Get Mystery Box with random crypto!

ሶስት የክረምቱን ብርድ ለመቋቋም የገባሁበት መጠጥ ቤት ውስጥ የተዋወኩት ሰው 'ወደድክም ጠላህም ም | ኖህቶኤል ከመጻሕፍት ገፅ📚

ሶስት
የክረምቱን ብርድ ለመቋቋም የገባሁበት መጠጥ ቤት ውስጥ የተዋወኩት ሰው "ወደድክም ጠላህም ምድር ላይ ስትኖር ሶስት አይነት ሰው ነህ እናንተ ሶስቱ ሰዎች ደግሞ ተራችሁን ጠብቃችሁ በጊዜ ሚዛንነት ስትፈራረቁ ትኖራላችሁ" ሲለኝ። ትኩር ብዬ እየተመለከትኩት "እንዴት ባክህ"? አልኩትና በሆዴ የራሴ ችግር አንሶኝ የማንም ሰካራም መቀለጃ ልሁን ረልኩኝ።
ሰውዬው ማብራራቱን ጀመረ፣ "ማን ነበር ያልከኝ ስምህን? ለነገሩ ስምህን ተወው ይሄን ለማወቅ ሰው መሆንህ ነው የሚፈለገው። ምን መሰለህ አንተ ፍቅር ሳይዝህ፣ አፍቅረህ ሳለ እና የፈቀርከውን ስታጣ ወደድክም ጠላህም ሶስት አይነት ሰው ትሆናለህ" አለኝ።
ነገሩ ብዙም ስላልተገለፀልኝ "እንዴት?" አልኩት።
ሰውዬው እጁን እያወናጨፈ "በል በል እኛ ሀበሾች ስንባል ከድፍኑ ዝርዝሩ ላይ እናተኩራለን እከሌ ሞተ ስንባል ቶሎ ብሎ ነፍስ ይማር እንደማለት ምን ገደለው እንላለን ሌላውን ተወው እከሊት ወለደች ስንባል ምን ወለደች የሚለውን አስቀድመን ነው እንኳን በሰላም ተገላገለች የምናስቀጥለው ይህ ሁሉ ምንድነው የዝርዝር ወሬ ጥማት አንተም እስኪ ትሞት እንደሆን አይሀላሁ እንግዲ" አለኝና የተቀዳለትን አረቄ ጨልጦ በሀሳብ ሲነጉድ ፈገግ ብዬ አየሁትና ውስጤ ሊኖሩ ስለሚችሉት ሶስት ሰዎች ማሰላሰል ያዝኩ መጠጤን እየተጎነጨሁ ለሰአታት ባስብም እኔ ፍቅር ሳይዘኝም አሁን ይዞኝም ያው ሄኖክ ነኝ ብዬ ደመደምኩና ከኪሴ ውስጥ ሞባይሌን አውጥቼ ሰአቱን ሳይ ሰይጣን ልጁን ድሮ ሆ የሚልበት እኩለ ለሊት ነው። በድንጋጤ ተውጬ አንድ ሰው ሶስት ሰው እንደሆነ የሚያምነውን ሰካራም (ይስከር አይስከር እንኳን እርግጠኛ አደለሁም) ተሰናብቼው ወደ ቤቴ ላቀና ስል፣ ''ትንሽ አታመሻሽም?" አለኝ
መለስ ብዬ አየሁትና ጠረጴዛው ላይ ያስቀመጠውን መለኪያ ብድግ አድርጌ እያቀበልኩት ''የማያድሩበት ቤት አያመሹም'' ብዬው ከመጠጥ ቤቱ ወጥቼ መንገዴን ጀመርኩ።
ቤቴ እንደገባሁ ለቀናት የጓጓሁለትን ነገር ለማድረግ ጫማዬን ወለቅ አድርጌ ዘልዬ ተከመርኩባት አልጋዬ ላይ ይግረማችሁ ስለኔና ስለፍቅረኛዬ ከመጨነቄ የተነሳ እንቅልፍ በአይኔ ከዞረ ድፍን ሶስት ቀኔ።
በማግስቱ የሞት ታናሽ ወንድም ከሆነው እንቅልፍ የነቃሁት ሰይጣን ምሳ ፍለጋ አመድ ላይ ተንከባሎ መንገድ ለመንገድ በሚዞርበት ጠራራ ቀትር ነው። የቀሰቀሰኝ የስልኬ ጥሪ ደዋይዋ ደግሞ ሰሚራ ናት። የሚጮኸው ስልኬን ድምፅ አጥፍቼ ይህን ሁሉ ጊዜ ጠፍቼ ምን አባቴ ልላት ነው ብዬ ጭንቀት ውስጥ ገባሁ።
ግን ወደዛው የማታው ሰውዬ ንግግር ወደ አእምሮዬ መጣ። ቆይ ቆይ ድሮ አላፈቀርኩም ነበር ግን አፍቅሬ አይቼዋለሁ ያፈቀርኳትንም አጊንቻታለሁ አሁን ደግሞ አሷን ባጣ በውስጤ ያሉት ሶስት ሰዎች ይገለፁልኝ የሆናል እኔም እየተጨነኩ ከምኖር እንለያይ ብላት ይሻለኛል አልኩና በችኮላ ስልኬን አንስቼ ወደ ሰሚራ ደወልኩ። ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ "ምነው ለቀናት ጠፋህ?" አለችኝ ሰሚራ።
"ለፍቅራችን የወደፊት መንገድ መልስ ፍለጋ ተጉዜ ነበር?" አልኳት በእንቅልፍ የሻከረ ጉሮሮዬን እየሞረድኩ።
"እና የጠፋው መንገድ ተገኘ?" አለችኝ የሚያስቀው ሳቋን እያሰማችኝ።
"አዎ በቃ እንለያይ" አልኳት፣
"ለምን? " ስትለኝ "ስለማልበጅሽ የእኔ ህይወት መንገድ መፍሰሻ ጅማሮ ከአንቺ መንገድ ጋር ሆድና ጀርባ ስለሆነ፣ ለሚያፈቅሩት ደግሞ ደግ ደጉን አይደል የሚመኙት እኔን አጥተሽ ዛሬን ብታለቅሽም ነገና ከነገ ወድያ የማያቋርጥ ሳቅ ፊትሽ ላይ ይዘንባል" አልኳት።

