Get Mystery Box with random crypto!

​​​​✞ እንኳን ለአጋእዝተ ዓለም 'ሥላሴ' እና 'ቅዱስ ሶል ዼጥሮስ' ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረ | ዝማሬ ዳዊት - Zimare Dawit

​​​​✞ እንኳን ለአጋእዝተ ዓለም "ሥላሴ" እና "ቅዱስ ሶል ዼጥሮስ" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ

#ሥሉስ_ቅዱስ

ምሥጢራት በእምነት ለማይኖር: በትሕትናም ለማይቀርብ የሚገለጡ አይደሉም::

+እግዚአብሔር አንድም ነው: ሦስትም ነው:: ጊዜ ሣይሠፈር ዘመንም ሳይቆጠር እግዚአብሔር በስም: በአካል: በግብር ሦስትነቱ: በባሕርይ: በሕልውና: በመለኮትና በሥልጣን አንድነቱ የጸና አምላክ ነው::

+ከዓለም መፈጠር በፊት ስለ ነበረው ነገር የሚያውቅ ራሱ ሥላሴ ብቻ ነው:: ዓለምን ከፈጠረ በሁዋላም ምሥጢረ ሥላሴ (መለኮት) ብለን የምንማረው ትምሕርት እንድንና እንጠቀም ዘንድ እርሱ የገለጠልንን ያህል ብቻ ነው::

+ይኼውም በየጊዜው እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ቅዱሳኑ የገለጠው ምሥጢር ነው:: ከዚህ አልፈን በሥጋዊ አዕምሯችን ጌታን "እንመርምርሕ" ብንለው ግን ፍጻሜአችን ሞት: ማደሪያችንም ገሃነመ እሳት መሆኑ አይቀርም::

+እግዚአብሔር በአንድነቱና ሦስትነቱ ሳለ ይህንን ዓለም ፈጠረ:: እግዚአብሔር ዓለምን ለምን ፈጠረ ቢሉ:- ስሙን ቀድሰን ክብሩን እንድንወርስ ነው:: ከዚህ የተረፈውን ምክንያት ግን ራሱ ያውቃል::

በአንድነቱ ምንታዌ (ሁለትነት): በሦስትነቱ ርባዔ (አራትነት) የሌለበት የዘለዓለም አምላክ: የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው:: አብ: ወልድ: መንፈስ ቅዱስ በስም: በአካል: በግብር ሦስትነት በባሕርይ: በሕልውናና በፈቃድ አንድነት የጸኑ ናቸው:: በዚህ ጊዜ ተገኙ: በዚህ ጊዜ ያልፋሉ አይባሉም:: መጀመሪያም መጨረሻም እነርሱ ናቸውና::

+ርሕሩሐን ናቸውና በእናት ሥርዓት "ቅድስት ሥላሴ" እንላቸዋለን:: የሚጠላቸው (የማያምንባቸውን) አይጠሉም:: የሚወዳቸውን ግን እጽፍ ድርብ ይወዱታል:: በቤቱም መጥተው ያድራሉ::

+ከፍጥረታት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የአብርሃምን ያህል በሥላሴ ዘንድ የተወደደ ፍጡር የለም:: አባታችን ቅዱስ አብርሃም የደግነት ሁሉ አባት ነውና በኬብሮን : በመምሬ ዛፍ ሥር ሥላሴን ተቀብሎ አስተናግዷል::

+አባታችን አብርሃም በ99 ዓመቱ: እናታችን ሣራ በ89 ዓመቷ ሥላሴን በድንኩዋናቸው አስተናገዱ:: አብርሃም እግራቸውን አጠበ:: (ወይ መታደል!) በጀርባውም አዘላቸው:: (ድንቅ አባት!) ምሳቸውንም አቀረበላቸው:: እንደሚበሉ ሆኑለት:: በዚያው ዕለትም የይስሐቅን መወለድ አበሠሩት::

+ሥላሴን ያስተናገደች ድንኩዋን (ሐይመት) የድንግል እመቤታችን ማርያም ምሳሌ ናት:: በድንግል ላይ አብ ለአጽንኦ: መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ: ወልድ በተለየ አካሉ ለሥጋዌ በእርሷ ላይ አርፈዋል / አድረዋልና::

