Get Mystery Box with random crypto!

'ፍትወት ያጠፍኦ ለሂሩት፤ ፍላጎት ቸርነትን ያጠፋል' (መጽሐፈ ገነት) ፈተወ ማለት ፈለገ፣ ወደ | መንፈሳዊ የህይወት ምክር

"ፍትወት ያጠፍኦ ለሂሩት፤ ፍላጎት ቸርነትን ያጠፋል" (መጽሐፈ ገነት)

ፈተወ ማለት ፈለገ፣ ወደደ፣ ከጀለ፣ ተመኘ፣ ጎመጀ የሚሉ ፍካሪያት ያለው ቃል ነው። ነገሩ ክፉና ደግ የሚሆነው ግን በአስደራጊ፣ በአድራጊ፣ በአደራራጊ፣ በተደራጊ፣ በድርጊት ነው። ለምሳሌ፦ ፍላጎቱ፣ ምኞቱ፣ ውዴታው፣ እግዚአብሔርን ማየት ከሆነ አስመኝው ራሱ እግዚአብሔር ነው። ተመኝውም መልአክ ነው፣ አብርሃም ነው። መመኛው ሃይማኖት ነው ምኞቱም ሥላሴ፣ ድርጊቱም ጽድቅ ነው፣ ዋጋውም መገለጥ ነው። (አብርሃም አባታችሁ ቀኔን ሊያይ ተመኘ አይቶም ደስ አለው) "መላእክትን የሚያስመኛቸው" እንዲል።
አስመኚው ሰይጣን፣ መመኛው ልብ ጠዋይ፣ ክህደት፣ ፈቃደ ሥጋ፣ ፍቅረ ሢመት፣ ትካዘ ዓለም፣ ሀልዮ መንበር፣ ፍቅረ ዉሉድ፣ ብእሲት ወዘመድ፤ ምኞቱም ሹመት ብዕል ድሎት በጥቅሉ የዓለም የልዕልና ማማ ላይ መውጣት የሆነ ጊዜ ግን "እፎ መልዐ ሰይጣን ውስተ ልብከ፤ ሰይጣን በልብህ ስለምን ሞላ?" የሚያስብል ቅዱሳንን ወደ ታች የሚያስደምም ርኩሰት ይሆናል። የሐ.ሥራ ፭፥፬ እንዲህ ያለው ምኞት ነው ቸርነትን የሚያጠፋ የተባለው።

ሰው ሁሉ ቸርነትን አቡሃ ለምሕረት ከሆኑ ከሥላሴ ዘንድ ይሻል። ምሕረትን የሚያገኙ ደግሞ ምሕረትን የሚያደርጉ ናቸው። "ብፁዓን መሐርያን እስመ ሎሙኒ ይምሕርዎሙ፤ የሚምሩ ብፁዓን ናቸው ይማራሉና" እንዲል። ማቴ. ፭፥፯
ይህ ሳይሆን እነርሱ እየጨከኑ ምሕረት የሚፈልጉ ግን አስደራጊው ሰይጣን ምኞቱ ምሕረት ማድረጊያው ጭካኔ ስለሆነ ፍየል ምሥራቅ ምዝግዝግ ምዕራብ መሆኑ ነው። መድኃኒትን በመርዝ መጠጣት እድን ብሎ ቢጠጡት ማዳኑንስ ቀርቶ መግደሉ ይብስ። የሥላሴን ቸርነት እየፈለጉ መጨከንም ማስማሩ ቀርቶ ያስፈርዳል። ወዲህም ጭካኔ የዲያብሎስ ምሕረት የእግዚአብሔር ስለሆነ ከሰይጣን ተነስቶ ወደ እግዚአብሔር ከመቼ ዕለት ወዲህ ተደርሶ ያውቃል? "እምኀበ እግዚአብሔር ይጸንዕ ሑረቱ ለሰብእ የሰው መንገዱ ከእግዚአብሔር የሆነ እንደሆነ ይቀናል" ተብሎ ነውና የተጻፈው። መዝ. ፴፮፥፴፬

