Get Mystery Box with random crypto!

የጥንቃቄ መልዕክት =============== (በአሁኑ ዘመን የተቸገረን መርዳት አስቸጋሪ ደረጃ ላ | Murad Tadesse (Official Channel)☪️🇪🇹

የጥንቃቄ መልዕክት
===============
(በአሁኑ ዘመን የተቸገረን መርዳት አስቸጋሪ ደረጃ ላይ ደርሷል!)
||
በአሁኑ ወቅት የበርካታ ሰዎችን መታመም ሰበብ በማድረግ እርዳታ በማሰባሰብ ሽፋን በተለያዬ መልኩ የሚያጭበረብሩ ሰዎች መብዛታቸው ትክክለኛ ተረጂዎች እንዳይረዱ መሰናክል ሆኗል።

ለናሙና ያክል፦
①) መኪና ተከራይተውና ሐሰተኛ የሕክምና ማስረጃ ይዘው «ወንድማችን ታሞብን ነው!» በማለት በተለያዩ ወረዳዎች እየተዟዟሩ ከማኅበረሰቡ ከታች በፎቶው የምትመለከቱትን ብር ያጭበረበሩ ሰዎች እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን የወላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊስ አሳውቋል።

አሁን የነዚህ ሰዎች ድርጊት በትክክል ሰው ታሞባቸው በመኪና ተዟዙረው ድጋፍ የሚያሰባስቡ ሰዎች በሙሉ በጥርጣሬ ዓይን እንዲታዩ የሚያደርግ ነው።

*
②) ከቅብር ጊዜ ወዲህ የቴክኖሎጂውን መሻሻል ተከትሎ ሌላኛው የማጭበርበሪያ መድረክ የሆነው ማኅበራዊ ሚዲያ ነው። በውሸት ውስወሳና ጅንጀና የተሻለ ገንዘብና ሥራ ታገኛላችሁ በሚል የሚያጭበረብሩ ዘርፈ ብዙ ስካመሮች እንዳሉ ሆነው፤ በተቸገሩ ሰዎች ሽፋን ኪሳቸውን የሚያደልቡም የትየለሌ ናቸው።

እነዚህን በሦስት ከፍለን እንያቸው፦
ሀ) የሆነ ወቅት ላይ የታመመን ህፃን ወይም ሰው ሆስፒታል ተኝቶ የሚያሳይ ወይም ህመሙን አሳዛኝ በሆነ መልኩ የሚገልፅ ፎቶ አያይዘው፤ ከስር የግላቸውን የባንክ አካውንት አያይዘው በሶሻል ሚዲያ በማሰራጨት የሚሸቅሉ አሉ። ምናልባትም ያ የለጠፉት ፎቶ የሆነ ወቅት ላይ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተፖስቶ ገንዘብ የተሰባሰበበት ይሆናል። ግን የተሰባሰበለት ሰው ብሩ ሞልቶለት ታክሞ ድኖ ይሆናል ወይም አላህ ከወሰነም ሞቶ ይሆናል። እነርሱ ግን ያንን እንደ አዲስ ፖስተው በነርሱ አካውንት እንድገባ ያደርጋሉ። ሰውም የተፖሰተውን አሳዛኝ ፎቶ ተመልክቶ ውስጡ ስለሚያዝን ሳያጣራ ይሰድቃል።
*
ለ) የተፖሰተው ፎቶ ወይም ቪድዮ እውነተኛ ይሆናል። በተለይም ቲክቶከሮችና ዩ ቲዩበሮች እዚያ ታማሚ ዘንድ ይሄዱና ቀርፀውት በፖስትና በቀጥታ ስርጭት ገቢ ያሰባስቡለታል። ግን የሚሰባሰብበት አካውንት የራሳቸው አካውንት ነው። ወይም እዛው ተመካክረው የሚተዋወቁት አጭቤዎች በግሩፕ የከፈቱት አካውንት ነው። በኋላ ለታማሚ ትንሽ ነገር ጣል ያደርጉለታል። ምክንያቱም ምን ያክል እንደተሰባሰበ መረጃው ስለሌለው የሰጡትን አምኖ ይቀበላል፤ ያንኑስ ማን አየበት በሚል መንፈስ!

