Get Mystery Box with random crypto!

እኔና የቆሎ ጓደኞቼ የአብነት መምህራችን መጋቤ ምሥጢር አለቃ መሠረት ተሰማን ቢያንስ በወር አንደዜ | መንፈሳዊ ግጥም ብቻ

እኔና የቆሎ ጓደኞቼ የአብነት መምህራችን መጋቤ ምሥጢር አለቃ መሠረት ተሰማን ቢያንስ በወር አንደዜ “ለምን መጽሐፍ አይጽፉም?” የሚል የልጅነት ቅንዓት ፣ ጉጉትና ምኞት የወለደው ሃሳብ በጉባኤ መሃል ወርወር ባደረግላቸው ቁጥር እንዲህ ብለው ይመልሱ ነበር።
“መጽሐፍ ልጻፍ ብል ቤት መቀመጥ ፣ መጻሕፍት ማገላበጥ ግድ ይሆናል። ይህ ደግሞ የእናንተን የትምህርት ጊዜ ይሻማል። ስለዚህ እኔ እናንተው ላይ መጻፉን መርጫለሁ። እናንተ ደግሞ መጽሐፉን ትጽፉታላችሁ።”
ይህ አነጋገራቸው “ሰዎች ሁሉ በሚያውቁትና በሚያነቡት በልባችን የተጻፈ መልእክታችን እናንተ ናችሁ። እናንተም በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በድንጋይ ጽላት ያልተጻፈ ፥ በእኛም የተገለገለ የክርስቶስ መልእክት እንደሆናችሁ የተገለጠ ነው።” የሚለው የቅዱስ ጳውሎስን ኃይለ ቃል ይመስላል።
እንዳሉትም እስከ መጨረሻይቱ ሕቅታ ድረስ አንድነትን ሦስትነትን ማመንን የሚያጸና ትምህርት እየጻፉ አረፉ። “መጽሐፉን እናንተ ትጽፉታላችሁ” የሚለው ትንቢትም ከዐሥር ዓመታት በፊት በበኩር የመንፈስ ልጃቸው በዲ/ን ዶ/ር አቤል ኃይሉ “የማእዘን ራስ” መጽሐፍ ተፈጽሟል። እነሆ አሁን ደግሞ የገዛ ብዕራቸው ውጤት “መጽሐፈ መሠረት” በሚል ርእስ ለኅትመት ብርሃን በቃ።

ይኼን መጽሐፍ የማዘጋጀት እድሌን አደንቃለሁ። ከፈቃደ እግዚአብሔር ጋር ይኼ ኃላፊነት ወደ እኔ እንዲመጣና እኔም በልዩ ትኩረት እንድፈጽመው ያደረጉኝ ክስተቶች ግን አሉ። በሕይወተ ሥጋ ሳይለዩን የአብነት ትምህርት የምስክር ወረቀት ከሰጧቸው የመጨረሻ ልጆቻቸው ማካከል አንዱ መሆኔ ፣ የመጨረሻ የጉባኤ ስብከታቸውን ያደግሁበትና በሰ/ት/ቤት አመራርነት ያገለገልኩበት ደብሬ ባዘጋጀው የኅዳር ሚካኤል ጉባኤ ላይ ጋብዣቸው ያስተማሩ መሆኑ ፣ በመጨረሻ በግል ሄጄ የተቀበልኩት የ”ዕዳ አለብህ” ቃላቸው ፣ የጊዜ ዕረፍታቸው የዓይን እማኝነት ዕጣ ከመንፈስ ልጆቻቸው መካከል እኔ ጋር የወደቀ መሆኑ በአጋጣሚ የሆነ አይመስለኝም።

ይልቁንም ዜና ሕይወታቸውንና ሥራዎቻቸውን ይዞ የወጣው የዳረጎት ልዩ ዕትም ዋና አዘጋጅ መሆኔ እኔ በግሌ ካሰባሰብኳቸው ሰነዶች በብዙ እጥፍ የሚበልጡ የልዩ ልዩ ዘመን አበርክቶአቸው እጄ እንዲገባ ምክንያት ሲሆን አንድ ላይ ሰብስቦ መጽሐፍ የማድረግ ሐሳብ ተፀነሰ። በፈቃደ እግዚአብሔርም እዚህ ደረሰ።

መጽሐፉ ሦስት አበይት ምእራፎች ያሉት ሲሆን በመጀመሪያው ምእራፍ ለኮርስ ስልጠና የተዘጋጁ ወጥ ሥራዎች ቀርበዋል። በሁለተኛው ምእራፍ በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ በጽሑፍ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በጽሑፍ የሰጡትን ምላሽ ይዟል። የመጨረሻው ምእራፍ የሕይወት ታሪክ አምድ ሆኖ የግላቸውን የጉባኤ ቤት ቆይታ በወፍ በረር ፣ ለስንክሣርና ግብረ ሕማማት መተርጉም ወዳጃቸው ለሊቀ መዘምራን ላእከ ማርያም ወልደ ኢየሱስ የጻፉትን በቅኔ የተዋዛ ጽሑፍ ፣ እንዲሁም ዜና ሕይወታ ለማርያም ድንግልን አካቷል።
በቅጽ አንድ የተካተቱት ሥራዎቻቸው ለኅትመት በሚበቃ ምሉዕነት ስለተገኙ ብቻ እንጂ በቀጣይ ተሟልተው የሚዘጋጁ ብዛት ያላቸው ርእሰ ጉዳዮች እንደሚኖሩ ይታወቅልኝ።
በተረፈ ስለ ብዕራቸው የሥነ ጽሑፍ ውበት ፣ የምሥጢር ጉልበትና የሐሳብ ፍሰት እየተነተኑ ሊቁን ለእናንተ ማስተዋወቁ አስፈላጊ አልመሰለኝም። “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” ይላልና ቃሉ ከፍሬያቸው ዕወቋቸው። የቻልኩትን ያህል ለቅሜ በያዛችሁት ቅርጫት አኑሬላችኋለሁ። የተባረከ ማዕድ ይሁላችሁ።
https://www.instagram.com/p/CqYPYpXIA4T/?igshid=MDJmNzVkMjY=