በዓለ ሥላሴ በዚህ ቀን የሚከበረው ስለ 2 ምክንያቶች ነው:: ቀዳሚው ሕንጻ ሰናዖርን ማፍረሳቸው ሲሆን 2ኛው ደግሞ ቅዳሴ ቤታቸው ነው::

#ሕንጻ_ሰናዖር

ሰናዖር ከሺዎች ዓመታት በፊት በአሁኗ ኢራቅ አካባቢ እንደ ነበረ የሚነገርለት ግዛት ሲሆን ስሙ ለሃገሪቱም: ለንጉሡም በተመሳሳይ ያገለግል ነበር:: ከናምሩድ ክፋት በሁዋላ ሰናዖርና ወገኖቹ ከሰይጣን ተወዳጁ::

+ከጥፋት ውሃ (ከኖኅ ዕረፍት) በሁዋላ በሥፍራው በአንድነት ይኖሩ ነበርና እርስ በርሳቸው "ኑ ሳንበተን ስማችን የሚጠራበትን ሕንጻ እንሥራ:: በዚያውም አባቶቻችን በውሃ ያጠፋ እግዚአብሔርን እንውጋው" ተባባሉ::

+ቀጥለውም ሰማይ ጠቀስ ፎቅን ገነቡ:: ከሕንጻው መርዘም የተነሳ በጸሐይ አብስለው በልተዋል ይባላል:: ቀጥለውም ጦር እያነሱ ፈጣሪን ሊወጉ ወርውረዋል::

+መቼም የእነዚህን ሰዎች ክፋትና ቂልነት ስንሰማ ይገርመን ይሆናል:: ግንኮ ዛሬ ሰለጠንኩ በሚለው ዓለም እየተሠራ ያለው ከዚህ የከፋ ነው:: ቸርነቱ ቢጠብቀን እንጂ እንደ ክፋታችንስ ጠፊ ነበርን::

+ርሕሩሐን ሥላሴ ግን የሰናዖር ሰዎች የሠሩትን አይተው ማጥፋት ሲችሉ አላደረጉትም:: የባሪያቸውን የኖኅን ቃል ኪዳን አስበዋልና:: ይልቁኑ "ንዑ ንረድ ወንክአው ነገሮሙ ለከለዳውያን-ቁዋንቁዋቸው እንደባልቀው" አሉ እንጂ::

+ከለዳውያን ልሳናቸው ተደበላልቆ 71 ቁዋንቁዎች ተፈጠሩ:: እነርሱም ስምምነት አጥተው ተበተኑ:: ሥላሴም ያን ሕንጻ በነፋስ ትቢያ እንዲሆን በተኑት:: ስለዚህም እስከ ዛሬ ሥፍራው "ባቢሎን (ዝሩት)" ሲባል ይኖራል::

#ቅዳሴ_ቤት

ልክ የዛሬ 324 ዓመት: አድያም ሰገድ ኢያሱ በኢትዮዽያ በነገሡ በ10ኛው ዓመት: (በ1684 ዓ/ም) በጐንደር ከተማ ንግሥተ አድባራት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተሰርታ ተጠናቃለች::

+ጥር 7 ቀንም ሊቁ ክፍለ ዮሐንስን ጨምሮ በርካታ ምዕመናን: ሠራዊት: መሣፍንትና ሊቃውንት ባሉበት ቅዳሴ ቤታቸው ተከብሯል:: በዕለቱም ታላቅ ሐሴት ተደርጉዋል:: ኢያሱ አድያም ሰገድ ኃያል: ደግ: ጥበበኛ: አስተዋይ: መናኝ ንጉሥ ነውና::

+ቤተ ሥላሴን አስጊጿታልና ከዚህ ቀን ጀምሮ ጥር ሥላሴ በድምቀት የሚከበር ሆኗል:: ነገር ግን በተሠራች በ16 ዓመቷ ደጉ ኢያሱ ከተገደለ በሁዋላ ቤተ ክርስቲያኑ በአደጋ ፈርሷል:: ዛሬ የምናየው በ1708 ዓ/ም በልጁ በአፄ ዳዊት ሣልሳዊ የታነጸውን ነው::

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur