኑት በኋላ "የማንን ታቦት እናስገባ?" ብለው ሲያስቡ ቶራ የምትባል እንስሳ ጭነት ተጭና ከመካከላቸው ተገኘች፤ ጭነቱን አውርደው ቢያዩት በሐር ጨርቅ የተጠቀለለ የቅዱስ እስጢፋኖስንና የቅዱስ ጊዮርጊስን ሁለት ታቦት አገኙ፡፡ በላዩም ላይ "ይህንን ታቦት በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የተሰወሩ ቅዱሳን ከእግዚአብሔር ታዘው የላኩት ነው" የሚል ጽሑፍ አገኙ፡፡ ይህ ከሆነ ከ 400 ዘመን በኋላ ነው አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ወደዚህ ቦታ የመጡት፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ለ52 ዓመት ቀን ቀን መንፈሳዊ ሥራቸውን እየሠሩ ሌሊት ሌሊት ሐይቁ ውስጥ ቆመው ሲጸልዩ ያድራሉ፡፡

አባ ኢየሱስ ሞዐ በሐይቅ እስጢፋኖስ በአበ ምኔትነት በቆዩባቸው 45 ዓመታት ከየገዳማቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመገልበጥና በማሰባሰብ የመጀመርያው ዘመናዊ የቤተ ክርስቲያን ቤተ መጻሕፍት በሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡ በዚሁ ገዳም ውስጥ የመጀመርያውን የቤተ ክርስቲያን ቋሚ ትምህርት ቤት በማቋቋም 800 መነኰሳትን በትምህርተ ሃይማኖት አሠልጥነው በንቡረ ዕድነት ማዕረግ ሾመው በመላ ሀገራችን እንዲሠማሩ አድርገዋቸዋል፡፡ ከእነዚህም ተማሪዎቻቸው መካከል አቡነ ተክለ ሃይማኖት (ደብረ ሊባኖስ)፣ አቡነ ኂሩተ አምላክ (ጣና ሐይቅ ዳጋ እስጢፋኖስ)፣ አቡነ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ (ቦረና)፣ አባ በጸሎተ ሚካኤል (ቦረና)፣ አቡነ ገብረ እንድርያስ (ቦረና)፣ አቡነ ሕዝቅያስ (ቦረና)፣ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ዳውንት)፣ አቡነ አሮን (መቄት)፣ አቡነ ተክለ ኢየሱስ ሞዐ (ሐይቅ)፣ አቡነ አላኒቆስ (ትግራይ)፣ አቡነ በግዑ (ሐይቅ)፣ አቡነ ሠረቀ ብርሃን (ሐይቅ)፣ አቡነ ብስጣውሮስ (ሐይቅ)፣ አቡነ ዮሴፍ (ላስታ) ዋና ዋናዎቹና በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ጻደቁን ንጉሥ ዐፄ ይኩኖ አምላክንም በትምህርተ ሃይማኖት አንጸውና ኮትኩተው ያሳደጉት ጻድቁ አባታችን ናቸው፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ መጥተው በሐይቁ ዳር ቆመው ሳለ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ በእግሩ በውኃው ላይ እየሄደ እያሳያቸው ተከትለውት እንዲሄዱ ነገራቸው። አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ሐይቁን በእግራቸው ጠቅጥቀው ተራምደው ተሻግረው አቡነ ኢየሱስ ሞዐን አገኟቸው፡፡ እርሳቸውም አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ እርሳቸው እየመጡ እንደሆነ በመንፈስ ዐውቀው ነበርና ሲያገኟቸው በጣም ተደስተው ከተቀበሏቸው በኋላ አመነኵሰዋቸዋል፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ እጅግ በጣም ብዙ መነኰሳትን አፍርተዋል፡፡ የመጀመሪያው መነኩሴ አባ እንጦንስ ነው፡፡ እንጦንስ መቃርስን፣ መቃርስ ጳኵሚስን፣ ጳኵሚስ ቴዎድሮስን፣ አቡነ አረጋዊንና 8ቱን ቅዱሳን አመነኰሱ፡፡ አቡነ አረጋዊም ወደ ኢትዮጵያ በ460 ዓ.ም መጥተው ክርስቶስ ቤዛን፣ አባ ክርስቶስ ቤዛም መስቀለ ሞዐን፣ መስቀለ ሞዐም አባ ዮሐኒን፣ አባ ዮሐኒም አባ ኢየሱስ ሞዐን፣ አባ ኢየሱም ሞዐም አቡነ ተክለ ሃይማኖትን አመነኰሱ፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ምን ያህል ቀደምትና ባለ ታሪክ አባት እንደሆኑ ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡

በዮዲት ጉዲት እጅጉን ተጐድታ የነበረችው አገራችን ዳግም የወንጌሉ ብርሃን እንዲበራባት ሊቃውንት፣ እንዳይታጡባት፣ ቅዱሳት መጻሕፍት እንዳይቆነጻጸሉ፣ መነኰሳት አባቶች ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ወርደው ገዳማትን እንዲያስፋፉ ያደረጉት አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለአገራችን ትልቅ ባለውለታ ናቸው፡፡ በተለይም በሐይቅ እስጢፋኖስ ያፈሯቸውን 800 ሊቃውንት መነኰሳት በመላዋ ኢትዮጵያ በመሰማራታቸው ዛሬ የምናያቸውን አብዛኛዎቹን ገዳማትና ቅዱሳት መጻሕፍት አቆይተውልናል፡፡ አባታችን ለ45 ዓመታት ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምን በአበ ምኔትነት እያስተዳደሩ ከቆዩ በኋላ ኅዳር 26 ቀን 1292 ዓ.ም በዕለተ እሑድ ዐርፈዋል፡፡ ከአባታች ከአቡነ ኢየሱስ ሞዐ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ።

በየቀኑ ይህን ቴሌግራም ላይ ማግት ከፈለጉ ከታች ያለውን ሊኩን ይጫኑት።

@sigewe

https://t.me/joinchat/AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA