Get Mystery Box with random crypto!

ኮኮብ ቆጣሪዎችንና አፈጮሌ ፖለቲከኞችን አትመኗቸው!!! ፎረር ኢፌክት (Forer Effect) አን | ኑ እናንብብ

ኮኮብ ቆጣሪዎችንና አፈጮሌ ፖለቲከኞችን አትመኗቸው!!!
ፎረር ኢፌክት (Forer Effect)

አንባቢዬ ሆይ ሊያስደነግጥህ ይችላል ግን እኔ በግል አውቅሃለሁ። አንተንም እንዲህ እገልፅሃለሁ፡፡ ‹‹ሌሎች እንዲወዱህና እንዲያደንቁህ በጣም ትፈልጋለህ፡፡ ለራስህም ምክንያታዊና አስተዋይ ለመሆን ትፈልጋለህ፡፡ ያልተጠቀምክበትና ሁሌ የሚቆጭህ እምቅ ችሎታ አለህ፡፡ የተወሰኑ ድክመቶች ቢኖሩብህም የምታስተካክላቸው አይነት ናቸው፡፡ ፆታዊ ግንኙነትህ የተወሰኑ ችግሮችን ፈጥሮብሃል፡፡ ከውጭ ለሚያይህ ስነ ስርዓትህን የጠበቅህ እና ራስህን የምትቆጣጠር ብትመስልም ውስጥህ ግን ይጨነቃል፤ ይፈራል፡፡

‹‹የወሰንከውን ውሳኔዎች ትክክለኛነት ወደኋላ እየተመለስክ የምትጠይቅባቸው ጊዜያት አሉ፡፡ ብዙ አማራጮችንና ለውጦችን ትፈልጋለህ፡፡ ይህንን የሚያደናቅፉብህ ነገሮች ሲበዙም ትበሳጫለህ፡፡ ራስህን እንደገለልተኛና ነጻ አሳቢ ስለምታይ ትኮራለህ፡፡ የማንንም ሀሳብ ሳታረጋግጥ አትቀበልም፡፡ ለሌሎች ራስህን ሙሉ በሙሉ ግልጽ ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ ታውቃለህ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ተግባቢ፣ ትሁት ፣ተጫዋች ትሆናለህ ፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ዝምተኛ እና ሰው የማታምን ትሆናለህ፡፡ አንዳንዶቹ ፍላጎቶችህ ፈጽሞ መሆን የማይችሉ ይመስላሉ አንተ ግን እንደምታደርጋቸው ታምናለህ ፡፡››

ራስህ ታውቀዋለህ? ምን ያህል ገልጬሃለሁ? እስኪ ከ 1 (በጣም ደካማ) እስከ 5 (በጣም ጥሩ) ማርክ ስጠኝ፡፡

የስነ ልቦና ባለሞያው በርትራም ፎረር በ1948 አሁን ከላይ ያቀረብኩትን ጽሁፍ ራሱ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ከዚያም ሁሉም ተማሪዎች እንዲያነቡት ሰጣቸው፡፡ እያንዳንዳቸውም በየግል እንደተጠኑና ጽሁፉም የባህሪያቸው ገላጭ የጥናት ውጤት መሆኑም ተነገራቸው። ካነበቡ በኋላም ከ 1-5 ውጤት እንዲሰጡት ጠየቃችው፡፡ ተማሪዎቹም በአማካይ 4.3/5 ሰጡት፡፡ በዚህም 86% ትክክል ነህ አሉት፡፡ ይህ ምርምር በቀጣዮቹ አስርት አመታት ለብዙ ጊዜ በተለያዩ ሰዎች ላይ ተደጋግሞ ተሰርቷል፤ ውጤቱም ተመሳሳይ ነበር።

አንተም ቢሆን ከ 4 ነጥብ በታች እንዳልሰጠኸኝ አምናለሁ፡፡ ሰዎች ራሳቸውን ለመለየት የሚሞክሩት እንዲህ ባሉ አለም አቀፋዊ መገለጫዎች ነው፡፡ ሳይንስ ይህንን አሳሳች ዝንባሌ ፎረር አፌክት ወይም (Barnum effect) ይለዋል፡፡ ይህ ዘርፍ እነዚህ የተሳሳቱ ሳይንሶች ለምን በትክክል እንደሚሰሩ ያወራል። አስትሮሎጂ(ኮኮብ ቆጣሪዎች) የእጅ ጽሁፍ ምርምር፣ መዳፍ ማንበብና የሙት ማናገር ጥበብ ወዘተን አስታውስ፡፡

