2022-08-06 10:55:21
የድንጋይ ሾርባ
ሰው ሲደክመው እና ሲርበው ምን ይመስላል? ይህንን ለማወቅ ወደዚች መንደር በመግባት ላይ ያለውን
መንገደኛ ማየት ብቻ ይበቃል፡፡ ዓይኖቹ ከፊቱ ላይ ጠፍተው የት እንዳሉ አይታወቅም፡፡ አፍንጫ
እንዳለው ለማወቅ መዳሰስ የግድ ያስፈልጋል፡፡ መታወቂያ ቢኖረው ኖሮ አሁን የእርሱ ሊሆን አይችልም
ነበር፡፡ የገዛ ልብሱ ስለከበደው አውልቆ እየጎተተው ይጓዛል፡፡ ሁለት ነገሮች ብቻ በትከሻው አሉ፡፡
ካናቴራው እና በስልቻ የያዛት ድስት፡፡
ረሃብ ምን ያህል ጊዜ ይሰጣል? ነበር ያለው ጸጋ ገብረ መድኅን፡፡ ይህንን ሰው ቢያይ ደግሞ ውኃ ጥም
ምን ያህል ጊዜ ይሰጣል? የሚል ድንቅ ግጥም ይጽፍ ነበር፡፡ ያ በበላዔ ሰብእ ታሪክ ጥርኝ ውኃ ሲያገኝ
ውኃው በእጆቹ ንቃቃት ላይ የቀረውን ሰው ታስታውሱታላችሁ?
አይደርሱ የለም ደረሰ፡፡ መጀመርያ ከድካሙ ለመላቀቅ በመንደሩ መካከል ከበቀለ ዋርካ ሥር ጋደም
አለ፡፡ ከጎኑ የዱባ ዛፍ ቢኖር ኖሮ
አንደ የባላገር ሰው ከገበያ ውሎ
ሲመለስ ቢደክመው በፀሐይ ቃጠሎ
ካንድ የሾላ ዛፍ ሥር ሄዶ ተጠግቶ
እያሉ ከበደ ሚካኤል የጻፉለት የባላገር ሰው ዛሬም ከዋርካው ሥር አልተነሣም እንዴ ያሰኛችኋል፡፡
ሆድ ባዶ ከሆነ ዕንቅልፍም ባዶ ይሆናል መሰል፡፡ የድካሙን ያህል ሊተኛ አልቻለም፡፡ ተነሣ፡፡ ተነሣና
ወደ መንደርዋ ቤቶች ተጠጋ፡፡ የሚያሳዝን ፊቱን እያሳየ፣ የደከመ እጁን እያርገበገበ፣ በሰለለ ድምፁ ቁራሽ
ለመነ፡፡
የሚሰጠው ግን አላገኘም ነበር፡፡ ቤቶቹን ሁሉ አዳረሰና ተመልሶ ዋርካው ሥር ተጋደመ፡፡
ያለው ሁለት ነገር ብቻ ነው፡፡ ነፍስ እና ብረት ድስት፡፡
ከተሠወሩበት እንደ ገጠር መብራት ብልጭ ባሉት ዓይኖቹ አንዳች ነገር አዩ፡፡ የሚወርድ የምንጭ ውኃ፡፡
እየተጎተተ ሄዶ በብረት ድስቱ ቀድቶ መጣ፡፡ አንድ ያልደረሰበት የርሱ ቢጤ መንገደኛ አንዳች ነገር
ጥዶበት የነበረ ምድጃ አጠገቡ አለ፡፡ እንጨቶቹን ቆስቆስ አደረገና የብረት ድስቱን ውኃ ጣደው፡፡
እናም በሚፍለቀለቀው ውኃ መዝናናት ጀመረ፡፡ ምን ያድርግበት? አንዱን ድንጋይ አነሣና ብረት ድስቱ
ውስጥ ጨመረው፡፡ድንጋዩ፣ ውኃ እና ብረት ድስቱ እየተጋጩ በሚፈጥሩት ዜማ ረሃቡን ለመርሳት አሰበ፡፡
እርሱ ድስት ድስቱን አይቶ ድንገት ቀና ሲል አንድ ሰው የሚያደርገውን በአግራሞት እያየው ነበር፡፡
«ምን እየሠራህ ነው ጃል» አለው ሰውዬው፡፡
«የድንጋይ ሾርባ እየሠራሁ ነው» አለው መንገደኛው በማሾፍ፡፡
