Get Mystery Box with random crypto!

ጥናታዊ ጽሁፍ/research ማዘጋጀት ትፈልጋለህ? እነዚህን 15 ነጥቦች ልብ በል። የጥናት/ሪሰርች | Research-ሪሰርች(ጁፒተር-Jupiter)

ጥናታዊ ጽሁፍ/research ማዘጋጀት ትፈልጋለህ? እነዚህን 15 ነጥቦች ልብ በል።
የጥናት/ሪሰርች ይዘት፣ ስፋትና ጥልቀት ሊለያይ ይችላል፡፡ ተጨባጭ ችግርን ለመፍታት ይሁን የተደበቀ ምስጢርን ፈልፍለን ለማግኘት ወይንም ከዚሁ ለተለየ ዓላማ ጥናት ሊታቀድና ሊከናወን ይችላል፡፡
በዚሁ መሰረት አንድ ጥናት/ሪሰርች ሲዘጋጅ ከዚህ በታች የተመለከቱትን ብዙዎች ዘንድ የተለመዱ ዋና ዋና ይዘቶችን ሊያካትት ይችላል፡፡ ዝርዝሩን ተመልከቱት፤

የጥናቱ ርዕስ/ Topic
የጥናት ርዕስ ቃላት ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ ትክክለኛ ስዋሰው፣ ገላጭ ቃላት፣ የጥናቱን ችግር፣ ሥፍራ/ቦታ በተቻለ መጠን በሚስብ ሁኔታ ቢጻፍ ይመረጣል፡፡ ርዕሱን የሚያነብ ሰው የጥናቱን ይዘት በቀላሉ እንዲረዳ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በዚሁ በፊት ገጽ ላይ ከርዕስ በተጨማሪ፣ የአጥኚው/ዎቹ ሙሉ ሥም፣ ጥናቱ የሚቀርብለት ሠው/ተቋም፣ጥናቱ የተዘጋጀበት ወቅትና ሥፍራ ይጠቀሳሉ፡፡

ምስጋና/ Acknowledgement
የምሥጋና መልዕክት ግልጽ ነው፡፡ ጥናቱ ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ በተለያዩ መልኩ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሠዎች የሚመሰገኑበት ክፍል ነው፡፡ ሠው ብቻ ላይመሰገንበትም ይችላል፡፤ ሥፍራዎች፣ ሁኔታዎች፣ ወቅቶችና ሌሎች ጉዳዮች በዚህ ክፍል ሊመሰገኑ ይችላሉ፡፡

ማውጫ/Table of content
በማውጫ የጥናቱ የተለያዩ አቢይና ንዑስ ክፍሎች የሚገለጽበት ገጽ ይጠቀሳል፡፡

መግቢያ/ Introduction
በዚህ ክፍል የጥናቱን መነሻ ለአንባቢዎች መረጃ የሚሰጥበት ነው፡፡ መግቢያ መንዛዛት የለበትም፡፡ አንድ ገጽ ይበቃል፡፡ ዞሮ ዞሮ የአንድ ጥናት መግቢያ የአንባቢውን ስሜት የሚቀሰቅስ፣ የጥናቱን ወሰንና አቅጣጫ የሚያመላክት፣ጥናቱን እንዴት እንደሚሰራና የጥናቱን ጭብጥ የሚያሳይ ይዘት እንዲኖረው ተደርጎ ይዘጋጃል፡፡

የጥናቱ ዓላማ /Objective
የጥናት ዓላማ ከተለያዩ ርዕሶች ጋር ጥልቅ ቁርኝት አለው፡፡ የጥናት ዓላማ፣ ከጥናቱ ችግሮች፣መላ ምቶች መረጃና ውጤት አቀራረብና አተናተን፣ ማጠቃለያና መደምደሚያ ጋር ይተሳሰራል፡፡ የጥናት ርዕሰ ከተመረጠ በኋላ፤ በጉዳዩ ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በሚገባ ከተረዳን በኋላ የጥናት ዓላማዎች ይዘጋጃሉ፡፡
የጥናት ዓላማዎች አቢይና ዝርዝር ተብለው ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ ዓላማዎች በጥናቱ የተጠቀሱ ቁልፍ ችግሮችን ወይንም መላምትን መሰረት ተደርገው ይቀረጻሉ፡፡

