Get Mystery Box with random crypto!

ሰኔ 24 - '#ቅዱስ_ሙሴ_ጸሊም_(#ጥቁሩ_ሙሴ) ግብጻውያን ስማቸውን ጠርተው ከማይጠግቧቸው ቅዱሳ | ዲያቆን ዳንኤል ወንድሙ ቻ

ሰኔ 24 - "#ቅዱስ_ሙሴ_ጸሊም_(#ጥቁሩ_ሙሴ)
ግብጻውያን ስማቸውን ጠርተው ከማይጠግቧቸው ቅዱሳን መካከል አንዱ ኢትዮዽያዊው አባ ሙሴ ጸሊም ነው:: በእኛ ኢትዮዽያውያን ግን ይቅርና በወርኀዊ በዓሉ በ24 በዓመታዊ በዓሉ እንኩዋ ሲከበር ብዙም አይታይም::
°°°
ቅዱሱ ሰው በትውልዱ ኢትዮዽያዊ ሲሆን፣ ያደገውም እዚሁ ሀገራችን ውስጥ እንደሆነ ይታመናል:: ገና በወጣትነቱ አገር የሚያሸብር ሽፍታ ነበር:: ሙሴ ጸሊም ወደ ግብጽ የሔደበት ምክንያት በግልጽ ባይታወቅም መምለክያነ ጣዖት (ፀሐይን ከሚያመልኩ ሰዎች) ጋር ይኖር ስለ ነበር። ምናልባት እነርሱ ወስደውት ሊሆን ይችላል::
°°°
ቅዱስ ሙሴ በምድረ ግብጽም በኃይለኝነቱ ምክንያት የሚደፍረው አልነበረም:: ፀሐይን ያመልካል: እንደ ፈለገ ቀምቶ ይበላል: ያሻውን ሰው ይደበድባል:: ነገር ግን በኅሊናው ስለ እውነተኛው አምላክ ይመራመር ነበርና አንድ ቀን ፀሐይን "አምላክ ከሆንሽ አናግሪኝ?" አላት:: እርሷ ፍጡር ናትና ዝም አለችው::
°°°
ቅዱስ ሙሴ ምንም አስቸጋሪ ሰው ቢሆንም ፈጣሪን መፈለጉን ግን ቀጥሏልና አንድ ቀን ተሳካለት:: መልካም ክርስቲያኖችን አግኝቶ . . . ወደ ገዳመ አስቄጥስ ቢሄድ በዛ ያሉ መነኮሳት ወደ እውነት እንደሚመሩት ነገሩት:: እርሱም ሰይፉን እንደታጠቀ ወደ ገዳም ገባ:: መነኮሳቱ ፈርተውት ሲሸሹ ታላቁ አባ ኤስድሮስ ግን ተቀብለው አሳረፉት::
°°°
"ምን ፈለግህ ልጄ?" አሉት:: "እውነተኛውን አምላክ ፊት ለፊት ማየት እፈልጋለሁ" የሙሴ ጸሊም መልስ ነበር:: አባ ኤስድሮስም "የማዝህን ሁሉ ካደረግህ ታየዋለህ" ብለው ወደ መነኮሳት አለቃ ቅዱስ መቃርስ ታላቁ ወሰዱት:: መቃሬም ክርስትናን አስተምረው አጠመቁትና ለአባ ኤስድሮስ መለሱላቸው::
°°°
ከዚህ ሰዓት በኋላ ነበር የአባ ሙሴ ጸሊም ሕይወት ፍጹም የተለወጠው:: በጻድቁ እጅ ምንኩስናን ተቀብሎ ይጋደል ጀመር:: በጠባቧ በር ይገባ ዘንድ ወዷልና ያ በሽፍትነት የሞላ አካሉን በገድል አረገፈው:: ከቁመቱ በቀር ከአካሉ አልተረፈለትም:: ወገቡን በአጭር ታጥቆ መነኮሳትን አገለገለ:: አጋንንት በቀደመ ሕይወቱ በሕልም: አንዳንዴም በአካል እየመጡ ይፈትኑት ነበር::
°°°
እንዳልቻሉት ሲረዱ ተሰብስበው መጥተው በእሳት አለንጋ ገርፈው አቆሳስለውት ሔዱ:: እርሱ ግን ታገሰ:: በበርሃ ለሚኖሩ አበው መነኮሳት ሁሉ ብርሃን በሆነ ሕይወቱ ሞገስ ሆነላቸው:: ለኃጥአን ደግሞ መጽናኛ ሆነ:: በተራራ ላይ ያለች ሀገር ልትሠወር አይቻላትምና ስም አጠራሩ በመላው ዓለም ተሰማ:: ሁሉም "ሙሴ ጸሊም ይል ጀመር ፡፡"
°°°
በየበርሃው ያሉ አበው ብቻ ሳይሆነ ዓለማውያን መኳንንት ሳይቀሩ ሊያዩት ይመኙ ነበር:: እርሱ ግን ራሱን "አንተ ጥቁር ባሪያ ስለ ኃጢአትህ አልቅስ" እያለ ይገስጽ: ከውዳሴ ከንቱም ይርቅ ነበር:: ከቆይታ በኋላም በመነኮሳት ላይ እረኛ (አበ ምኔት) ሆኖ ተሾመ:: እንደሚገባም አገለገለ:: የበርካቶችን ሕይወት ጨው በሆነ ሕይወቱና ምክሩ አጣፍጦ: ድርሳናትንም ደርሶ እያረጀ ሄደ::
°°°
ከቁመቱ መርዘም የጽሕሙ ነጭነትና አወራረዱን ያዩ ሁሉ ሲያዩት ያደንቁት ነበር:: በመጨረሻም በ375 ዓ/ም በርበረሮች (አሕዛብ) ገዳመ አስቄጥስን ሲያጠፉ ሌሎች መነኮሳት ሸሹ:: እርሱ ግን አልሸሽም ብሎ ከ7 ደቀ መዛሙርቱ ጋር በዚህች ቀን ተሰይፎ በሰማዕትነት አልፏል::
ምንጭ፦ ዜና ቅዱሳን
°°°
"አምላከ ቅዱሳን ልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ ሙሴ ጸሊምን ለርስቱ ያበቃ ጌታ ለእኛም ዕድሜ ለንስሐ: ለዘመን ለፍስሐን አይንሳን፤ ከበረከቱም ያድለን::"
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!