Get Mystery Box with random crypto!

#ኹሉንም_ነገር_ለእግዚአብሔር_እንስጠው ወርቅን የሚያነጥር ሰው አንዲትን የወርቅ ቅንጣት ወደ እ | ኦርቶዶክሳዊ ፎቶዎች(Orthodox pictures)

#ኹሉንም_ነገር_ለእግዚአብሔር_እንስጠው

ወርቅን የሚያነጥር ሰው አንዲትን የወርቅ ቅንጣት ወደ እሳት ውስጥ ጨምሮ እጅግ ንጹህ እስክትኾን ድረስ ይጠብቃታል፡፡ እግዚአብሔርም ልክ እንደዚሁ ሰዎች እስኪነጹ፣ እስኪለወጡና ባገኛቸው ነገር ጥቅም እስኪያገኙ ድረስ ፈተና ውስጥ እንዲቆዩ ይፈቅዳል፡፡ ይህ ደግሞ ከጥቅምም እጅግ ከፍ ያለ ጥቅም ነው፡፡

ስለዚህ ፈተና ሲገጥመን ውስጣችን ሊረበሽ ወይም ተስፋ ሊቈርጥ አይገባውም፡፡ ያ ወርቅን የሚያነጥር ሰው በእሳት ውስጥ የጨመራትን የወርቅ ቅንጣት እዚያ ውስጥ ምን ያኽል ጊዜ መቆየት እንዳለባት ያውቃል፤ መቼ ከእሳቱ ሊያወጣት እንደሚገባውም ያውቃል፡፡ እንዲሁ እስከ መጨረሻው በእሳቱ ውስጥ ተጥላ እንድትቀርና በዚያ እንድትቃጠል አይፈቅድም፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ይህን ከወርቅ አንጣሪው በላይ ያውቃል፡፡ መቼ ከርኵሰታችን እንደምንነጻ ያውቃል፡፡ በመኾኑም ራሳችንን በመጣልና ተስፋ በመቁረጥ በክፋት ላይ ክፋት እየጨመርን እንዳንሔድ ሽቶ መቼ ከዚያ ፈተና እንደሚያወጣን ያውቃል፡፡ ስለዚህ ድንገት ያላሰብነው ነገር ቢገጥመን በፍጹም የምናማርር፣ ወይም ተስፋ የምንቈርጥ ልንኾን አይገባንም፡፡ ከዚህ ይልቅ የእነዚህ ነገሮች ምንነትን የሚያውቅ እግዚአብሔርን መጠበቅ፣ እርሱ እስከ ፈቀደው ጊዜ ድረስም ልቡናችንን በእሳት እንዲፈተን ማድረግ ይገባናል፡፡ ምክንያቱም ይህ ነገር በእኛ ላይ እንዲኾን የፈቀደው ለእኛ ጥቅምና በዚያ ውስጥ ኾነን በምናሳየው ጥረት ይበልጥ ሊያከብረን ስለሚወድ ነው፡፡

ይህን በማስመልከትም ጠቢቡ ሰው እንደዚህ ሲል መክሮናል፡- “ልጄ ሆይ! ለእግዚአብሔር ትገዛ ዘንድ ብትሔድ ሰውነትህን ለመከራ አዘጋጅ፤ ልብህን አቅና፤ ኹልጊዜ ታገሥ፤ አታወላውልም፤ በመከራ ብትጨነቅም አትጠራጠር” /ሲራ.2፥1-2/፡፡ “ኹሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ስጠው፡፡” ለምን? እግዚአብሔር ከዚያ መከራ መቼ እኛን ማውጣት እንዳለበት ያውቃልና፡፡ ስለዚህ ኹሉንም ለእርሱ ልንሰጥ፣ ዘወትር እርሱን ልናመሰግን፣ ኹሉንም ነገር - ጥቅምም ይኹን ቅጣት - በአኰቴት ልንቀበል ይገባናል፤ ይህም ቢኾን ለእኛ ረብሕ የሚኾን ነውና፡፡ አንድ ሐኪም፥ ሐኪም የሚባለው ታካሚውን ገላዉን ሲያጥበውና ሲመግበው እንዲሁም ደስ ወደሚያሰኝ ስፍራ ሲወስደው ብቻ አይደለም፤ በእርሱ (በታማሚው) ሰውነት ላይ የቀዶ ጥገና ምላጭና ቢላ ሲያሳርፍም ጭምር ሐኪም ነው፡፡ አባትም አባት የሚባለው ልጁን ሲንከባከብ ብቻ አይደለም፤ የገዛ ልጁን ከቤት ሲያስወጣው፣ ሲገሥጸው፣ ሲገርፈውም ያው አባት ነው፡፡ ስለዚህ እኛም እግዚአብሔር ከሐኪሞችም በላይ ሰውን ወዳጅ እንደ ኾነ በማወቅ፥ ምን ዓይነት የሕክምና ዓይነት እንደሚሰጠን በጥልቀት አንጠይቅ፤ ወይም ደግሞ ለደረሰብን መከራ እርሱን ተጠያቂ አናድርግ፡፡ ከዚህ ይልቅ እርሱ የወደደውን ነገር - ቅጣትም ይኹን ቅጣት የሌለው ነገር - ብቻ ምንም ይኹን ምን በአኰቴት ልንቀበል ይገባናል፡፡

በየትኛውም መንገድም ቢኾን የእርሱ ፈቃድ እኛ እንድንድንና ከእርሱ ጋር አንድ እንድንኾን ነውና፡፡ የትኛው መንገድ ለእኛ እንደሚጠቅምም እርሱ ያውቋል፡፡ እያንዳንዱ ሰው የትኛው መንገድ ወደ እርሱ እንደሚመልሰው ያውቃል፡፡ ኹላችንም እንዴትና በምን ዓይነት መንገድ ልንድን እንደምንችል ያውቃል፡፡ በመኾኑም የሚመራን በዚህ እኛ በምንድንበት መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ ወደየትኛውም መንገድ ቢወስደንም - ልክ እንደ መጻጉዑ - እርሱ እንደሚያዘ’ን ተከትለን መሔድ እንጂ ትልቁ ጉዳያችን በለስላሳና በቀላል አልያም ደግሞ በከባድና በሸካራ ጎዳና እንድንሔድ የሚያዘ’ንን ትእዛዝ መኾን የለበትም (ልንሔድበት የሚገባው መንገድ እርሱ ስለሚያውቀው እንዲሁ መታዘዝ እንጂ የመንገዱን ከባድነት ወይም ቀላልነት የእኛ አጀንዳ ሊኾን አይገባውም፡፡)

@orthodox_pictures
@orthodox_pictures