Get Mystery Box with random crypto!

#የቅዳሜ_ውዳሴ_ማርያም_ትርጓሜ ከተለዩ የተለየሽ፣ ከከበሩ የከበርሽ በውስጧም ሕግ የተጻፈበት ኪ | ቤተ ቅዱስ ሚካኤል

#የቅዳሜ_ውዳሴ_ማርያም_ትርጓሜ

ከተለዩ የተለየሽ፣ ከከበሩ የከበርሽ በውስጧም ሕግ የተጻፈበት ኪዳን ያለብሽ የተሠወረ መና ያለበት መሶበ ወርቅ ያለብሽ ደብተራ (ድንኳን) አንቺ ነሽ /ዘጸ.፳፮፡፩-፴/፡፡ ይኸውም መና የተባለው ሰው ኾኖ በማኅፀንሽ ያደረው ወልደ እግዚአብሔር ነው፡፡ መተርጕማኑ ይህን የበለጠ ሲያብራሩት፡- “ድንኳኗ የእመቤታችን ምሳሌ፤ ቅድስት የነፍሷ፤ ቅዱሳን የሥጋዋ፤ ታቦቱ የመንፈስ ቅዱስ፤ ጽላት የልቡናዋ፤ ቃሉ በመንፈስ ቅዱስ የተገለጸላት ምሥጢር ምሳሌ ነው፡፡ አንድም ቅዱሳን የሥጋዋና የነፍሷ፤ ቅድስት የልቡናዋ፤ ታቦት የማኅፀኗ፤ ጽላት የትስብእት፤ ቃሉም የመለኮት ምሳሌ ነው” ይላሉ /ውዳሴ ማርያም ንባቡና ትርጓሜው፣ ገጽ ፻፸፬/፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በአርጋኖን ዘሐሙስ ላይ፡- “ተፈሥሒ ኦ ደብተራ ብርሃን ማኅደሩ ለዐቢይ ሊቀ ካህናት - የታላቁ ሊቀ ካህናት ማደርያ የብርሃን ድንኳን ሆይ! ደስ ይበልሽ” በማለት የሊቀ ካህናት የባሕርይ አምላክ የክርስቶስ እናት አማናዊት ድንኳን መኾኗን አስተምሯል፡፡
አካላዊ ቃል ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኾነ፡፡ የክብር ባለቤት እርሱን በዚህ ዓለም ወለደችው፡፡ ለዘለዓለሙ ጸንቶ የሚኖር አካላዊ ቃል ሰው ኾኖ ከኃጢአታችን ፍዳ አድኖናልና ሰው ኾኖ ያዳነን የነባቢ በግዕ (የሚናገር በግ የክርስቶስ) እናቱ ደስ ይላታል /ዮሐ.፩፡፳፱/፡፡ ለዘለዓለሙ ጸንቶ የሚኖር አካላዊ ቃል ሰው ኾኖ ከኃጢአታችን ፍዳ ካዳነን ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

እርሱን ከወለድሽ በኋላ ማኅተመ ድንግልናሽ ሳይለወጥ ኑረሻልና የክርስቶስ እናቱ ተባልሽ፡፡ ድንቅ በሚያሰኝ ተዋሕዶ አማኑኤልን ወልደሸዋልና ባለመለወጥ አጸናሽ፡፡ ታላቁ የቤተ ክርስቲያን መምህር ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ለማንም ሴት ያልተሰጠ ለድንግል ማርያም ብቻ የተሰጠ ድንግልና ከእናትነት ጋር አስተባብራ ስለ መገኘቷ ሲገልጥ “ወሰቦሂ ወለደቶ ዐቀበ ድንግልና፣ ዘእንበለ ርኩስ ከመ በፀንሳ መንክር ትኩን መራሂተ ለሃይማኖት ዐባይ - ከድንግል ተወለደ፤ በወለደችውም ጊዜ ድንግልናዋ ያለመለወጥ አጸና፡፡ ድንቅ የሚኾን ፅንሷ ለደገኛው ሃይማኖት መሪ ትኾን ዘንድ” በማለት ቅድስት ድንግል ማርያም አምላክን ስትወልድው ማኅተመ ድንግልናዋ እንዳልተለወጠ ጌታም ሰው ሲኾን ባሕርየ መለኮቱ ላለመለወጡ፣ እርሷ ድንግል ወእም (ድንግልም እናትም) ስትባል እንደምትኖር አካላዊ ቃል ክርስቶስም አምላክ ወሰብእ (ሰው የኾነ አምላክ) ሲባል የሚኖር የመኾኑን የተዋሕዶ ልዩ ምሥጢርን ያወቅንባት የተረዳንባት እርሷ ብቻ መኾኗን አስተምሯል /ሃይ.አበ.፷፮፡፴፪/፡፡ እንዲህ ካለ ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

ከምድር እስከ ሰማይ ደርሳ፣ በላይዋ ዙፋን ተነጽፎባት፣ በዚያ ላይ ንጉሥ ተቀምጦባት፣ መላእክት ሲወጡባት ሲወርዱባት ያዕቆብ በፍኖት ሎዛ ያያት የወርቅ መሰላል አንቺ ነሽ /ዘፍ.፳፰፡፲-፳፪/፡፡ ሰው ከመኾኑ አስቀድሞ ሰውም ከኾነ በኋላ የማይመረመር እርሱን በተፈትሖ በማይታወቅ በማኅፀንሽ ችለሸዋልና እኛን ስለማዳን ከአንቺ ሰው ከኾነ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሰዋስው (አማላጅ) ኾንሽን፡፡ እኛን ስለማዳን ከአንቺ ሰው ከኾነ ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

ጽርሐ ንጽሕት ሆይ! እነሆ ጌታ የፈጠረውን ዓለም ኹሉ በቸርነቱ ብዛት ያድን ዘንድ ከአንቺ ተወለደ፡፡ ቸር ሰው ወዳጅ ነውና በአፍአ በውስጥ እናመስግነው፡፡ ቸር ሰው ወዳጅ ከኾነ ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