ወንድሞቼ ሆይ ሞሕረትን የምንፈልግ ከሆነ ምሕረት ይኑረን። ምሕረትንም ለማድረግ ፍላጎታችን እንጠብቅ። ፍላጎት ምሕረትን ይደመስሳልና። የቀደመው ጠላት ምሕረት አጥቶ የቀረው ምሕረት የለሽ ስለሆነ ነው። ምሕረት የለሽ ያደረገውም ፍላጎቱ ነው። የማይገባውን አምላክነት ተመኘ፤ በክህደት ተመኘ፤ ክፋ ፍላጎቱ በአምላኩ ላይስ እንኳ ጨክኖ አምላክ ነኝ አስባለው። ስለዚህ ምሕረት ያልተገባው ሆነ። ይሁዳ በጌታው ላይ ለመሸጥ ያስጨከነው ክፉ የገንዘብ ፍላጎቱ። ጸሐፍት ጌታን ለመስቀል እንጀራ አበርክተው ያበሏቸውን እጆች ለመቸንከር የጨከኑት ክብርና የሥልጣን ፍላጎት ነው። ሄሮድስ በእናታቸው ወተት ቤተልሔም እስክትነጣ፣ በሕጻናቱ ደም እስክትቀላ እነዚያን ሕጻናት ያረዳቸው ያለ ሽረት ከመግዛት ክፉ መጎምጀት ነው። ኮቲባ ለድንግል ለምን ውኃ አልሰጥም አለች? ቅናቷና ስስቷ ነው።

ዛሬም ደም የሚያስፈስስ እኔ ብቻ ልኑር ነው። በሚያለቅሱና እንባን ከማሩኝታ ጋር በሚያቀርቡ ዓይኖች ላይ የሚጨክኑ ሾተል የሚመዙ እጆች ደም የተቀባን እንጀራ መጥገብ የሚልጉ ክፋ ልቦች ያበቀሏቸው ናቸው። በትዳራቸው ላይ የሚደፍሩ ለትዳራቸው ምሕረት የሌላቸው "በቃ ይበተን" የሚሉ ክፉ ምኞት የሚገረኛቸው ናቸው። በርህርኂቷ እመቤት፣ በጽድልቷ ንግሥት፣ በወላዲተ አምላክ ጨክነው ከልባቸው አሰድደው የሚሰድቧት የዛሬ ሄሮድሶችም እኔ ልክበር ልበልጽግ ልብላ ከሚል ምቀኛ ልብ የሚወጣ አሳባቸው ነው። አባቶቻችን የሚገባን መመኘት ጠቢብነት ነው የማያገኙትን ሁሉ መመኘት ግን ምቀኝነት ነው ይላሉ። ሰው በድንግል ማርያም ቢቀና እኔም እኮ ከእርሷ ጋር እኩል ነኝ ቢል አምላክን መውለድ አይችልምና አጉል ምቀኝነት ሆኖ ይቀራል።

ሄሮድስ የማይተካከለውን እገላለሁ ብሎ ሕጻናትን እንደገደለ ዛሬም እመቤታችንን ከልባቸው አሰድደው በአእምሮ ሕጻናት የሆኑትን የቤተልሔም እርሷ ልጆችን በምንፍቅና ሾተል ያርዳሉ።
ሄሮድስ እመቤታችንን በእኩይ ፍላጎቱ በርኩስ ቅናቱ አሰድዶ ሞተ። ወዳጄ ቅናትና ምቀኝነት እናታችን ከልባችን አንዳያሰድብን እንጠንቀቅ። ስለረከሱ ሕልሞች ስለሚጣፍጡ የሐኬት እንቅልፎች ውዳሴዋን አቋርጠን የምሕረትን ጠል ያዘለችውን ደመና ከእኛ እንዳትሰደድ እንንቃ። ለሄሮድስ መሰለው እንጂ ርግቢቱስ ገላግልቷን ይዛ በበረሃ ጉያ ውስጥ መዐዛዋን እያወደች ነው። ስለ ክፉ ምኞታቸው ሰማይን ከነ ፀሐይዋ አሳድደው ለጨለሙ ሄሮድሶች ይብላኝ እንጂ እርሷስ በየገዳማቱ "ምስለ ወልድኪ ልዑል በዘባንኪ ኅዙል ጎየይኪ እፎ ድንግል ደወል እምደወል" እየተባለች ትወደሳለች። ብቻ ዘመዶቼ በአንድ በጎ ነገር ላይ "አይ ይቅርብኝ" የሚያስብል አሳብ በመጣ ጊዜ የሰይጣን እንደሆነ አስተውሉ። ለቅዱስ ምኞት ያብቃን!!!
( መጋቤ ሐዲስ ወብሉይ አባ ገብረ ኪዳን ግርማ)