Get Mystery Box with random crypto!

በስመአብ  ወወልድ  ወመንፈስ ቅዱስ  አሃዱ  አምላክ  አሜን [ኅዳር 8 የእግዚአብሔርን ዙፋን የ | ትምህርተ ሃይማኖት ርትዕት

በስመአብ  ወወልድ  ወመንፈስ ቅዱስ  አሃዱ  አምላክ  አሜን

[ኅዳር 8 የእግዚአብሔርን ዙፋን የሚሸከሙ የኪሩቤልና የሱራፌል ዓመታዊ በዓል፤ ክብራቸውና ስማቸው]

 ክብራቸው ታላቅ የኾኑት የኪሩቤልን ነገር ሊቁ ኤጲፋንዮስ “ወለዳግም ጾታ ዐሠርቱ ስሞሙ ኪሩቤል ካህናተ ቅዳሴ ወውዳሴ እምታሕተ ሐቌሆሙ አሐዱ ወእምላዕለ ሐቌሆሙ አርባዕቱ እለ ግሉፋን በአዕይንት” ብሎ  እንደገለጸው ኹለተኞቹ አመስጋኞች የኾኑት ዐሥሩን ነገድ ስማቸው ኪሩቤል ሲባሉ ከወገባቸው በታች አንድ ከወገባቸው በላይ አራት አድርጎ ሲፈጥራቸው ዐይናቸው ብዙ ነው፤ አለቃቸውም ኪሩብ ሲኾን የሰው መልክና የአንበሳ መልክ ያለው ነው፡፡

❖ ሦስተኛውን ዐሥሩን ነገድ ስማቸው ሱራፌል ሲባል የእነዚኽ አለቃቸው የንስር መልክና የእንስሳ መልክ ያለው ነው፤ አለቃቸውም ሱራፊ ሲባል ሲፈጥራቸውም ስድስት ስድስት ክንፍ አድርጎ ፈጥሯቸዋል፨

❖ ልዑል እግዚአብሔር ከነገደ ኪሩቤል ኹለት ገጸ ሰብእ እና ገጸ አንበሳን፤ ከሱራፌል ኹለት ገጸ ንስርና ገጸ እንስሳን አንሥቶ ከኢየሩሳሌም ሰማያዊት በላይ ከሰማይ ውዱድ በታች አቁሞ በነርሱ ላይ ሰማይ ውዱድን እንደ መረሻት ጫነባቸው፤ በላይም ሕብሩ በረድ የመሰለውን ዙፋን እንደ ሠረገላ ጭኖባቸዋል፤ እነዚኽንም በምሥራቅ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን፣ በደቡብ በአራቱ መኣዝን ዠርባቸውን ወደ ውስጥ ፊታቸውን ወደ ውጪ እያደረገ አቁሟቸዋል።

❖ነቢዩ ሕዝቅኤል ስለዚኽ ነገር በምዕ ፩፥፲፪ ላይ “እያንዳንዱም ወደ ፊት ቀጥ ብሎ ይኼድ ነበር መንፈስም ወደሚኼድበት ኹሉ ይኼዱ ነበር ሲኼዱም አይገላመጡም ነበር” በማለት እንደተናገረ ገጽ ለገጽ ሳይተያዩ ሥላሴ በፈቀዱት ፍኖት አንዱ በኼደበት ሦስቱ እየተከታተሉ ይኼዳሉ፡፡

❖ እነዚኽንም እንደ ነቢዩ ሕዝቅኤል ገለጻ ፲፮ ሲኾኑ የቀሩት ከውስጥ ስለኾኑ ስለማይታዩ አራቱ ግን ብቅ ብቅ ብለው ስለሚታዩ ዮሐንስ አራት ብሏቸዋል እንጂ እንደ ሕዝቅኤል ገጻቸው ፲፮ ነው ይላሉ መተርጉማን፡፡

❖  ሊቁ “እምርእሶሙ እስከ ሐቌሆሙ አርባዕቱ ወእምሐቌሆሙ እስከ እግሮሙ አሐዱ ከመ ርእየተ እለ ቄጥሩ ዘውእቱ ዖፍ ዘይነብር በሀገረ ፋርስ” እንዲላቸው፤ ሊቁ ቅዱስ ያሬድም “ከመ ርእየተ እለቄጥሩ ገጸ በገጽ ኢይትናጸሩ” ብሎ እንደገለጻቸው በፋርስ ሀገር የሚኖረው እለቄጥሩ የተባለውን ዎፍ ከወገቡ በታች አንድ ከወገቡ በላይ አራት እንደኾነ እነዚኽንም ከወገባቸው በታች አንድ ከወገባቸው በላይ አራት አድርጎ ፈጥሯቸዋል ፡፡

❖ ኪሩቤልን “እለ ብዙኃት አዕይንቲሆሙ” አላቸው፤ ከላይ እስከ ታች ድረስ ዐይንን የተመሉ ናቸውና፤ ይኽስ አይደለም እንደ ብርሌ እንደ ብርጭቆ እያብለጨለጨ ለዐይን ባልተመቸም ነበር ብሎ ዐልፎ ዐይን ዐልፎ ዐይን ነው፤ እንደ አልጋ መለበሚያ እንደ ሱቲ መጠብር እንደ ቀሽመሪ መታጠቂያ፣ እንደ ነብር ለምድ፣ እንደ ዐይነ በጎ፣ እንደ ማር ሰፈፍ ይላሉ፤ ይኽስ አይደለም ብሎ ዐይናቸው ከአንገታቸው በላይ ሰድ ነው፤ ይኽም እንደ መስታዮት እያወለወለ እንደ ብርጭቆ እያንጸበረቀ አይደለም ብሎ ኀላፍያትን መጻእያትን የሚያውቁ ስለኾነ እንዲኽ አለ እንጂ ዐይናቸውስ ኹለት ነው ይላሉ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቀደምት መተርጉማን ፡፡

❖ በኢሳ ፮፥፩-፫ ላይ፡- “ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረዥምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየኹት የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን መልቶት ነበር፤ ሱራፌልም ከርሱ በላይ ቆመው ነበር ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው በኹለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር በኹለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር በኹለቱም ክንፍ ይበር ነበር፤ አንዱም ለአንዱ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ኹሉ ከክብሩ ተመልታለች እያለ ይጮኽ ነበር” ይላል ይኽ መሸፈናቸው ያድናቸዋል ቢሉ? ትእምርተ ፍርሀት ነው፤ ዛሬ በዚኽ ዓለም ሴቶችን ሕፃናትን እንመታችኋለን ባሏቸው ጊዜ እጃቸውን መጋረዳቸው የሚያድናቸው ኾኖ ሳይኾን ትእምርተ ፍርሀት እንደኾነ ኹሉ፡፡

አንድም በኹለት ክንፋቸው ፊታቸውን መሸፈናቸው ፊትኽን ማየት አይቻለንም ሲሉ በኹለት ክንፋቸው እግራቸውን መሸፈናቸው ከፊትኽ መቆም አይቻለንም ሲሉ፤ ኹለት ክንፋቸውን ወዲያና ወዲኽ ያደርጋሉ አለ ትእምርተ ተልእኮ ነው፡፡

አንድም በኹለት ክንፋቸው ፊታቸውን መሸፈናቸው ባሕርይኽን መመርመር አይቻለንም ሲሉ፤ በኹለት ክንፋቸው እግራቸውን መሸፈናቸው ባሕርይኽን መረማመድ መተላለፍ አይቻለንም ሲሉ፤ ኹለት ክንፋቸውን ወዲያ ወዲኽ ያደርጋሉ ከእእምሮ ወደ አእምሮ ለመፋለሳቸው፡፡

 አንድም ኹለት ክንፋቸውን ወደ ላይ አድርገው ይታያሉ አለ ወደላይ ቢወጡ ቢወጡ አትገኝም ሲሉ፤ ኹለት ክንፋቸውን ወደታች አድርገው ይታያሉ ወደታች ቢወርዱ ቢወርዱ አትገኝም ሲሉ፤ ክንፋቸውን ወዲያና ወዲኽ ያደርጋሉ ወዲያና ወዲኽ ቢሉ አትገኝም ሲሉ፤

አንድም ወደላይ መዘርጋት በሰማይ ምሉእ ነኽ ሲሉ ወደታች መዘርጋቸው በምድርም ምሉእ ነኽ ሲሉ፤ ወዲያና ወዲኽ መዘርጋታቸው በኹሉ ምሉእ ነኽ ማለታቸው ነው፤

አንድም ወደላይ መዘርጋት ትእምርተ ተመስጦ ወደታች መዘርጋት ትእምርተ ትሕትና፤ ወዲያና ወዲኽ ረብቦ መታየት ትእምርተ ተልእኮ ነው

❖ በአጠቃላይ ኹለት ክንፋቸውን ወደላይ ኹለት ክንፋቸውን ወደታች ኹለት ክንፋቸውን ወዲያና ወዲኽ አድርገው ትእምርተ መስቀል መሥራታቸው በብሉይ ኪዳን ከኾነ እንዲኽ ባለ መስቀል ተሰቅለኽ ዓለምን ታድነዋለኽ ሲሉ በዘመነ ሐዲስ የኾነ እንደኾነ እንዲኽ ባለ ትእምርተ መስቀል ተሰቅለኽ ዓለምን አድነኸዋል ሲሉ ነው፡፡

❖  የእነዚኽ አርባዕቱ እንስሳ መላእክት ፊታቸው በርካታ ምስጢራትን ሲያመለክቱ ገጸ ሰብእ በማቴዎስ፤ ገጸ አንበሳ በማርቆስ፤ ገጸ ላሕም በሉቃስ፤ ገጸ ንስር በዮሐንስ ተመስሏል።

❖  በሌላ ምስጢር የሰው ገጽ ያለው የጌታን ሰው የመኾንን ነገር፤ የላም መልክ ያለው በቀራንዮ ላይ ደሙን ማፍሰሱ፤ የአንበሳው መልክ ያለው የጌታችንን ትንሣኤ፤ የንስር መልክ ያለው የጌታን ዕርገት እንደሚያመለክቱ ቀደምት መተርጒማን ይተነትኑታል።

❖ዐምደ ሃይማኖት አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም እጅግ ምጡቅ በኾነው ዕውቀቱ ዕጓለ አንበሳ የተባለው የወልድ የባሕርይ አባቱን አብን በአንበሳ ይመስለዋል።

❖ሥጋን ተውሕዶ ፍጹም ሰው የኾነው ወልድን የሰው መልክ ባለው መስሎ ገልጾታል፡፡

❖ በአምሳለ ርግብ ወርዶ በወልድ ራስ ላይ ተቀምጦ የታየው መንፈስ ቅዱስን የንስር መልክ ባለው መስሎ አብራርቶ ጽፎታል።

❖በቀንዱ የማይበራታ ላሕም ተብሎ የተመሰገነው የወልደ እግዚአብሔር ቅዱስ ሥጋው የሚፈትትባት፤ ክቡር ደሙ የሚቀዳባት በአራቱ ኪሩቤል አምሳል አራት መአዝን ያላት ቤተ ክርስቲያንን በገጸ ላሕም አምሳል ገልጦ በተአምኆ ቅዱሳን ላይ ስማቸውን በመጥቀስ ሲያወድሳቸው፦

[“ሰላም ለ፬ እንስሳሁ ለአብ እለ ይጸውሩ መንበሮ እለ ስሞሙ አግርሜስ ገጸ አንበሳ፡፡ አግርሜጥር ገጸ ሰብእ፡፡ ባርቲና ገጸ ላሕም፡፡ አርጣን ገጸ ንስር፡፡ ለቀዳማዊ ገጹ ከመ አንበሳ፤ በአምሳለ ፈጣሪሁ ዘውእቱ አብ፡፡ ለካልዕ ገጹ ከመ ሰብእ በአምሳለ ወልድ፤ ዘውእቱ ነሥአ ፍጹመ ስባኤ፡፡ ለሣልስ ገጹ ከመ ንስር በአምሳለ መንፈስ ቅዱስ ዘውእቱ አስተርአየ በርእየተ ርግብ በሥጋ፡፡ ወለራብእ ገጹ ከመ ላሕም በአምሳለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፤ እስመ ፬ቱ መኣዝኒሃ”፡፡]

(የአብ ዙፋኑን ለሚሸከሙና ስማቸውም የአንበሳ መልክ ያለው አግርሜስ፤ የሰው መልክ ያለው አግርሜጥር፤ የላም መልክ ያለው ባርቲና፤ የንስር መልክ ያለው አርጣን ለተባሉ ለአራቱ እንስሳ ሰላምታ ይገባል፤

@meskal