Get Mystery Box with random crypto!

ሰሞንኛ (በእውቀቱ ስዩም) የሆነ ጊዜ ላይ የተወሰኑ ጓደኞቼን የምወዳት ልጅ ወላጆች ቤት ሽ | እግር ኳስ Meme™

ሰሞንኛ
(በእውቀቱ ስዩም)

የሆነ ጊዜ ላይ የተወሰኑ ጓደኞቼን የምወዳት ልጅ ወላጆች ቤት ሽምግልና ላክሁዋቸው::
የፍቅረኛየ አባት “ልጁ ምናለው?” ብለው ጠየቁ ::
ከሽማግሌዎች አንዱ ትንሽ ሲያቅማማ ከቆየ በሁዋላ፥

“ ከሁለት መቶ ሺህ ያላነሰ ተከታይ አለው፤ ፌስቡክ ላይ “ ብሎ ተከዘ::
ቁሞ የመቅረት ታሪኬም በዛች ቀን ጀመረ፤

በቀደም ለታ፥ ፌስቡክ ፥ ከሁለት መቶ ሺህ በላይ ተከታዮቼ መካከል፥ ዘጠኝ ሺውን ብቻ አስቀርቶል ሌላውን አፈሰብኝ፤ የገንዘቡ ሳያንስ የተከታይ ግሽበት መታገስ የምችልበት ጫንቃ አልነበረኝም::

ከተከታዮቼ መሀል ፥ ጽፌ የምለጥፈውን አንብበው መውደዳቸውን የሚያሳዩኝ አስተያየቱን የሚለግሱኝ ከአስር ሺህ አይበልጡም፤ ከተከታዮቼ መሀል” ክንዴ ቢዝል፥ ምላሴን ቢያዳልጠው፥ ግጥሜ ልቦና ባይረታ፥ ቀልዴ ጥርስ ባይመታ፥ ልክ ልኬን ሊነግሩኝ መከትከቻውን እየሳሉ እሚጠብቁኝ እንዳሉ አውቃለሁ፤ዝም ብለው ደጃፍ ላይ ተቀምጠው ሳልፍ ሳገድም እሚያዩኝም ሞልተዋል::

ቢሆንም “
“ባይነዳ ባይረዳ ባይኖረውም ሀብት “
ከደጃፍ ሲቀመጥ ደስ ይላል አባት “ ይላል እማ ሸንበቆ ጠላ ቤት ግድግዳ ላይ የተለጠፈ ጥቅስ!
እኔም እለላሁ፤
“ባይለይክ፤ ባይኮምንት ፤ አሻራው ባይታይ”
ከደጃፍ ሲቀመጥ ደስ ይላል ተከታይ”

የፌስቡክ አለቃ ፥ በሁሉን አወቅነቱ፥ ይህንን ስሜቴን ተረድቶ ፥ በነበሩት ተከታዮቼ ላይ አንድ የቀበሌ አዳራሽ የሚሞሉ ተከታዮች ከራሱ ጨምሮ መለሰልኝ::

በባለፈው ዝግጅት ላይ ለታደሙ ወዳጆቼ የምስጋና ቃል ልጽፍ ሰንዳ ሰንዳ ስል መብራት እልም አለ:: እኛ ሰፈር ያለው ትራንስፎርመር በሚፈነዳበት መጠን የልደት ፊኛ አይፈነዳም ፤ አሁን አሁንማ፥ መብራት ሲጠፋ እንደ ድሮው መናደድ አቁሚያለሁ፤ በጨለማ ውስጥም ቢሆን ስራ እንዳልፈታ ምቾት እንዳላጣ አድርጌ ራሴን አላማምደዋለሁ፤ ሆመር ፥ ሀሰን አማኑ፥ እማሆይ ገላነሽ፥ ወዘተ፤ ውበት ፥ ሀሳብ እና ለዛ ለማፍለቅ የግድ ውጫዊ ብርሀን አስፈላጊ እንዳልሆነ ምስክር ናቸው፤ እንዲህ እያልሁ ዘና ብየ ጥቂት እንደቆየሁ አምፖሉ እንደ ነሀሴ ሰማይ ብልጭ ብሎ ድርግም ይላል፤ ጉዋደኛየ ምኡዝ አንድ የሚወዳት ልጅ ነበረች፤ የሆነ ቀን ሲጽፍላት አትመልስም፤ ሲደውልላት አታነሳም፤ ጭራሽ ለተወሰኑ ወራት መገኛዋን ሁሉ ትደመስሳለች፤ እሱም ያለ እሷ ለመኖር ራሱን ለማለማመድ ይፍጨረጨራል፤ ከዛ እፎይ ብሎ እየኖረ እያለ You miss me? '' የሚል ቴክስት ትልክለታለች፤ አምፖሌ ብልጭ ብሎ የተለማመድሁትን የጨለማ ደስታ ሲያደፈርስብኝ ትዝ የሚለኝ ይሄ ነው፤

ጥለት ሚድያ ባሰናዳው የሰኞ ዝግጅት ላይ የታደማችሁ ምስጋናየን ይድረሳችሁ፤ ገና ሁለተኛ ዝግጅታችን እንደመሆኑ መጠን ጉድለታችንን ለማሻሻል አጥብቀን እንሰራለን፤ ሐረር ባንድ ጀንበር አልተገነባችም፤ (በጊዜው በጉልህ የታየው የድምጽ ችግር ከመብራት መጥፋት ጋራ በተያያዘ በጄኔረተር ምክንያት የመጣ ነው፤ ለዚህ ይቅርታ እንጠይቃለን) ሌላ እንዲስተካከል እምትፈልጉትን ሳታስባንኑ ፥ በአካል አግኝታችሁ፥ ምሳ እየጋበዛችሁ፤ ትከሻየን እየቸበቸባችሁ ንገሩኝ፤ በማቱሳላ አቆጣጠር ገና ልጅ ነኝ፤ እታረማለሁ::

የዝግጅቱ ቀን ከጉዋደኛየ ጋራ ስደርስ ጥቂት አርፍጄ ነበር፤ ከብሄራዊ ትያትር ወዲህ ማዶ፥ ኢትዮጵያ ሆቴልን አለፍ ብሎ ሰው በረጅሙ ተሰልፎ ሳይ ራሴን መቆጣጠር ተሳነኝ፤ ልቤ ተነካ፤” ወንድ ልጅ ብቻውን ነው እሚያለቅሰው “ ይላል ባለቅኔ ጸጋየ ገብረመድህን:: እኔ ግን ወንድ ልጅ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ባያላቅስ ደስ ይለኛል፤ የዛን ቀን ግን አልቻልኩም፤ የደስታ እምባየ “ናፕኪን” ከደረት ኪሴ እስካወጣ እንኳን አልታገሰኝም

“ አሁን እኔ ይሄን የሚያህል ሰልፍ deserve አደርጋለሁ?”
አልሁት ጓደኛየን፥

“ ተረጋጋ! እነዚህ ወደ ሜክስኮ የሚሄደውን ምኒባስ ለመሳፈር የተሰለፉ ናቸው “

ከወደዱ ያጋሩ

@yegetemkalat
@poem_merry