Get Mystery Box with random crypto!

'በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን'። ነሐሴ ፳፩ ( | ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ)

"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

ነሐሴ ፳፩ (21) ቀን።

እንኳን ለኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ታቦተ ጽዮንን ወደ አገራችን ላመጣ ለንጉሥ ምኒልክ ቀዳማዊ እናት ለንግስት ማክዳ ወይም ለንግስተ ሳባ (አዜብ) ለልደት በዓል፣ ለንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ለንግሥት እሌኒ የልደት በሰላም አደረሰን።

+ + +
"ሰላም ለእሌኒ ንግሥት ዘከሠተት መስቀለ በጎልጎታ ለክርስቲያን ዘይከውን ወልታ፤ እምኀበ ወጽአ ጢስ በሃይማኖታ፤ ወዓዲ ረከበት ቅንዋተ መስቀሉ ለክርስቶስ፣ ወአግበረት ልጓመ ፈረስ በከመ ይቤ ዘካርያስ"። ትርጉም፦ ጢስ በሃይማኖቷ ከወጣ ዘንድ ለክርስቲያን ጋሻ የሚኾን መስቀልን በጎልጎታ ያወጣች ለኾነች ለንግሥት እሌኒ ሰላምታ ይገባል፤ ዳግመኛም የክርስቶስን የመስቀሉን ችንካሮች አገኘች፤ ዘካርያስ እንደተናገረው ለፈረስ ልጓም አሠራች። ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በተአምኆ ቅዱሳን ላይ።

+ + +
ንግሥት ቅድስት ዕሌኒ፦ ይቺም ቅድስት በፊት የአንድ ነጋዴ ሰው ሚስት ነበረች እርሱም በነገረ ሠሪ ንጽሕት ሁና ሳለች ወደ ባሕር ጣላት። የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ፈቃድም ሮሐ ከሚባል አገር ደርሳ የበራጥያ ንጉሥ ቊንስጣ አገኛት። ውበቷንና ደምግባቷንም አይቶ አገባት። ለክርስቲያን ነገሥታት መጀመርያቸው የሆነውን ቈስጠንጢኖስን ወለደችው ምግባርንና ሃይማኖትን በማስተማር በመልካም አሳደገችው።

ልጇም በነገሠ ጊዜ "ወደ ኢየሩሳሌም ሔደሽ የክብር ባለቤት የሆነ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ግለጪ የከበሩ ቦታዎችንም ሥሪ" የሚላትን በሕልሟ አይታ እንዴት እንዳየች ይህን ለልጇ ነገረችው እርሱም ከብዙ ሠራዊቱ ጋራ ሰደዳት። በደረሰችም ጊዜ የክብር ባለቤት ስለሆነ ስለ ጌታችን መስቀል መረመች አዳኝ የሆነ መስቀሉንም ሁለት ወንበዴዎች ከተሰቀሉባቸው መስቀሎች ጋራ አገኘችው። የክብር ባለቤት የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል የትኛው እንደሆነ ታውቅ ዘንድ በወደደች ጊዜ ከራሱ በላይ "ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ ነው" የሚል በእንጨት የተቀረጸበት ጽሑፍ ያለው እንደሆነ የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ ቅዱስ መቃርስ ነገራት።

ከዚህም በኋላ ከእርሱ ምልክት ታይ ዘንድ ፈለገች የሞተ ሰውም አግኝታ መስቀሎችን በበድኑ ላይ አኖረች አልተነሣም። ከዚህ በኋላ ሦስተኛውን መስቀል በላዩ አኖረች። ያን ጊዜ ያ ምውት ተነሣ ሃይማኖቷም ጸና ደስታዋም በዛ።

ከዚህ በኋላ ዜናቸው በመስከረም ወር በዐሥራ ሰባት የተጻፈ በከበሩ ቦታዎች ውስጥ አብያተ ክርስቲያናትን ትሠራ ዘንድ ጀመረች። ለአባ መቃርስም በከበሩ ቦታዎች ሁሉ አብያተ ክርስቲያናትን እንዲሠራ ብዙ ገንዘብ ሰጠችው።

ከዚህ በኋላ ወደ ልጇ ተመልሳ የሆነውን ሁሉ ነገረችው የከበረ መስቀል በመገኘቱ እጅግ ደስ አለው። ይቺም ቅድስት በጎ ገድላሏን ከፈጸመችና እግዚአብሔርንም ከአገለገለች በኋላ ስለ ካህናትም ልብስና ቀለብ ለአብያተ ክርስቲያናትና ለገዳማት ብዙ ጉልቶችና ርስቶችን ለድኆችና ለምስኪኖችም እንዲሁ ከሠራችና ከተከለች በኋላ ግንቦት9 ቀን በሰላም ዐረፈች መላ ዕድሜዋም ሰማንያ ሆነ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት ዕለኔ በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ የግንቦት9 ስንክሳር።

+ + +
ንግሥተ ሳባ፦ ይህቺ ኢትዮዽያዊት ንግሥት ከ3 ሺ ዘመናት በፊት የነበረች ደግ እናት ናት። በሥጋዊ ደረጃ ከታንዛንያ እስከ የመን ያስተዳደረች ስመ ጥር ንግሥት ስትሆን በመንፈሳዊው ደረጃ ደግሞ እግዚአብሔር የቀባውን ሰው ፍለጋ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዛለች።

ከዚያውም አምልኮተ እግዚአብሔርን ከሥርዓተ ኦሪት ጋር አምጥታለች። ድንግልናዋን ለታላቁ ንጉሥ ሰሎሞን ሰጥታ ቀዳማዊ ምኒልክን ወልዳለች።

ይህቺ ንግሥት በጌታችን (በፈጣሪ) አንደበትም ተመስግናለች። (ማቴ. 12፥42) በስምም ሳባ፣ አዜብና ማክዳ ተብላ ትታወቃለች። ዛሬ ዕለተ ልደቷ ነው። ምንጭ፦ ከዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ።

በየቀኑ ይህን ቴሌግራም ላይ ማግት ከፈለጉ ከታች ያለውን ሊኩን ይጫኑት።

@sigewe

https://t.me/joinchat/AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA