Get Mystery Box with random crypto!

††† እንኳን ለሰማዕታት ቅዱሳን ቂርቆስ ወኢየሉጣ: ወነቢይ አብድዩ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም | ዝማሬ ዳዊት - Zimare Dawit

††† እንኳን ለሰማዕታት ቅዱሳን ቂርቆስ ወኢየሉጣ: ወነቢይ አብድዩ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

✞ ቂርቆስ ወኢየሉጣ ✞

††† ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ካሏት ዐበይት ሰማዕታት አንዱ ቅዱስ ቂርቆስ ነው:: በተለይ በዘመነ ሰማዕታት ተነስተው እንደ ከዋክብት ካበሩትም አንዱ ነው:: ቅዱስ ወንጌል እንዲህ ይላል:- "መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራል::" (ማቴ. 7:17)

መልካም ዛፍ ቅድስት ኢየሉጣ መልካም ፍሬ ብጹዕ ቂርቆስን አፍርታ ተገኝታለችና ክብር ይገባታል:: ቡርክተ ማሕጸንም እንላታለን:: የተባረከ ማሕጸኗ የተባረከ ልጅን ለ9 ወር ተሸክሟልና::

በዚያ ክርስቲያን መሆን መከራ በነበረበት ዘመን ይህንን ደግ ሕጻን እርሷን መስሎ: እርሷንም አህሎ እንዲገኝ አስችላለችና:: አበው በትውፊት እንዳቆዩልን ከሆነ በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን እናታችን ቅድስት ኢየሉጣ ብጹዕ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስን ወልዳለች::

በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን በሮም ግዛት ክርስትና ቢስፋፋም በዚያው ልክ መምለክያነ ጣዖቱ የገነኑ ነበሩ:: በተለይ ከነገሥታቱ ጀምሮ ዋና ዋና የሥልጣን ቦታዎች በአሕዛብ እጅ በመሆናቸው ለዘመኑ ክርስቲያኖች ፈታኝ ነበር::

ማንኛውም ክርስቲያን መሠረታዊ ፍላጐቶቹ እንዲሟሉለት አሕዛብ ላቆሟቸው ጣዖቶች መንበርከክ ነበረበት:: መብቱን ከመገፈፉ ባሻገር "ተበድያለሁ" ብሎ ወደ ፍርድ ቤት ሔዶ እንኩዋ የመጮህ እድል አልነበረውም:: ምክንያቱም የሚሰማው አልነበረም::

በዚያ ላይ በየጊዜው ለክርስቲያኖች ፈታኝ የሆኑ አዋጆች ይወጣሉ:: የክርስትናን ጐዳና ይበልጥ የሚያጠቡ ሕጐችም ዕለት ዕለት ይፈበረኩ ነበር:: ስለዚህም በወቅቱ የነበረ አንድ ክርስቲያን ሃይማኖቱን ከወደደ ወይ እስከ ሞት መታገስ: ካልሆነ ደግሞ ሃገርን ጥሎ በዱር: በገደል መሰደድ ነበረበት::

እውነት ለመናገር ዜና ሰማዕታትን የማያውቅ ክርስቲያን ክርስቶሳዊ ነው ሊባል አይችልም:: ምክንያቱም ዛሬ እንዲህ እንደ ዋዛ የያዝናት ሃይማኖታችን እንዴት እንደ መጣችና ምን እንደ ተከፈለባት አብዛኛው ትውልድ አያውቅምና::

ሕጻኑ ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ብጽዕት ኢየሉጣም የዚህ ዘመን (የዘመነ ሰማዕታት) ፍሬ ናቸው:: በጊዜው በሮም ግዛት ሥር እስክንድሮስ የሚሉት ክፉ ንጉሥ ነግሦ ነበርና ብዙ ክርስቲያኖች ተሰደዱ:: ጣዖትን ላለማምለክም ተሰው::

በዚህ ጊዜ አንጌቤናይት (ኢጣልያዊት) ብጽዕት ኢየሉጣም በመበለትነት (ባሏ በሕይወት ባለ መኖሩ) ትኖር ነበር:: ልጇ ቅዱስ ቂርቆስ ምንም ገና 3 ዓመቱ ቢሆንም ነገረ ሃይማኖትን ታስተምረው: ፍቅረ ክርስቶስን ትስልበት ነበር::

እስክንድሮስ የክህደት አዋጅን ሲያውጅም ቅድስቲቱ ለሕጻን ልጇ ራርታ ሽሽትን መረጠች:: ሃብት ንብረቷን: ወገንና ርስቷንም ትታ: ሕጻን ልጇን ተሸክማ ተሰደደች:: መከራው ግን በሔደችበት አለቀቃትም::

እስክንድሮስ ተከትሎ ባለችበት ቦታም አገኛት:: ወታደሮች ልጇን ሳያገኙ እርሷን ብቻ ይዘው ወደ መኮንኑ አቀረቧት:: መኮንኑም "ስምሽን ንገሪኝ" ቢላት "ስሜ ክርስቲያን ነው" አለችው:: ተቆጥቶ "ትክክለኛውን ስምሽን ተናገሪ" ቢላት "እውነተኛው ስሜ ክርስቲያን ነው:: ሞክሼ (ሞክሲ) ስም ከፈለግህ ኢየሉጣ እባላለሁ" አለችው::

"ለጣዖት ልትሰግጂ ይገባል" ሲላትም "እውነትን ይነግረን ዘንድ የ3 ዓመት ሕጻን ፈልገህ አምጣና ተረዳ" ስላለችው ወታደሮቹን እንዲፈልጉ ላካቸው:: የሃገሩ ሰዎች ልጆቻቸውን ስለደበቁ የተገኘ ቅዱስ ቂርቆስ ነበር::

ቅዱሱ ሕጻን በወታደሮች ተይዞ ሲቀርብ መልኩ ያበራ ነበርና መኮንኑ "በሐከ ፍሡሕ ሕጻን - ደስ የተሰኘህ ሕጻን እንዴት ነህ" ቢለው "ትክክል ነህ! እኔ በጌታየ ክርስቶስ ዘንድ ደስታ ይጠብቀኛል:: አንተ ግን በክህደትህ ወደ ገሃነም ትወርዳለህ" አለው::

በሕጻኑ ድፍረት የደነገጠው መኮንኑ በብስጭት "እሺ! ስምህን ንገረኝ" አለው:: ያን ጊዜ "ከንጹሕ ምንጭ የተቀዳ: ስሜ ክርስቲያን ነው:: እናቴ የሰየመችኝን ከፈለክ ግን ቂርቆስ ነው" ሲል መለሰለት::

ከዚያም እየደጋገመ "እኔ ክርስቲያን ነኝ" ብሎ በመጮሁ መኮንኑ ስቃይን በቅዱሱ ሕጻን እና በቡርክት እናቱ ላይ አዘዘ:: ከዚህ በሁዋላ በእነርሱ ላይ የተፈጸመውን ግፍና የወረደባቸውን የመከራ ዶፍ እናገር (እጽፍ) ዘንድ ግን የሚቻለኝ አይመስለኝም::

በግርፋት የጀመረ ስቃይ ሊሰሙት ወደ ሚጨንቅ መከራ ቀጠለ::
*7 ብረት አግለው በዐይናቸው: በጆሯቸው: በአፋቸውና በልባቸው ከተቱ::
*በ4 ችንካሮች ላይ አስቀመጧቸው::
*በእሳት አቃጠሏቸው::
*ጸጉራቸውን ከቆዳቸው ጋር ገፈፉ::
*ከዚህ በላይ ብዙ ስቃይንም አመጡባቸው::

እናትና ልጅ ግን ለክርስቶስ ታምነዋልና ጸኑ:: ቅድስት ኢየሉጣ ብትደነግጥ ልጇ አጸናት:: ከብዙ ስቃይና መከራ በሁዋላም በዚህች ዕለት በሰማዕትነት ሲያርፉ ጌታ እንደ ቃሉ የሕጻኑን ሥጋ በሠረገላ ኤልያስ አኑሮታል:: ለእኛ የሚጠቅም ብዙ ቃል ኪዳንንም ሰጥቶታል::

††† ቅዱስ አብድዩ ነቢይ †††

††† "አብድዩ" ማለት "የእግዚአብሔር አገልጋይ" ማለት ነው:: ቁጥሩ ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን የቅዱስ ኤልያስ ታላቁም ደቀ መዝሙር ነው:: ቅዱሳን ነቢያት ዮናስና ኤልሳዕም ባልንጀሮቹ ነበሩ::

ቅዱስ አብድዩ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ800 ዓመት አካባቢ የከሃዲው ንጉሥ የጦር መሪ ሆኖ በሃምሳ አለቃነት አገልግሏል:: ግፈኛዋ ኤልዛቤል ነቢያተ እሥራኤልን ስታስፈጅ 50ውን በአንድ ዋሻ : 50ውን ደግሞ በሌላ ዋሻ አድርጐ አትርፏቸዋል:: 900ው ግን ተጨፍጭፈዋል::

ያተረፋቸውንም ክፉ ዘመን እስኪያልፍ ድረስ መግቧቸዋል:: አክአብና ኤልዛቤል ከሞቱ በሁዋላም ቅዱስ ኤልያስን ተከትሎ ሹመቱን ትቷል:: እግዚአብሔር ገልጾለትም ትንቢት ሲናገር: ሕዝቡንም ሲገሥጽ ኑሯል::

በብሉይ ኪዳን ካሉ የትንቢት መጻሕፍትም በጣም አጭሩን የጻፈው ይሕ ነቢይ ነው:: ትንቢተ አብድዩ ባለ አንድ ምዕራፍ ብቻ ናትና:: ቅዱሱ በዚህች ቀን ዐርፎ ወገኖቹ ቀብረውታል::

††† አምላከ ሰማዕታት በምሕረቱ ይማረን:: በይቅርታው ኃጢአታችንን ይተውልን:: ከበረከተ ሰማዕታትም ይክፈለን::

††† ጥር 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ
2.ቅዱስ አብድዩ ነቢይ
3.ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ
4.ቅድስት ሶፍያ
5.ቅድስት አድምራ
6."11,004" ሰማዕታት (ከቅዱስ ቂርቆስ ጋር በሰማዕትነት ያለፉ)

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ
2.ቅዱስ ሚናስ ሰማዕት
3.ቅድስት ክርስጢና
4.ቅድስት እንባ መሪና

††† "በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ የምትኖር: ማደሪያህንም ከፍ ከፍ ያደረግህ: በልብህም:- 'ወደ ምድር የሚያወርደኝ ማን ነው?' የምትል አንተ ሆይ! የልብህ ትዕቢት አታልሎሃል:: እንደ ንስር መጥቀህ ብትወጣ: ቤትህም በከዋክብት መካከል ቢሆን: 'ከዚያ አወርድሃለሁ' ይላል እግዚአብሔር::" †††
(አብድዩ 1:3)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር
†††

@ortodoxbibele
@ortodoxbibele
@ortodoxbibele