Statement of the problem ፦ ይኸኛው ዋና መሠረት ነው። ትክክለኛ ገለጻም ይጠይቃል። “የጥናቱ ርዕስ ለመስራት ያነሳሳህ/ሽ ምን ችግር ኖሮ ነው[what is the problem that initiate you to apply your research over this title?.....]” ለሚል ጥያቄ ተገቢ መልስ የምትሰጡበት የጥናት ሰነድ ክፍል ነው። ለጥናት የተሰማራችሁበትን ችግር ወይም የአንድ ነገር እጥረት ለማስቀመጥ ሞክሩ። ገለጻችሁም "There is lack of/a problem of/ ____" የሚል አይነት ቢሆን መልካም ነው።

የጥናቱ አስፈላጊነት/ Significance of the study
ጥናት ለተለያየ አገልግሎት ይውላል፡፡ በዚህ ክፍል የዚህን ጥናት ውጤት አስፈላጊነት ግልጽ በሆነ መልኩ በዝርዝር ይቀመጣል፡፡
የጥናቱን ወሰን/ Scope of the study
በዚህ ንዑስ ክፍል የጥናቱ አጠቃላይ ስፋት፣ ርዝመትና ጥልቀት ይገለጻል፡፡ ለምሌ ያህል፣ ጥናቱ የት እንደሚሰራ፣ በእነማን ላይ እንደሚሰራ፣ ጊዜና የመሳሰሉ ወሰኖች በግልጽ ይቀመጣሉ፡፡ ወሰን ያልተበጀለት ጥናት መጀመሪያውንና መጨረሻውን ማወቅ ይቸግራል፡፡

የጥናቱ ታሳቢ ክፍተቶች/ Limitation
አንድ ጥናት ሲካሄድ ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ ሊሆን አይችልም፡፡ የተለያዩ ክፍተቶች ሊፈጠሩ ይችላሉና በዚህ ክፍል በጥናቱ ወቅት ሊገጥሙን የሚችሉ ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ችግሮች ከአጥኚው አቅም በላይ ሊሆኑ ይገባል እንጂ ሁሉንም ችግር መጥቀስ አይገባም፡፡ ታዲያ በዚህ ክፍል ክፍተቶቹን ለማጥበብ በአጥኚው ሊደረጉ የሚገቡ ጥረቶችም ሊካተቱ ይገባል እንጂ ክፍተቶችን ብቻ ጠቅሶ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ አይገባም፡፡

የጥናቱ ዘዴና አካሄድ/ Methodology of the study
የአንድ ጥናት ዘዴና አካሄድ/ Methodology እንደየ ጥናቱ ጠባይ፣ችግር፣አይነትና ዓላማ የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ ዘዴና አካሄድ መጥቀስ ማለት በአጭሩ ጥናቱ እንዴት እንደሚሰራ፣ የት እንደሚሰራ፣ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴ ፣ የመረጃውም መሰብሰቢያ ዘዴ እንዴት አንደተዘጋጀ፤ ምን አይነት ጥናት እንደሆነ፣ የናሙና ይዘት፣ አመራረጥና መጠን (ናሙና ያለው እንደሆነ) ፣ ውጤቱ እንዴት እንደሚተነተን፣ውጤቱ እንዴት እንደሚሰራጭና የመሳሰሉ የጥናቱን አጠቃላይ አሰራርና አካሄድ መግለጽ ማለት ነው፡፡

