Get Mystery Box with random crypto!

የነርቭ ህመም የነርቭ ህመም፣  በአንድ የህመም ምልክት ብቻ የሚገለፅ ህመም አይደለም፣ እ | Dr. Seife | ዶ/ር ሰይፈ

የነርቭ ህመም

የነርቭ ህመም፣  በአንድ የህመም ምልክት ብቻ የሚገለፅ ህመም አይደለም፣ እንደ ቦታው እና እነደ ነርቭ ጉዳቱ ደረጃ፣ በተለያየ አይነት የህመም ምልክቶች ይገለፃል።

መቆጥቆጥ፣ ማቃጠል፣ መለብለብ ፣መደንዘዝ ፣መዛል ፣ እና ከአቅም ማጣት ጀምሮ እስከ ራስ መሳት ድረስ ሁሉ ያሉ የህመም ምልክቶች ፣በነርቭ ህመም ተጠቂዎች ሊገለፁ ይችላሉ።

ነርቭ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰ፣ አንዳንዴ፣ በህክምና እንኳን መመለስ ስለማይቻል ፣ ብዙ ሰዎችን ዘላቂ ለሆነ የአካል ጉዳት ይዳርጋል።

ጉዳቱ አነስተኛ ከሆነ ደሞ፣ እንደ ተጎዳው ነርቭ  እና፣ ጉዳቱን እንዳስከተለው በሽታ፣ በህክምና ፣ ወደነበረበት መመለስም ይቻላል።

አንድ ሰው ላይ፣ ባጋጣሚ ከሚደርስ አደጋ አንስቶ በቂ ክትትል በሌላቸው ስር ሰደድ በሽታዎችም ጭምር የነርቭ ህመም ሊጀምር ይችላል።

አንድ ጤናማ ሰው ላይ ያለ የነርቭ አካል አፈጣጠር በአቀማመጡ በሁለት ይከፈላል፣  ማእከላዊ የነርቭ አካል እና ውጫዊ የነርቭ አካል።

ማእከላዊ የነርቭ አካል ማለት፣ አይምሮ እና ሀብለ ሰረሰር ናቸው። ውጫዊ የነርቭ አካሎች ደሞ፣ ከአይምሮ እና ከ ሀብለ ሰረሰር የሚነሱ የነርቭ መስመሮች ናቸው።

አይምሮ ውስጥ ያሉ የነርቭ ህዋሶች በከፍተኛ ደረጃ ሲጎዱ ራሳቸውን መልሶ የማደስ ብቃታቸው አነስተኛ ስለሆነ አይምሮ ላይ የሚደርስ ጠንከር ያለ የነርቭ ጉዳት ሲኖር ዘላቂ ለሆነ ወይም በህክምና ለማይመለስ የአካል ጉዳት ሊዳርግ ይችላል።

ከአይምሮ እና ከሀብለሰረሰር ውጪ ያሉ የነርቭ መስመሮች ደሞ፣ እንደ ጉዳት ደረጃቸው ራሳቸውን የማደስ የተወሰነ አቅም አላቸው።

አብዛኛውን ግዜ፣ ቀለል ያለ እና መካከለኛ የጉዳት ደረጃ የደረሰባቸው ከሆነ በግዜ ሂደት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የሚያገግሙ ይሆናሉ።

ነገር ግን፣ አንዳንዴ እነዚህ የነርቭ መስመሮች ላይ የሚደርሰው አደጋ ከፍተኛ ከሆነ፣ ጉዳቱ የነርቭ መስመሮቹ ራሳቸውን ከሚያድሱበት አቅም በላይ ስለሚሆን ዘላቂ ለሆነ የአካል ጉዳት ሊዳርጉ ይችላሉ።

የነርቭ ህመም በተለያዩ አደጋዎች እና የውስጥ ደዌ በሽታዎች ምክኒያት ሊከሰት ይችላል፣ የነርቭ ህመሙ በአደጋ ምክኒያት ሲጎዳ፣ ነርቩ ሊጨፈለቅ፣ በከፍፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ሊቆረጥ ይችላል።

ስርሰደድ በሽታዎችን ተከትለው የሚመጡ የነርቭ ህመሞች፣ ለምሳሌ፣ የስኳር በሽታን ተከትሎ የሚመጣ የነርቭ ህመም፣ ከእይታ ድክመት ጀምሮ እንደ ደረጃው በብዙ መንገድ ሊገለፅ ይችላል፣

ነገር ግን አብዛኛውን ግዜ ፣ ከጉልበት በታች በሁለቱም እግር ላይ የሚሰማ የመለብለብ እና የማቃጠል ስሜት በተለይ ከመሀል እግር ጀምሮ ወደላይ ከፍ እያለ የሚሄድ የህመም አይነት ይሰማቸዋል።

ከዚህ ውጪ ፣ ለምሳሌ፣ በአልኮል ጥገኝነት፣ በቫይታሚን ቢ እጥረት፣ በመመረዝ፣ በታይሮይድ ህመም እና በተለያዩ ኢንፌክሽኖችም ጭምር የሚመጡ ሌሎች አሳሳቢ የሆኑ የነርቭ ህመም አይነቶችም አሉ።

የነርቭ ህመምን በተመለከተ፣ ሰፋ ያለ መረጃ በ YouTube ቻናሌ ላይ አስቀምጫለሁ፣ የሚቀጥለውን ማስፈንጠሪያ ተጭናችሁ መመልከት ትችላላችሁ። መልካም ግዜ!!