Get Mystery Box with random crypto!

✞ በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን:: ✞ ''' ነሐሴ 27ቀን የሚከበሩ | ሰኞ መርሃ ግብር / ማኅበረ ጽዮን

✞ በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን:: ✞

""" ነሐሴ 27ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት """

+" 12ቱ አበው ደቂቀ እሥራኤል "+

=>እነዚህ አበው የአብርሃምና የይስሐቅ የልጅ ልጆች የያዕቆብ ደግሞ ልጆች ናቸው:: ትውልድ ከአዳም እስከ ቅዱስ ያዕቆብ አንድ ሐረግ ይዞ መጥቶ እዚህ ላይ ሲደርስ ይበተናል:: አባታችን ያዕቆብን እግዚአብሔር ሲባርከው እሥራኤል አለው:: ትርጉሙም "ሕዝበ እግዚአብሔር: ወልድ ዘበኩር (የበኩር ልጅ): ከሃሊ: ነጻሪ (አስተዋይ) እንደ ማለት ነው::

+ይህ ቅዱስ አባት ለድንግል ማርያም ቅድመ አያት ከመሆኑ ባሻገር ነቢያትን: ካህናትን: ነገሥታትንና መሣፍንትን ወልዷል:: ከወንድሙ ኤሳው ጋር ተጣልቶ ወደ ሶርያ በሔደ ጊዜ ከ2ቱ ሚስቶቹ (ልያና ራሔል) 8 ልጆችን: ከ2ቱ የሚስቶቹ ደንገ ጥሮች (ዘለፋና ባላ) 4 ልጆችን: በድምሩ 12 ልጆችን ወልዷል::

#‎ልያ  የወለደቻቸው:-
1.ሮቤል
2.ስምዖን
3.ሌዊ
4.ይሁዳ
5.ይሳኮር እና
6.ዛብሎን ይባላሉ::

#‎ራሔል  የወለደቻቸው:-
7.ዮሴፍና
8.ብንያም ይባላሉ::

#‎ባላ :- 9.ዳን እና
10.ንፍታሌምን ስትወልድ

#‎ዘለፋ :- ደግሞ 11.ጋድና 12.አሴርን ወልዳለች::

#‎12ቱ  ደቂቀ እሥራኤል (ያዕቆብ) ማለት እኒህ ናቸው::

+ከ12ቱ በቅድስና ዮሴፍ ከፍ ቢልም እግዚአብሔር ለክህነት ሌዊን: ለመንግስት ደግሞ ይሁዳን መርጧል:: ከእነሱ ዘርም ዓለምን ለማዳን ተወልዷል:: 10ሩ አበው በተለይ በዮሴፍ ላይ ግፍ ሠርተው የነበረ ቢሆንም በኋላተጸጽተዋል:: እነሆ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ታስባቸዋለች:: (ዘፍ. ከ28-31)

+" ነቢዩ ቅዱስ ሳሙኤል "+

+እሥራኤል ከግብፅ ባርነት ወጥተው ከነዓንን ከወረሱበት ዘመን ጀምረው መሳፍንትና ካህናት ያስተዳድሯቸው ነበር:: በወቅቱ ታዲያ ክህነት ከምስፍና ተስማምቶለት ኤሊ የተባለ ሊቀ ካህናትና ልጆቹ (አፍኒና ፊንሐስ) ያስተዳድሩ ጀመር::

+በዘመኑ ደግሞ ማሕጸኗ ተዘግቶባት ዘወትር የምታለቅስ ሐና የሚሏት ደግ ሴት ነበረች:: እግዚአብሔር የእርሷን ጸሎትና የሊቀ ካህናቱን ምርቃት ሰምቷልና ቅዱስ ልጅን ሰጣት:: "ሳሙኤል" አለችው:: "ልመናየን አምላክ ሰማኝ" ማለት ነውና::

+ሐና ስዕለቷን ትፈጽም ዘንድ ሳሙኤልን በ3 ዓመቱ ለቤተ እግዚአብሔር ሰጠችው:: በዚያም ስብሐተ እግዚአብሔርን እየሰማ: ማዕጠንቱን እያሸተተ: ከደብተራ ኦሪቱ ሳይለይ በሞገስ አደገ:: የኤሊ ልጆች (አፍኒና ፊንሐስ) በበደል ላይ በደልን አበዙ::

+ወቅቱ የአሁኑን ዘመን ይመስል ነበር:: ሁሉም ሰው ክፋተኛ የሆነበት በመሆኑ እግዚአብሔር ርቆ ስለ ነበር ትንቢትና ራዕይ ብርቅ ነበር:: አምላክ ተቆጥቷልና ሳሙኤልን በሌሊት 3 ጊዜ ጠራው:: ነቢዩም ታጥቆ የፈጣሪውን ቃል ሰማ:: በዚሕም የተነሳ ታቦተ ጽዮን ለመጀመሪያ ጊዜ በአሕዛብ ተማረከች:: ከ34ሺ በላይ ሕዝብ በኢሎፍላውያን አለቀ:: አፍኒና ፊንሐስም ተገደሉ:: ኤሊም ወድቆ ሞተ::