የተዛማጅ ፅሁፍ ምልከታ/ Literature Review
በዚህ ክፍል ከዚህ በፊት የተደረጉ ጥናቶችንና ስምምነቶችን የተቀመጡ ንድፈ-ሃሳቦችን በጥልቀት ይመረመራሉ፡፡ ተዛማጅ ጽሁፍ በጥናት ውስጥ በተለያየ መልኩ ማካተት የሚስችል የጥና ጽሁፍ ምልከታ አጻጻፍ አለ፤ ከዚህ ውስጥ የሚስማማንን መርጠን መጠቀም የእኛ ምርጫ ነው፡፡ የተዛማጅ ፅሁፍ ምልከታ ሥራ ሰፊና ጥልቅ ነውና በዚህች አጭር ንዑስ ርዕስ ሁሉን መግለጽ ይከብዳል፡፡

የጥናት ግኝት አቀራረብ ትንተና/ Data analysis & Interpretation
የአንድ ጥናት ውጤት እንደ ጥናቱ አይነትና የመረጃ ማጠናቀሪያ ሥልት ሁኔታ፣ በተለያየ መልክ ሊቀርብና ሊተነተን ይችላል፡፡ አንድን ጥናት ጥናት የሚያሰኘው አጥኚው የሳይንስና የሎጂክን ስልት በመከተል በግኝቶቹ ላይ የሚደረገው ትንታኔና ትርጉም እንጂ ጥሩ የሆኑ መረጃ ማቅረብ ብቻ ሊሆን አይችልም፡፡
በመሆኑም በግኝት አቀራረብና አተናተን ወቅት አስተያየትን ከተጨባጭ ሁኔታ መለየት፤የጥናቱን ወሰን ማስታወስ እንዲሁም የተሳሳተ ትንታኔና ትርጉም ላለመስጠት ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ማጠቃለያ/ Conclusion
ጥናቶች የተለያየ ስፋትና ጥልቀት አላቸው፡፡ ታዲያ ይህ ክፍል ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ያሉ የወቅቱን ሁኔታና ግኝቶች በማጠቃለል አጠር ተደርጎ የሚቀርበት ነው፡፡

የመፍትሔ ሐሳብ/ Recommendation
በጥናቱ የተለዩ ችግሮችና መንስዔዎቻቸው ከታወቁ በኋላ የመፍተሄ ሃሳቦች በዝርዝር ይቀመጣሉ፡፡ ስለዚህ የመፍተሄ ሃሳቦችን ከማቅረባችን በፊት ችግሮቹን በሚገባ መረዳት ይገባል፡፡
በዚህ ክፍል ሁሉም የመፍሔ ሀሳብ ሊገለጽ አይገባም፡፡ ተጨባጭ ሁኔታን በመረዳት ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉትን በመለየት በቅደም ተከተል ማቀመጥ ያስፈልጋል፡፡

አባሪ/ Appendices
በዚህ ክፍል ለጥናቱ የተገለገልንባቸውን ዝርዝር የመረጃ ማጠናቀሪያ ቅጾችና ሌሎች ዝርዝር ግብዓቶች ይቀመጣሉ፡፡
ጥናቱ ለማካሄድ የተጠቀምናቸውን መረጃዎች ማለትም መጠይይቆች፤ የተለያዮ ፕሮግራሞች እና ሌሎች ፎርማቶች ከጥናቱ ጋር ተያይዘው የሚቀርቡበት ነው፡፡

ማጣቀሻ /Reference
ይህ ክፍል ለጥናቱ የተጠቀምናቸው መረጃዎች የሚገለጽበት ነው፡፡ መረጃዎቹ በማን፣ መቼ፣የት እንደተጻፉ በግልጽ መቀመጥ አለባቸው፡፡ ስምምነት የተደረሰባቸው የተለያዩ ማጣቀሻ አጻጻፍ ስልቶች አስተምህሮዎች አሉና በተፈላጊው ስልት ማጣቀሻን በግልጽ በማስቀመጥ የጥናቱ እውነተኛነት በዚህ ክፍል ይረጋገጣል፡፡