«የድንጋይ ሾርባ!» ሰውዬው ተገረመ፡፡
«አዎ ከድንጋይኮ ምርጥ ሾርባ ይሠራል፡፡ በተለይማ ድንች ቢገባበት ኖሮ» አለው መንደኛው፡፡
«ርግጠኛ ነህ»» ሰውዬው የሚሆነውን ለማወቅ ጓጉቷል፡፡
«መቶ በመቶ» መንገደኛው መለሰ፡፡
«ቆይ እኔ ድንች አመጣለሁ» አለና መንገደኛው ተጓዘ፡፡
የርሱ እግር እንደለቀቀ መንገደኛው ዓይኑን ጨፈነ፡፡ ምንም ያህል ሳይቆይ ግን «ጌታው» የሚል ድምፅ
ቀሰቀሰው፡፡
«እርስዎም እንግዳ ነዎት፤ የሚሠሩትም እንግዳ ነገር ነው» አለ የቆመው ሰው፡፡
«እንዴት ማለት» ጠየቀ መንገደኛው፡፡
«ድንጋይ ውኃ ውስጥ ጨምረው ምን ሊሠሩ ነው»
«ሾርባ ነዋ»
«የምን ሾርባ»
«የድንጋይ ሾርባ»
«የድንጋይ ሾርባ ደግሞ ከምን ከምን ነው የሚሠራው»
«ከድንጋይ፣ ከሥጋ፣ ከድንች፣ ከካሮት፣ ከጨው፣ ከሽንኩርት፣ ከዘይት እና ከሩዝ»
«አሁን የማየው ድንጋዩን ብቻኮ ነው»
«ሌላው ነገርማ የለኝም፤ ቢኖረኝ ኖሮ ያዩት ነበር»
«ይህንን እንግዳ ነገር ማወቅ እፈልጋለሁ፤ እኔ ካሮት እና ጨው ላመጣልዎት እችላለሁ» አለ ሰውዬው፡፡
«መልካም፣ እኔ ደግሞ አዲስ ሞያ ላሳይዎት እችላለሁ»
ሁለተኛው መንደርተኛ በጥድፊያ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡
የርሱን መጓዝ ተከትሎ ሌላም መንደርተኛ መጣ፡፡ ያም ዘይት፣ ሥጋ እና የማቅረቢያ ሰሐን ሊያመጣ
ተጓዘ፡፡ ሌላው ደግሞ ዳቦ ሊያመጣ መንደር ገባ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያሉ ሰባት ሰዎች ለሾርባ
የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሁሉ አመጡ፡፡
መንገደኛውም በሚያውቀው ሞያ እያዋሐደ ሾርባውን መሥራት ጀመረ፡፡ «አሁን ድንጋዩ አያስፈልግም»
አለና አወጣው፡፡
ሾርባው ሲደርስ በየሰሐኑ አቀረበላቸው፡፡ ማንኪያውንም ጨምረው ሊውጡት ነበር፡፡
ይህንን ያዩ ሌሎች መንደርተኞች የድንጋይ ሾርባ እንዲሠራላቸው ጠየቁት እርሱም ሠራ፡፡ ለሌሎች
መንደሮች ሁሉ ዜናው ተዳረሰ፡፡ እናም መንገዱን ትቶ ሾርባ እየሠራ ይሸጥ ጀመር፡፡
እዚህ መንደር ዋርካው ሥር ምግብ ቤት የከፈተው ሰውዬ እይውላችሁ እንዲህ አድርጎ ነው ምግብ ቤት
ከፍቶ ሀብታም የሆነው፡፡
ከብዙ ጊዜ በኋላ ጋዜጠኞች መጥተው ጠየቁት፡፡
«ድንጋዩ ለሾርባው ምኑ ነው?» አሉት፡፡
እርሱም «ምኑም አይደለም» አለና መለሰላቸው፡፡ ደነገጡ፡፡
«ታድያ ለምን ትጨምርበታለህ?»
