Get Mystery Box with random crypto!

'በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን'። እንኳን ለማዕከለ ክረምት ለዕጒ | ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ)

"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

እንኳን ለማዕከለ ክረምት ለዕጒ(ጓ)ለ ቋዓትና ደስያት ለሚታሰብበት ሳምንት እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።

+ + +
የዚህ ሳምንት መዝሙ፦ ሃሌ ሉያ "ይሁበነ ዝናመ በጊዜሁ ይሁበነ ዝናመ በጊዜሁ ወይሁበነ እክለ በረከት፤ አዝ፣ ያርኁ ክረምተ ይገብር ምሕረተ ወይሁበነ ዝናመ በረከት፤ አዝ፣ ከሢቶ ዐይኖ ሰፊሖ የማኖ ይፌኑ ሣህሎ ወበዘአእመረ ይሴባሕ፤ አዝ፣ ወሠርዐ ሰንበት ለሰብእ ዕረፍተ ወብውህ ሎቱ ይኅድግ ኀጢአተ ዐይነ ኵሉ ነፍስ ይሴፎ ኪያከ ኪያሁ ይሁቦሙ ሲሳዮሙ በጊዜሁ"። ትርጉም፦ ዝናመ ምሕረቱን በጊዜው ይሰጠናል፤ እክለ በረከቱንም በጊዜው ያድለናል፤ አንቀጸ ክረምትን ይከፍታል (ያመጣል) ምሕረትንም ያደርጋል፤ የበረከት ዝናምንም ይሰጠናል፤ የፍቅር ዓይኖቹ ከፍቶ የምሕረቱን ቀኝ እጁን ዘርግቶ ቸርነቱን ይቅርታውን ይልካል፤ እርሱ ባወቀ ይመሰገናል፤ ለሰው ልጅ ዕረፍት እንዲሆን ሰንበትን ሠራ ኃጢአትን ይቅር ይል ዘንድ የሁሉም ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፤ እርሱም በጊዜው ምግባቸውን ይሰጣቸዋል። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በድጓው ላይ።

+ + +
ዕጕ(ጓ)ለ ቋዓት፦ ይህ ክፍለ ክረምት ከነሐሴ 10 እስከ ነሐሴ 27 ቀን ድረስ ያሉት ዕለታት የሚጠሩበት ነው። በዚህ ክፍል ክረምት ፍጥረታትና በባሕር የተከበቡ ደሴቶች የሚታወሱበት ሲሆን ወቅቱም ዕጕ(ጓ)ለ ቋዓት ይባላል። ዕጕ(ጓ)ለ ቋዓት የሚለው ቃል ቁራን ሲያመለክት፤ ቁራ ሲወለድ ያለ ፀጉር (ያለላባ) በሥጋ ብቻ ይወለዳል። እናትና አባቱም እነርሱን ባለመምሰሉ ደግንጠው ይሸሻሉ፤ በዚህ ጊዜ የሚንከባከበው ያጣል፤ ምግብ በሚያስፈልገው ሰዓት አፉን ከፈት ያደርጋል፤ እግዚአብሔር በረድኤት ተሕዋስያንን ብር ትር እያደረገ ከአፉ ያስገባለታል ይመግባል።

አባታች ኢዮብ "ልጆቹ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ የሚበሉትም አጥተው ሲቅበዘበዙ ለቁራ መብልን የሚሰጠው ማን ነው?" ኢዮ 38፥41 ብሎ እንደ ገለጠው ያ ዕጕ(ጓ)ለ ቋዓት እግዚአብሔር የሰጠውን እየተመገበ ቆይቶ ሲጠነክር እንደ እናቱና እንደ አባቱ ፀጉር ያወጣል። በዚህ ጊዜ እናትና አባቱ ቀርበው ይንከባከቡታል።

በሥነ ፍጥረት አቆጣጠር በክንፍ የሚበሩ የሰማይ አዕዋፍን ሁሉ ይወክላል። ይህን አምላካችን እግዚአብሔር ለፍጥረት ሁሉ የሚያስብ በመሆኑ ርኅርኄ ለተመላው አምላክነቱና ከሃሊነቱ መታሰቢያ እንዲሆን ይህን ወቅት ቤተ ክርስቲያን "ዕጒ(ጓ)ለ ቋዓት" በማለት ታስታውሰዋለች።

+ + +
ደስያት፦ ማለት በውኃ የተከበቡ ቦታዎች ማለት ነው። እነዚህን ቦታዎች በውኃ እንዲሸፈኑ አድርጎ በውስጣቸው ያሉትን ሰዎች፣ እንስሳት፣ አራዊትና አዕዋፍ ሁሉ የሚጠብቃቸው፤ በወርኃ ክረምት የወንዞች ሙላት የአብሕርትና የውቅያኖስ መነዋወጥ አይሎ እንዲያጠፋቸው ሁሉም ከልኩ እንዳያልፍ በማድረግ በደስያት ውስጥ የሚኖሩትን ፍጥረታት በተስፋና በእምነት አበርትቶ የሚያኖራቸው እግዚአብሔር ነው። ይህን ድንቅ ሥራ ያዩ ሰዎች እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ፤ ከሃሊነቱን ያደንቃሉ።

እንደዚሁ በደሴት (በቤተ ክርስቲያን) የተጠጉ ሁሉ ከሞተ ሥጋና ከሞተ ነፍስ ይጠበቃሉ። በዚህ ወቅት ክፍለ ክረምቱ እንደተገባደደ ውኃው እየጠራ፣ መሬቱ እየረጋ፣ ደመናውና ጉሙ እየቀለለ፣ የወንዙ ሙላት እየጎደለ፣ የክረምት ምግባቸውን ይዘው በየዋሻው የከረሙ ጭልፊቶችና አሞራዎች ድምፃቸውን እያሰሙ ምግብ ፍለጋ ሲወጡ የሚታዩበት ወቅት ነው። ምንጭ፦ ኆኅተ ስብከት ዘቅዱስ ያሬድ ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ።

+ + +
የዕለቱ ምስባክ፦ "ዐይነ ኵሉ ነፍስ ይሴፎ ኪያከ። እንተ ትሁቦሙ ሲሳዮሙ በጊዜሁ። ትሰፍሕ የማነከ ወታጸግብ ለኵሉ እንስሳ ዘበሥርዓትከ"። መዝ 144፥15-16። የሚነበቡት መልዕክታት ዕብ 3፥1-ፍ.ም፣ ያዕ 5፥1-12፣ የሐዋ.ሥራ 22፥1-22። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 6፥41-ፍ.ም። የሚቀደሰው የቅዱስ ኤጲፋንዮስ ቅዳሴ ቅዳሴ ነው። መልካም የነቢዩ የቅዱስ ሚክያስ የዕረፍትበዓል። ለሁላችን ይሁንልን።

በየቀኑ ይህን ቴሌግራም ላይ ማግት ከፈለጉ ከታች ያለውን ሊኩን ይጫኑት።

@sigewe

https://t.me/joinchat/AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA