Get Mystery Box with random crypto!

+ ዝም ብለን የምንጠላው ሰው + ከሩቅ የምናውቀው አንዳንድ ሰው የለም? ብዙም አናውቀውም:: ቀ | ቤተ ቅዱስ ሚካኤል

+ ዝም ብለን የምንጠላው ሰው +

ከሩቅ የምናውቀው አንዳንድ ሰው የለም? ብዙም አናውቀውም:: ቀርበን አውርተነው አናውቅም:: ስናየው ግን እንዲሁ ደስ የማይለንና ያለ ምክንያት የምንጠላው ሰው የለም?

"እሱን ሰውዬ ጥሎብኝ አልወደውም"

"አይ እሱን ልጅ ቀልቤ ትከሻዬ አልወደደውም"

"እኔ እንጃ ለምን እንደሆነ ባላውቅም አልወዳትም:: ምክንያቴን አትጠይቀኝ ግን በቃ እንዲሁ አልወዳትም"

ምንም ምክንያት ሳይኖረን እንዲሁ የምንጠላው ሰው አለ::

እግዚአብሔር ግን
"አንድያ ልጁን እስኪሠጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአል" (ዮሐ 3:16)

ጠላቶቹ ሳለን በልጁ ሞት አዳነን እንደሚል እርሱ እኛን ለመጥላት ብዙ ምክንያት ነበረው:: እርሱ ግን እንዲሁ ወደደን:: ከእኛ ምንም ባያገኝም ስለ እኛ ያለው ፍቅር የእንዲሁ ፍቅር (unconditional love) ነበረ:: እርሱ እንዲሁ ወዶናል እኛ ግን እንዲሁ ሰው እንጠላለን::
ያለ ምክንያት መውደድ ቢያቅተን እንኳን ያለ ምክንያት መጥላታችን (unconditional hate) ቢቀር ምናለ?
የሚያሳዝነው ያለ ምክንያት የጠላናቸውን ሰዎች የበለጠ ለመጥላት በልባችን እስር ቤት ውስጥ በጥላቻ ሰንሰለት እናስራቸውና የበለጠ ለመጥላት ስለእነርሱ ክፉ ክፉ ማስረጃ ለመስማት እንተጋለን:: ጥሩ ነገራቸውን ለመስማት አንፈልግም:: ክፉ ስንሰማ ግን "እኮ እኔ እኮ ዝም ብሎ ትከሻዬ ይነግረኝ ነበር" ብለን በደስታ እንፈነድቃለን:: እንዲሁ የጠላነውን ሰው በምክንያት ለመጥላት በመቻላችን ደስ ይለናል::

እኛ ሰውን ለመጥላት ምክንያት የምንፈልገውን ያህል እንዲሁ የወደደን እግዚአብሔር ግን እኛን ለመማር ሰበብ ይፈልጋል:: ትንሽ በጎነት ቅንጣት ቅንነት ሲያገኝ እጅግ ይደሰታል:: ባለቅኔው "እግዚአብሔር መንግሥቱን በርካሽ ዋጋ ሸጠው:: በቀዝቃዛ ውኃ በዘለላ ዕንባ እና ማረኝ በሚል የወንበዴ ጩኸት!" እንዳሉት እሱ እኛን ይቅር ለማለት የሚታይ በጎነት ቢያጣ ልባችን ውስጥ ገብቶ ትንሽ መጸጸት ካለ ይፈልጋል:: እንዲሁ ወዶናልና እንዲሁ ሊተወን አይፈልግም::

"እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለሆነ
ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳን በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወትን ሠጠን"
ኤፌ 2:4

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ታኅሣሥ 30 2013 ዓ ም
ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ! በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)

https://youtube.com/channel/UCqIww_vrxOATvuc5K_EDf1A?sub_confirmation=1

https://t.me/saint_mikael