+ከዚህች ቀን በኋላ ቅዱስ ሳሙኤል በእሥራኤል ላይ ነቢይና መስፍን ሆኖ ተሾመ:: በዘመኑ ሁሉ እንደሚገባው እየኖረ: የእግዚአብሔርን ለእሥራኤል: የእሥራኤልን ለእግዚአብሔር ሲያደርስ ኑሯል:: ሕዝቡ ንጉሥ በፈለጉ ጊዜ ሳዖልን ቀብቶ አነገሠላቸው:: እርሱ (ሳዖል) እንደ ሕጉ አልሔደምና ፈጣሪ ናቀው::

+ሳሙኤል ግን ደግ አባት ነውና ክፋተኛውን (ሳዖልን) ከጌታው ጋር ያስታርቅ ዘንድ ብዙ ደከመ: አለቀሰም:: እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን:- "አትዘን! እንደ ልቤ የሆነ: ፈቃዴን የሚፈጽም ዳዊትን አግኝቸዋለሁና እርሱን በእሥራኤል ላይ አንግሠው" አለው::
ቅዱስ ሳሙኤልም ወደ ቤተ ልሔም ሔዶ: ከእሴይ ልጆችም መርጦ ልበ አምላክ ዳዊትን ቀባው: አነገሠውም::

+ቅዱስ ሳሙኤል በተረፈው ዘመኑ ለፈጣሪው እየተገዛ ኑሯል:: ነቢዩ ዘወትር ከእጁ የሽቱ ሙዳይና የቅብዐት እቃ (ቀንድ) አይለይም ነበረ:: እነዚህም የድንግል ማርያም ምሳሌዎች ናቸውና አባ ሕርያቆስ:-
"ሙዳየ ዕፍረት ወቀርነ ቅብዕ ዘሳሙኤል" ብሎ አመስግኗታል::

+ነቢዩም በወገኖቹ መካከል በዚሕች ቀን አርፏል:: እሥራኤልም አልቅሰውለታል:: ዛሬ ቅዱሱ ነቢይ ለአገልግሎት የተጠራበት ቀን ነው::

+" ቅዱስ ሱርያል ሊቀ መላዕክት "+

+ከታላላቅ ሊቃናት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሱርያል ክብሩ ብዙ ቢሆንም ብዙ ምዕመናን አያውቁትም:: የመላእክት መዓርግ ሲነገር ሚካኤል: ገብርኤል: ሩፋኤል ብሎ ቀጥሎ የሚመጣው ሱርያል ነው::

+በ3ቱ ሰማያት ካሉት 9ኙ ዓለመ መላእክት የአንዱ (የሥልጣናት) መሪ (አለቃ) ነው:: መልአኩ እጅግ ርሕሩሕ እና ተራዳኢ ነውና አንዘንጋው:: ለኖኅ መርከብርን ያሳራው: ከጥፋት ውሃም ያዳነው ይህ ቅዱስ መልአክ ነው::

+በገድለ ሰማዕታትም ላይ እንደተጠቀሰው የሰማዕታት ረዳትና አዳኝም ነው:: ቅዱስ ሱርያል በሌላ ስሙ "እሥራልዩ" ይባላል:: "የእሥራኤል ረዳት" እንደ ማለት::

=>ቸሩ አምላከ ቅዱሳን ስለ አባቶቻችን ብሎ ይማረን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

=>ነሐሴ 27 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1."12ቱ" ደቂቀ ያዕቆብ (እሥራኤል)
2.ቅዱስ ሳሙኤል ነቢይ (የተጠራበት)
3.ቅዱስ ሱርያል ሊቀ መላእክት
4.ቅዱስ ብንያሚንና እህቱ አውዶከስያ (ሰማዕታት)
5.ቅዱስ ፊቅጦርና እናቱ ሣራ
6.አባ ባስልዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮዽያ (የተሾሙበት)

በ 27 የሚከበሩ ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት
1.የጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በዓለ ስቅለት
2.አቡነ መብዐ ፅዮን ጻድቅ
3.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)
4.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
5.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
6.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት
7.ማር ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት

=>+"+ እነዚህም ሁሉ አሥራ ሁለቱ የእሥራኤል ነገዶች ናቸው:: አባታቸው የነገራቸው ይህ ነው:: ባረካቸውም:: እያንዳንዳቸውን እንደ በረከታቸው ባረካቸው:: +"+ (ዘፍ. 49:28)
=>+"+ በመንፈስም ወደ ታላቅና ወደ ረዥም ተራራ ወሰደኝ:: የእግዚአብሔርም ክብር ያለባትን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን ከሰማይ: ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ . . . አሥራ ሁለት ደጆችም ነበሯት:: በደጆቹም አሥራ ሁለት መላእክት ቆሙ:: የአሥራ ሁለቱም የእሥራኤል ልጆች ነገዶች ስሞች ተጽፈውባቸው ነበር:: +"+ (ራዕይ. 21:11)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>