አንዳንዶች ግን በተለይም አሁን ከትናንት በፊት ቲክቶክ ላይ የተከሰተው፤ «ያሰባሰብንለት ልጅ አይድንም ብዬ ብሩን አጥፍቼዋለሁ!» ብሎ በአደባባይ ሲናገር የተቀዳውን ቪድዮ በጆሮዬ ሰምቻለሁ። አለፍ ሲልም ብሩ 350 ሺህ ብር እንደሆነና "ወጣት ነኝ፣ ሰይጣን አሳስቶኝ ነው፣ አካውንቴን ሽጬ እከፍላለሁ!» ብሏል። ውርደት ከነ ግርማ ሞገሱ!
*
ሐ) ለአላህ ብለው ሳይሆን ጉዳዩን እንደ ቢዝነስ አድርገውት በኮሚሽን የሚያሰባስቡ አሉ። ማለትም በፌስቡክ ወይም በቴሌግራም ወይም በቲክቶክ ወይም በዩ ቲዩብ… በርካታ ተከታታይ ያላቸው ግለሰቦች ሰው የታመመበት ሰው ወይም ራሱ የታመመው ሰው ለሕክምና ተቸግሮ አሰባስቡልኝ ሲላቸው «እሺ! ግን ከሚሰባሰበው ገንዘብ ላይ 20%ቱን ልትሰጠን ትስማማለህ ወይ?» ይሉታል። ከዚያ አማራጭ ስለሌለው እሺ ይላል። ህዝቡ በዚህ መልክ እንደሚሠሩ ስለማያውቅ ዝም ብሎ ይሰጣል። ግን ከፊሉ ገንዘብ ለአሰባሳቢው ነው። ይህ ሥራ 100% ሐራም ነው ለማለት ባልደፍርም ግን ብልግና ነው። ወይ በዛ መልኩ እንደምትሠሩ ማሳወቅ አለባችሁ። የተጨነቀን ሰው ከኪሳችሁ አውጥታችሁ መርዳት ባትችሉ እንኳ በነፃ ብታስተባብሩለት ምን ትጎዳላችሁ? ከአላህ አጅር ማግኘት አትሹም?
አላህ ቢጠይቃችሁስ? ወጣት ናችሁ፤ የሶሻል ሚዲያ ጡረተኛ ከመሆን ሠርታችሁ አትበሉም?


ለካ ለዛ ነው ብዙዎች ሰው ታሞባቸው እንዳሰባስብላቸው ሲጠይቁኝ ወይም ሰውም ሆነ መኪና ጠፍቶባቸው አፋልጉኝ እንድለጥፍላቸው ሲጠይቁኝ፤ «የሚያስፈልግ ነገር ካለ እናሟላለን!» ይላሉ። ለካ በሌሎች ስለሚጠየቁ እኔም የምጠይቃቸው መስሏቸው ነው።



መፍትሄ፦
①) በማይታወቅ ሰው ለተፖሰተ አፋልጉኝ ሳታጣሩ አትሰድቁ። የሚታወቅ ቢሆንም በደንብ የሚታመን መሆኑን እወቁ። በተለይ ኮሚሽን ባልኳችሁ ዘዴ በርካታ የምታውቋቸው ሰዎች ጭምር ይሠራሉ። ወላሂ! ብነግራችሁ ታፍራላችሁ። የማትጠብቁት ሰው ሁላ ተዘፍቆበታል።

*
②) በቀጥታ የታመመውን ሰው በብረት ዓይናችሁ ካላያችሁ ወይም ያዬ የምታምኑት ሰው ካልነገራችሁ በመኪና ለሚዞሩትም ቢሆን አትስጡ። የሆነ ፎቶ ስለተለጠፈ ወይም ታማሚ ተብሎ የሆነ ሰው መኪናው ውስጥ ስለተኛ ብቻ እውነት ነው ማለት አይደለም። አንዳንዱ እግሩን በጀሶ ጠግኖ በውሸት የታመመ መስሎ ተኝቶ የተጋለጠ አለ።
በዚህ መልኩ ለሕክምና ከሚያስፈልገው በላይም የሚያሰባስብ አለ። እንዳውም የሆነ ቀልድ ላይ «መኪናህን መታከሚያ ገንዘብ ላሰባስብበት አከራየኝ ያለህ ሰው፤ በሳምንቱ "ስንት ትሸጠዋለህ?" ሲልህ…!» የሚል አይቻለሁ። ሁሉንም አይመከትም።

በነዚህ አጭበርባሪዎች የተነሳ በትክክል መረዳት ያለባቸው እንዳይጎዱና መተማመን ጠፍቶ መጨካከን እንዳይመጣ፤ እያጣራን እንርዳ እላለሁ። ውስጣቸውን ሳይሰቀጥጠው የአሳዛኝ ታማሚ ሰውነ ገንዘብ የሚያጭበረብሩና በሐሰት የሚለምኑ ሰዎችንም አላህ ልቦናቸውን ለሐቅ ይክፍትላቸው።


ወንድማችሁ፦ ሙራድ ታደሰ
========
ኦገስት 20, 2024 G.C.
ሚያዚያ 12, 2016 E.C.
||
t.me/MuradTadesse