Get Mystery Box with random crypto!

አንድ ሃሳብ! ፨፨//////፨፨ የተዘጋውን በር ለመክፈት፣ ከባዱን ጉዞ ለማቅለል፣ እርምጃን ለማፍጠ | Mental Counsel ETH | ምክረ-አዕምሮ™

አንድ ሃሳብ!
፨፨//////፨፨
የተዘጋውን በር ለመክፈት፣ ከባዱን ጉዞ ለማቅለል፣ እርምጃን ለማፍጠን፣ ህይወትን ለመቀየር፣ እድገትን ለማምጣት አንድ ጠንካና ግልፅ ሃሳብ በቂ ነው። እስከ ዛሬ ከመጡልን ድንቅ ሃሳቦች አንዱን እንኳን ብንተገብረው የት ነበርን? አንዱን የተለየ መንገድ ብንከተል የት በደረስን? መቼም የዛሬ ስፍራችን እንደማንሆን ግልፅ ነው። መጥተው የጠፉ አስደናቂ ሃሳቦችህን አስታውስ፤ ሳትይዛቸው ያመለጡህን አዳዲስ እይታዎች ወደኋላ ቃኛቸው። ምናልባትም ምንጫቸውን ዳግም ብታገኘው እነርሱንም ልታገኛቸው እንደምትችል አስብ። ሁላችንም ያልኖርናቸው እጅግ በጣም ብዙ ሃሳቦች ይኖሩናል። የትናንት ያይደሉ፣ የነገም ያልሆኑ፣ የዛሬና የአሁን የሆኑ እጅግ ብዙ ሃሳቦች አሉን። ምናልባትም ቢተገበሩ በብዙ መልኩ ህይወታችንን አቅጣጫ ሊያስይዙልን የሚችሉ ይሆናሉ።

አዎ! ጀግናዬ..! አንድ ሃሳብ በቂህ ነው፤ አንድ የሚኖር፣ ምድር ላይ የሚወርድ፣ የሚተገበር ጠንካራ ሃሳብ ፍፁም የተለየውን ህይወት የመስጠት ሃይል አለው። አለም የተቀየረችው ከሃሳብ ከተነሱ ጥቃቅን ተግባሮች ነውና የሚመጡልህን ሃሳቦች ችላ አትበላቸው። ቅዠት ቢመስሉህም እንኳን በተቻለህ መጠን ትኩረት ሰተህ ለማዳመጥ ሞክር፤ በአቅምህ ልክም አዎንታዊነታቸውን በማረጋገጥ ወደ ምደር ለማውረድ ተንቀሳቀስ። ብዙዎቻችን የሃሳብ ችግር የለብንም፣ እንደውም የሃሳቦች ሀብታም ነን። ነገር ግን እነዚህን ሃሳቦች ለመኖር በብዙ እንቸገራለን። ከአንድ በላይ ሃሳብ ይዘን ከአንዱ ሃሳብ ያነሰ ህይወት ስንኖር እንገኛለን። የህይወት ሚስጥርህ የሚፈታው ከማትተገብራቸው ሃሳብ ጋር በመታገል ሳይሆን ትንሽም ቢሆን እነዛኑ ሃሳቦች ስራ ላይ በማዋል ነው።

አዎ! ለዓመታት ያልተፋታህ፣ ዘወትር ደጋግሞ የሚመጣብህ ህይወትህን ቀያሪና ወደፊት አራማጅ ሃሳብ ካለህ ጨክነህ ትገበራውን ጀምረው፤ እንደምንም ብለህ የሚከወንበትን መንገድ ፈልግ። ከእራስህ በላይ ለብዙዎች የሚተርፍ ትልቅ ሃሳብ ይዘህ እስከመቼ እንደ መደበኛ ሰው ለማሟያነት ታገለግላለህ? ከማንም ያላነሰ እውቀት እያለህ እስከመቼ የማይመጥንህን ህይወት ተኖራለህ? የፈጠራህ አቅም የላቀ ሆኖ እስከመቼ የጥቃቅን ተግባሮች አድናቂ ሆነህ ትቀራለህ? የሃሳብህ ግዝፈት፣ ቅዠት መምሰሉና መወሳሰቡ ካስፈራህ በእርግጥም ትክክለኛው ሃሳብ እርሱ ነውና ጊዜ ሰተህ ደጋግመህ በጥሞና አስበው፤ አሰላስለው። አንዷ ሃሳብህ ተግባር ላይ ስትውል የዛሬ ህይወትህን ታሪክ የማድረግ አቅም እንደሚኖራት ጠንቅቀህ እወቅ። ከሃሳብ ይልቅ የሚያኮራው ተግባር ነውና፣ ከባዶ እውቀት ይልቅ አትራፊው የሚኖር እውቀት ነውና ሃሳብህን በተግባር፣ እውቀትህንም በስራ ግለፀው።
ውብ ምሽት ይሁንልን!
ምክረ-አዕምሮ ለተሻለ ነገ!

YouTube አማራጭ ይቀላቀሉን!
SUBSCRIBE NOW
https://www.youtube.com/channel/UCIZv4h3iDx2C7CGbv9WIkVg?sub_confirmation=1
ምክረ-አዕምሮ/ @MentalCounsel