Get Mystery Box with random crypto!

#ጾመ_ነቢያት_ (#የገና_ጾም_) የ2014 ዓ.ም. የገና (የነቢያት) ጾም፤ ፠ #ጾሙ_ኅዳር_15_ | ትምህርተ ሃይማኖት ርትዕት

#ጾመ_ነቢያት_ (#የገና_ጾም_)
የ2014 ዓ.ም. የገና (የነቢያት) ጾም፤
፠ #ጾሙ_ኅዳር_15_ይጀምራል_!!
#Share

፠ ከ7ቱ አጽዋማት (ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ፍልሠታ፣ ጾመ ሐዋርያት፣ ጾመ ነቢያት፣ ጾመ ድኅነት፣ ጾመ ነነዌ ና ጾመ ገሃድ) መካከል አንዱ ነው፡፡
፠ ኅዳር 15 ቀን ተጀምሮ እስከ ልደት ዋዜማ ለአርባ ሦስት ቀናት የሚጾም ጾም ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን ለማዳን ሲል የሰውን ሥጋ ስለ መልበሱ፤ ወደ ግብጽ ስለ መሰደዱ፤ በባሕረ ዮርዳኖስ ስለ መጠመቁ፤ በትምህርቱ ብርሃንነት ጨለማውን ዓለም ስለ ማብራቱ፤ ለሰው ልጆች ድኅነት ልዩ ልዩ መከራን ስለ መቀበሉ፤ ስለ መሰቀሉ፣ ስለ ሞቱ፣ ትንሣኤው፣ ዕርገቱና ዳግም ምጽአቱ በየዘመናቱ የተነሡ ቅዱሳን ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው ትንቢት ተናግረዋል፤ ትንቢቱ ደርሶ፣ ተፈጽሞ ለመመልከትም ‹‹አንሥእ ኃይለከ ፈኑ እዴከ፤ ኃይልህን አንሣ፤ እጅህን ላክ›› እያሉ በጾም በጸሎት ተወስነው አምላክ ሰው የሚኾንበትን ጊዜ በቀናት፣ በሳምንታት፣ በወራትና በዓመታት እያሰሉ ሲጠባበቁ ቆይተዋል፡፡
፠ ይህንን ጾም በዘመነ ብሉይና በዘመነ ሐዲስ ብዙ ቅዱሳን ጾመውታል፤ በዚህም ምክንያት የሚከተሉት ስያሜዎች አሉት፡፡
እነርሱም፤
† ፩. #ጾመ_አዳም_፤ አዳም ዕፀ በለስን በልቶ ከገት ከተባረረ በኋላ; በፈጸመው በደል አዝኖ ፥ ተክዞ፤ አለቀሰ (እንባ ቢያልቅበት እዥ እስከሚያፈስ፤ እዥ ቢያልቅበት ደም በዓይኑ እስከሚፈስና ዓይኑ ይቡስ ወይም ደረቅ እስከሚሆን ድረስ አለቀሰ) ፥ ጾመ፣ ጸለየ፡፡ ከልብ የሆነ ጸጸቱን፣ ዕንባውን፣ በራሱ መፍረዱንም እግዚአብሔር አይቶ ተስፋ ድኅነት ሰጠው፡፡ ‹‹ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ፣ በደጅህ ድኼ፣ በዕፀ መስቀል ተሰቅዬ፣ ሞቼ አድንሃለሁ፡፡›› የሚል ነው፡፡ /ገላ. ፬፥፬፣ መጽ.ቀሌምንጦስ/ ስለዚህ ጾሙ የተሰጠው ተስፋ ፥ የተቆጠረው ሱባኤ ስለተፈጸመበት ‹‹ጾመ አዳም›› ይባላል፡፡

