Get Mystery Box with random crypto!

'በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን'። ነሐሴ ፳፩ ( | ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ)

"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

ነሐሴ ፳፩ (21) ቀን።

እንኳን ለኢትዮጵያዊ ጻድቅ ኤርትራ አገር የሚነኘው ደብረ ጥሉል ገዳምን ለመሰረቱ በዐፄ ሱስንዮስ ዘመን የነበረውን የቤተ ክርስቲያንን ጥፋት ላለማየት ሳይወለዱ በእናታቸው ማኅፀን 7 ዓመት ከ6 ወር ለቆዩት ለታላቁ አባት አቡነ አብራኒዮስ ዓመታዊ ለዕረፍት በዓላቸው በሰላም አደረሰን።

+ + +
አቡነ አብራኒዮስ፦ አባታቸው ወልደ ክርስቶስ እናታቸው ወለተ ትንሣኤ የሚባሉ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ የተወለዱት በ1624 ዓ.ም ምሥራቅ ጎጃም አካባቢ ልዩ ስሙ እነብሴ ይሁን እንጂ ተጋድሏቸውን ያደረጉትና ገዳማቸውን የገደሙት በዛሬዋ ኤርትራ ውስጥ ነው፡፡ ገዳሙ ኤርትራ ውስጥ ዞባ ድባርዋ ደቂ ድግና በተባለ አካባቢ ይገኛል፡፡ የገደሙት ጻድቁ በ1705 ዓ.ም ነው፡፡

አቡነ አብራኒዮስ የተፀነሱት በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል አብሳሪነት ነው፡፡ ነገር ግን ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ጻድቁ በዐፄ ሱስንዮስ ዘመን የነበረውን የቤተ ክርስቲያንን ጥፋት ላለማየት ሳይወለዱ በእግዚአብሔር ፈቃድ በእናታቸው ማኅፀን 7 ዓመት ከ6 ወር ተቀምጠዋል፡፡ በዚህም ወቅት እሳት ልትጭር ከጎረቤቷ የመጣች አንዲት ሴት የአቡነ አብራኒዮስ እናት "የማትወልጂው ምን ሆነሽ ነው?" ብላ ስትናገር ጻድቁ በእናታቸው ማኅፀን ሆነው "…ለምን ክፉ ትናገሪያለሽ?" ብለው መልስ ሰጥተዋታል፡፡ ይህም ቅዱሳን ልክ እንደ ነቢዩ ኤርምያስ ገና በእናታቸው ማኅፀን ሳሉ እንደሚመረጡ አንድ ማሳያ ነው፡፡

በርካታ ምእመናንን በሰማዕትነት ከገደሉ በኋላ በመጨረሻም ዐፄ ሱስንዮስ በመቅሰፍት ተመተው ሊሞቱ ሲሉ "ሃይማኖት ይመለስ፣ ፋሲል ይንገሥ" ብለው የቤተ ክርስቲያን ሰላም መልሰው ንስሓ ገብተው ሞቱ፡፡ አቡነ አብራኒዮስም ይህ የቤተ ክክርስቲያን የመከራ ዘመን ሲያልፍና ሃይማኖት ሲመለስ ተወለዱ፡፡ ገና በ5 ዓመታቸው ከጥንቆላ መጻሕፍት በቀር ሁሉንም የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትንና ምሥጢራትን ሁሉ ተምረው ዐወቁ፡፡ በ12 ዓመታቸው መነኰሱ፡፡ ዲቁና ሲሾሙም ጳጳሱ "ገና ሕፃን ነው፣ አሁን አልሾመውም" ሲሉ የሰማይ መላእክት "ይባዋል" ብለው መስክረውላቸዋል፡፡

በልጅነታቸውም መነኰሳቱ ወደ ጫካ ሔደው ዕንጨት እንዲሰብሩ ሲያዟቸው ጌታችን ግን ለአቡነ አብራኒዮስ ኃይል ሰጥቷቸው በነፋስ ሠረገላ እየሔዱ የ6 ሰዓቱን የእግር መንገድ እሳቸው ግን ዕንጨቱን ሰብረው በቶሎ ይመለሱ ነበር፡፡ ይህም ሲታወቅባቸው ውዳሴ ከንቱን ንቀው ከዚያ ገዳም ወጥተው ወደ አቡነ ተጠምቀ መድኅን ዘንድ ሔዱ፡፡ በዚያም በታላቅ ተጋድሎ ከኖሩ በኋላ አቡነ ተጠምቀ መድኅን "በአንተ ምክንያት ብዙ ነፍሳት ይድናሉ፣ ክፍልህ በዚያ ነው" ብለው አሁን ገዳማቸውን ወደገደሙበት ቦታ (ኤርትራ) ላኳቸው፤ ሲመጡም ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል እየመሯቸው እንደመጡ ገድላቸው ይናገራል፡፡ ጻድቁ ወደዚህ ገዳም ሲመጡ በፊት ይቀመጡባት የነበረችው ትልቅ ድንጋይ በተኣምር ከመሬት 7 ክንድ ከፍ ብላ አብራቸው መጥታለች፡፡ ድንጋይዋ ዛሬም ድረስ በገዳማቸው በክብር ስለተቀመጠች ምእመናን እየዳሰሷት ይባረኩባታል፣ መካኖች ይወልዱባታል፣ ሕሙማን ይፈወሱባታል፡፡