"ታድያ ለምን እስከዛሬ ከጎኔ ሆንክ አለችኝ? "
"እስከዛሬማ ያየነውን ቅዠት በህልም እየፈታን ቁሙ የሚለን አካል አጥተን በለጋ ጉልበት ዳገቱን በሳቅ ጀመርንና መሀሉ ስንደርስ መጀመሪያ ያልሰበሰብነው ሀይል ከየት ይምጣ? አሁን ደግሞ ድካም ሲመጣ ጣት መጠቋቆም ጀመርን" ስላት
"እኛ እኮ እንፋቀራለን" አለችኝ በልመና ድምፅ።

"እውነት ብለሻል ግን ፍቅር እኔ የምለውን እንድናስተውል ፋታ አልሰጠንም ቅርብ ቅርቡን ብቻ ነው የገለጠልን ። አሁን እኔ ማስታገሻ መድሀኒት ሳይሆን ነቃይ መድሃኒት እየሰጠሁሽ ነው። ያው የሚፈውስ መድሃኒት ደግሞ ብዙ ባህሪ ያሳያል ፊትሽን ያሳብጠዋል፣ ያስለቅስሻል፣ ወይ ሆድሽ ላይ አልያም ልብሽ ላይ ውጋት ሊለቅብሽ ይችላል ግን ከቀናት በኋላ ጤነኛ ሰው ያደርግሻል።" ስላት ጥቂት ፀጥ ብላ ከቆየች በኋላ በስልኩ ውስጥ በሲቃ የታጀበ ለቅሶ ይሰማኝ ጀመር እንደገባኝ ከሆነ እንባዋ መንታ መንታ እየወረደ ነው። ሁለታችንንም የሚመለከተንን ሰው ቢኖር እሷ አልቃሽ እኔ አስለቃሽ እንደምንመስል አልጠራጠርም። ዳሩ የእኔን የልብ እንባ ግን ማን አየው ?
ሰሚራ እንደምንም ብላ በሚንቀጠቀጥ አንደበቷ "ግን ለምን ሄኖኬ ለምን እንዲህ ታደርገኛለህ እኛን ምንም አይለየንም ትለኝ አልነበር? ቆይ መንገድ አስጀምረህ አልፈልግም ብሎ መመለስ ቃል አባይ አያረግህም ሞት ነው የሚለየን ብለህ መኖር ሊለያየን ነው?" አለችኝ።

ላስረዳት ብዙ መጣር አልፈለኩም ምክንያቱም ጠጣር እውነት መልኩን እስኪገልጥ ብዙ ጭጋግ ያልፋል ግን ከጥቄዋ ይበልጥ ለቅሶዋ ሲያስጨንቀኝ "ከመሞት በላይ ብዙ ነገር ለየን እኮ ምን አትይኝም?" ስላት ምን? ማለቱ ከብዷት ይሆን እንጃ "እ?" አለችኝ።

"ሀይማኖት ሰሚራዬ አንድ ቤት ሁለት መንግስት አይነግስም እኔና አንቺም ሁለት እውነታ ይዘን አንድ ትልቅ ተቋም ውስጥ አንገባም እንደዛ ካደረግንማ ከሚያስማማን ነገር የሚለያየን ገዘፈ ማለት ነው"።
ተንሰቀሰቀች፣ "ኧረ ሄኖክ ትንሽ እንኳን ላሳዝንህ እሺ እኔን ተወኝ ለእራስህ እንኳን እዘን እንጂ" ስትለኝ
"አንቺ አይዞሽ የሚታይ ሀዘን እኔን ባይ አያጣም በአፅናኝ ብዛት ትበረቻለሽ። የእኔ ሀዘን ግን ስውር ስፌት ሆኖ ይቆይ። ለጊዜው አንቺ ተፅናንተሽ ስትስቂ ካየሁ እንቺን መታደጌ ነው የኔ የዘላለም ደስታ" አልኳትና በሀሳቤ ሶፍት አቀብያት እንባዋን ስትጠርግ አሰብኩና መውደድዋም ከእንባዋ ጋር አብሮ እየወጣ እንደሆነ ሲቃዋ ሲነግረኝ ሀሳቧን ሳትቀይር ስልኩን ዘጋሁባትና ያቋረጠችኝን እንቅልፍ ቀጠልኩ። በድጋሚ ከእንቅልፌ ስነቃ ቀኑ መምሸት ስለጀመረ ሰአቱ ሰይጣን ወዳጆቹን ሰብስቦ ወንዙ ላይ ቡና የሚጠጣበት እንደሆነ ተረዳሁ እና ጆሮዬን ቀስሬ ስሰማቸው ሰይጣንና ጓደኞቹ "ካሁን በኋላ ሄኖክ ሶስት እራሱን አግኝቷል አሉ" እያሉ ቡና መጠጫ ሲያረጉኝ ሰማኋቸሁ።
ልክ የሴጣኑንና የጭፍሮቹን ሀሜት ስሰማ፣ ሶስት ማንነቶቼን ላገኝ ቀርቶ ያለኝን አንድ ማንነት እንዳጣሁ ብልጭ አለልኝ።
ጥቁር አቡጀዴ
--/--
@Noahtoaels_idea