«ታሪኩ ረዥም ነው» አለና በዚያች በተራበ ሰዓት ያደረገውን ነገራቸው፡፡
«እና ያኔም ድንጋዩ ምንም አልነበረም ማለት ነው?» አሉት፡፡
«አሁን ታሪኩን ትቼ የተማርኩትን ልንገራችሁ፡፡ እኔ መንገደኛ ሆኜ ወደዚች መንደር ስመጣ፡፡ ያጣሁ
የነጣሁ ድኻ የሆንኩ መስሎኝ ነበር፡፡ ምንም ነገር የሌለኝ መስሎኝ ነበር፡፡ ስሕተቴ ከዚህ ይጀምራል፡፡
ምንም ነገር የሌለው ሰው የለም፡፡ ያለውን የማያውቅ እና እንዴት መጠቀም እንዳለበት የማያውቅ ሰው
ግን ሞልቷል፡፡
«ችግሩ የሚጀመረው ከአቆጣጠራችን ነው፡፡ እኛ ቁጥር መቁጠር የምንጀምረው ከሌለን ነገር ነው፡፡ ተስፋ
የምንቆርጠውም ከሌለን ነገር ስለምንጀምር ነው፡፡ ወዳጄ ሁይ ካለህ ነገር ተነሣ፡፡ ምን አለህ? ጉልበት፣
ዕውቀት፣ ጤና፣ መልካም ትዳር፣ ጥሩ ልጆች፣ ደስተኛ ቤተሰብ፣ እምነት፣ ነገር የማቅለል ችሎታ፣ ጥበብ፣
ዕውቀት፣ ትምህርት፣ ልምድ፣ ገንዘብ፣ ጊዜ? ምን አለህ? ካለህ ነገር ጀምር፡፡ ተአምር የማይሠራበት ነገር
በዓለም ላይ የለም፡፡
«እኔ በዚያ ጊዜ ውኃ፣ ድስት እና ድንጋይ ነበረኝ፡፡ የድንጋይ ሾርባ ለመሥራት ባልነሣ ኖሮ ማን ዘወር
ብሎ ያየኝ ነበር፡፡ ድንቹ፣ ካሮቱ፣ ጨው፣ ዘይቱ፣ ሩዙ፣ ዳቦው፣ ሁሉንም ያመጣቸው ድንጋዩ ነው፡፡ ያ
ድንጋይ እዚያ ቦታ ላይ ስንት ዘመን ኖሯል፡፡ ስንት ሰው ተደባድቦበታል፣ ስንት ሰው ተቀምጦበታል፣
ስንቱን ሰው እንቅፋት ሆኖ መትቶታል፡፡ ስንቱ ሰውስ ተጫውቶበታል፡፡
«እኔ ግን ሾርባ ሠራሁበት፡፡ ወዳጄ አንተም አጠገብህ ባለው በቀላሉ ልታገኘው በምትችለው ነገር፣
እግዜር በነጻ ባደለህ ነገር በርሱ ሾርባ ለመሥራት ተነሣ፡፡ የሌለህን ሥጋ፣ ድንች፣ ካሮት፣ ሩዝ፣ እያሰብክ
ለምን ትናደዳለህ፣ ለምንስ ታዝናለህ፣ ለምንስ ተስፋ ትቆርጣለህ፣ ለምንስ ራስህን ድኻ ታደርጋለህ?
«ሀብታም ነህ ወዳጄ፣ ሀብታም ነህ፡፡እግዜር የሰጠህን ስላላወቅከው እንጂ ካለህ ከጀመርክ ሀብታም ነህ፡፡
ከሌለህ ከጀመርክ ያለህን ታጣለህ፡፡ ካለህ ከጀመርክ ግን የሌለህንም ታመጣዋለህ፡፡ ድንጋይ ሾርባ
አይሆንም፡፡ ካሰብክበት ግን ድንጋይ ሾርባ ያመጣል፡፡
«በልመና የምታገኘው የበታችነትን ብቻ ነው፡፡የምትለምን ከሆነ ተለማኞቹ ይንቁሃል፡፡ ተወው አትለምን፡፡
37 views07:55