ከፎረር ኢፎክት ጀርባ ያለው ምንድን ነው? #በመጀመሪያ ደረጃ በፎረር ጽሁፍ ውስጥ ዓረፍተ ነገሮቹ በጣም ጠቅላላና ለሁሉም ሰው የሚሆኑ ናቸው፡፡ #ሁለተኛ አንዳንድ እኛን የማይገልጹንን ነገር ግን ደስ የሚሉንን ዓረፍተ ነገሮች የመቀበል አባዜ አለብን፡፡ ለምሳሌ «በራስህ የምታስብ በመሆንህ ትኮራለህ» የሚለውን ሀሳብ ተመልከት፡፡ ምንም ጭንቅላት የሌለው፣ ማንንም እየተከተለ የሚኖር መሆን ማን ይፈልጋል? እውነታው ግን ያ ላይሆን ይችላል። #ሶስተኛ ‹‹የአሉታ ተጽዕኖ›› የሚባለው ነገር ሚናውን ይጫወታል። የተዘረዘሩት ዓረፍተ ነገሮች በሙሉ አዎንታዊ ሃሳቦች ብቻ የያዙ ናቸው፡፡ #አራተኛ የስህተቶች ሁሉ አባት የሆነ ነው የማረጋገጥ መድሎዕ (confirmation bias) አለ፡፡ ሳናስበው የሚስማማንና የሚመስለንን ነገር ሁሉ እየተቀበልን ሌላውን እንተዋለን ወይም ደግሞ እውነትም ውሸትም ለማለት የሚከብዱ ሀሳቦችን በመጠቀም ሰዎች እውነት የሚመስለውን እንዲመርጡ የማድረግ ጥበብ ነው።


የጠ/ሚኒስትራችንን ንግግሮችና ፁሁፎች ልብ ካላችሁት በእንደዚህ አይነት ጥበብ (Forer Effect) የተካኑ ናቸው።በህዝብ ዘንድ ተወዳጅነት ካገኙትበት ምክንያትም አንዱ በforer effect የበለፀጉ ንግግሮቻቸው ነው። ንግግሮቹ ከላይ የተጠቀሱት አራቱም ባህሪዎች ይንፀባረቁበታል። ለዚህም ነው ንግግሮቹ ሁሉን የሚያስደስቱና ሁሉንም ህዝብ የሚገልፁ የሆኑት ነገር ግን የጠ/ሚኒስትሩንም ሆነ የፓሪቲያቸውን ግልፅ አቋም አያሳዩም።አጨቃጫቂ እውነታዎችን አድበስብሰው ያልፋሉ፤ እናም ሁልጊዜም ሁሉንም የሚያስደስት ቀጭን መንገድ ይፈልጋሉ።ለጊዜው ሁሉንም ሳይስከፉ ቢያልፋም አቋማቸው በተግባር ሲገለፅ ግን ብዙ ተቃውሞ ይገጥማቸዋል። ምክንያቱም ሁሉንም ማስደሰት የማይቻል ነገር ነውና ሁሉንም ለማስደሰት የሚያደርጉት ጥረትም አቋም የለሽ እንዲሆኑ አርጓቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ንግግሮቻቸውና ተግባራቸው ፍፁም የማይገናኙ ይሆናሉ።ይህም ንግግሮቻቸው እውነተኛውን አቋማቸውን ስለማይገልፁ ነው። ታዲያ እንደዚህ አይነት መሪዎችን ከንግግሮቻቸው ይልቅ ተግባራቸውን በማየት ብቻ ነው አቋማቸውን ማወቅ የሚቻለው።

መነሻ ሀሳብ
(The Art of clearly thinking)
ሮልፍ ዶብሊ

#አቤል
የስብዕና ልህቀት
@Human_intelligence
@Human_intelligence