† ፪. #ጾመ_ነቢያት_፤ ነቢያትም የምሥጢረ ሥጋዌ ነገር ተገለጦ ስለታያቸው፣ ክርስቶስ ለሰው ልጅ የሚከፍለውን የፍቅር ዋጋ በትንቢት ተመልክተው ጾመውታልና ጾመ ነቢያት ይባላል፡፡ ይህ ጾም ከአባታችን አዳም እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ድረስ የተነሱ አበውና እናቶች: ድኅነትንና ረድኤትን ሲሹ የጾሙት ጾም ነው:: በተለይ አባታችን አዳም: ቅዱስ ሙሴ: ቅዱስ ኤልያስ፣ ቅዱስ ዳንኤል ና ቅዱስ ዳዊት በጾማቸው የተመሰከረላቸው ቅዱሳን ናቸው:: (ዘዳ 9:19, ነገ. 19:8, ዳን. 9:3፣ መዝ. 68:10, 108:24) ቅዱሳን ነቢያት በጭንቅ በመከራ ሆነው የጾሙት ጾም ወደ መንበረ ጸባኦት ደርሶ: ወልድን ከዙፋኑ ስቦታል:: ለሞትም አብቅቶታል::

† ፫. #ጾመ_ሐዋርያት_፤ ሐዋርያት ‹‹ትንሣኤን ዐቢይ ጾምን ጾመን እናከብራለን፣ ልደትን ምን ሥራ ሠርተን እናከብረዋለን?›› ብለው ከልደተ ክርስቶስ በፊት ያሉትን ፵፫ ዕለታት ጾመዋልና፡፡
† ፬. #ጾመ_ማርያም_፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር አምላክ ቅድስናዋን አይቶ በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ወልደ አምላክን ያለ ሰስሎተ ድንግልና በግብረ መንፈስ ቅዱስ ጸንሳ እንደምትወልደው ቢነግራትም የትሕትና እናት ናትና ‹‹ምን ሠርቼ የሰማይና ምድርን ፈጣሪ እችለዋለሁ?›› ብላ ጌታን ከመውለዷ አስቀድማ ጾማለችና ‹‹ጾመ ማርያም›› ይባላል፡፡

† ፭. #ጾመ_ፊልጶስ_፤ ሐዋርያው ፊልጶስ በአረማውያን ዘንድ ገብቶ እያስተማረ ሳለ በሰማዕትነት ሲሞት፤ አስክሬኑ ከደቀመዛሙርቱ ስለተሰወረ፤ እግዚአብሔር የተሰወረውን የመምህራቸውን አስክሬን እንዲገለጽላቸው ከኅዳር ፲፮ ጀምረው ጾመው በሦስተኛው ቀን የመምህራቸው አስክሬን ተመልሶላቸዋል፤ ነገር ግን አስከሬኑ ቢመለስላቸውም ጾሙን ግን እስከ ልደት ቀጥለዋል፡፡

† ፮. #ጾመ_ስብከት_፤ የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን ያስተማሩበት፥ የሰው ልጆች ተስፋ የተመሰከረበት፥ የምስራች የተነገረበት ስለሆነ ጾመ ስብከትም ይባላል፡፡

† ፯. #ጾመ_ልደት_፤ የጾሙ መጨረሻ (መፍቻ) በዓለ ልደት ስለሆነ ‹‹ጾመ ልደት›› ይባላል፡፡

   ጾምን ትእዛዝ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን የፍቅርና የበረከት ምንጭ በመሆኑ ጭምር ደስ እያለን ብንጾመው የቅዱሳኑ በረከት ያድርብናል፡፡
ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት በረከት እንዲያሳትፈን፤ መንግሥቱንም እንዲያወርሰን ዅላችንም በዚህ በጾመ ነቢያት ወቅት በጾም በጸሎት ተወስነን እግዚአብሔርን ልንማጸነው ይገባል፡፡

ኦርቶዶክሳዊ ወንድሞች ሆይ ለኦርቶዶክሳዊ ወንድምዎ ሼር በማድረግ የቤተክርስቲያናችንን ቀጥተኛ ትምህርት ያሳውቁ ይመስክሩ ።


@meskal
@meskal
@meskal