አቡነ አብራኒዮስ በቅዳሴ ጊዜ ጌታችንን በዕለተ ዐርብ እንደተሰቀለ ሆኖ ይመለከቱት ስለነበር በኀዘን በተመስጦ ሆነው ይቆዩም ስለነበር ሕዝቡም "በቅዳሴ ሰዓት ይተኛል" እያሉ ያሟቸው ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ ጻድቁ ወደ አካለ ጉዛይ በመሔድ በዘንዶ ላይ አድሮ ይመለክ የነበረውን ሰይጣን በጸሎታቸው አጥፍተው ዘንዶውን ገድለው ሕዝቡንም አስተምረው በንስሓ መልሰው አጥምቀዋቸዋል፡፡ ወደ ታላቁ ገዳም ደብረ ቢዘንም ሲሔዱ 6400 አጋንንትን አግኝተው በጸሎታቸው አጥፍተዋቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አቡነ አብራኒዮስ "ሰዳዴ አጋንንት-አጋንንት አባራሪ" ተብለዋል፡፡

አቡነ አብራኒዮስ ወደ ሌላ ቦታ ሔደው ሰለዳዋ የምትባል ቦታ ላይ ሆነው ሳለ አንድ ሰው ወደ ገዳማቸው ገብቶ አንዲትን ዛፍ ሲቆርጥ በመንፈስ ቅዱስ መነጽርነት አዩት፡፡ ቆራጩም ሰው "ተው አትቁረጥ" የሚል የአባታችንን ድምፅ ሰማ፣ በአካል የሉም ብሎ እምቢ አለ፣ ነገር ግን በመቅሠፍት ተመቶ ወዲያው ሞተ፡፡ በአንድ ዕለትም ልጃገረዶች እየዘፈኑ ሲሔዱ ብዙ አጋንንት በዘፈናቸው ተደስተው አብረዋቸው ሲጨፍሩ አባታችን በመንፈስ ተመልክተው ለልጃገረዶቹ ዘፈን የአጋንንት መሆኑን እንዳስተማሯቸው ገድላቸው ይናገራል፡፡

ለአቡነ አብራኒዮስ ለዕፍታቸው ሲደርስ ክብርት እመቤታችን ተገልጻ "ቤተ ክርስቲያን በስሜ አንጽልኝ" አለቻቸው፡፡ እርሳቸውም ውብ አድርገው በእመቤታችን ስም አነጹ ነገር ግን ፍጻሜውን ሳያዩ በዕለተ ቀኗ ነሐሴ 21 ቀን ዐረፉ፡፡ በዕረፍታቸውም ወቅት ጌታችን ተገልጦ ታላቅ ቃልኪዳን ሲሰጣቸው "...ዋስ እፈልጋለሁ፣ ዋስ ስጠኝ" አሉት፡፡ ጌታችንም "ሐዋርያት፣ ሰማዕታት፣ ከአንተ በፊት የነበሩ ጻድቃን ያልጠየቁኝን አንተ እንዴት ጠየከኝ?" አላቸው፡፡ እርሳቸውም "አምላኬ ሆይ! አንተ መሐሪና በጽድቅ ፈራጅ ቃልህም የማይለወጥ እንደሆንክ አውቃለሁ" አሉት፡፡ ጌታችም ፍግግ ብሎ "ይሁን የምትሻውን አላሳጣህም" በማለት ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን በላይ የሆነች ክብርት እመቤታችንንና ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስን ዋስ አድርጎ ቃል ኪዳን ከገባላቸው በኋላ ነሐሴ 21 ቀን 1713 ዓ.ም በሰላም ዐረፉ። ከታላቁ ጻድቅ ከአባታች አቡነ አብራኒዮስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን፣ በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦ ከገድላት አንደበት።

በየቀኑ ይህን ቴሌግራም ላይ ማግት ከፈለጉ ከታች ያለውን ሊኩን ይጫኑት።

@sigewe

https://t.me/joinchat/AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA