Get Mystery Box with random crypto!

የበረሐው መናኝ የአቡነ ዕንጦንስ ገዳም እግዚአብሔር ግሩም በቅዱሳኒሁ እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ | ሰኞ መርሃ ግብር / ማኅበረ ጽዮን

የበረሐው መናኝ የአቡነ ዕንጦንስ ገዳም
እግዚአብሔር ግሩም በቅዱሳኒሁ
እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ግሩም ነው

ርዕሰ መነኮሳት ኮከበ ገዳም የበረሃው ፈርጥ የሆኑት ቅዱስ አባታችን አቡነ ዕንጦንስ የመነኮሳት ሁሉ አባት ናቸው።

ልብሰ መላእክት ለብሶ የምናኔን በረከት ለዓለሙ ሁሉ ያሰራጨ ቅዱስ አባት ነው።

በዚህ ቦታ ለመገኘት ብዙ ዋጋ ከፍለው አባቶቻችን በረከት ለመቀበል ይመጡ ነበረ።

ብዙዎቹ ቅዱሳን ቦታዎችን በዓይን አይተው
በእግር ተረግጠው
በእጅ ዳሰው የሚገኘውን በረከት ለመቀበል ይመጡ ነበረ
እግዚአብሔር እንደ እምነታችን እንደሚያደርግልን እናምናለን

ከብፁዕነታቸው ከብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ጋር በመሆን የጀመርነው ሐዋርያዊ የበረከት ጉዞ እንደቀጠለ ነው

ከአቡነ ዕንጦንስ ገዳም ለመድረስ ከካይሮ የዘጠኝ ሰዓት የመኪና ጉዞ የተጓዝን ሲሆን በቦታው ስንደርስ የአባታችን በረከት ያለመለመውን ገዳም ተመለከትን።

ገዳሙን ስትመለከቱ ገዳመ ቆሮንቶስ ቁልጭ ብሎ ይታያችኋል መልክአ ምድሩ አየሩ ሐሩሩ እና ያለው በረከት ስታዩ ቅዱሱ አባት ዳግማይ ገዳመ ቆሮንቶስን የመሠረቱበት ግሩም የበረከት ስፍራ ታያላችሁ።

በዚህ ገዳም ከፀሐዩ ዋዕይ የተነሣ አይደለም የሰው ዘር ትንኝ ነፍሳት አታዩም ምድሩ አየሩ ያቃጥላል ።

ጻድቁ አባታችን በዚህ ስፍራ ማንም በሌለበት የሰው ዘር እንኳ በማይታይበት ዛፍ ቅጠል በማይገኝበት በዚህ ስፍራ
47 ዓመት በጽናት ጾመዋል ከፈጣሪያቸው ጋር በግልጽ አውርተዋል ሰፊ የሆነ በረከት ተቀብለዋል በረከታቸው አይለየን።

እርሳቸው የጸለዩበት ስፍራ ዋሻ ውስጥ ስለሆነ ሳይነካካ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ይጸለይበታል ሰው እየመጣ በረከት ይቀበልበታል።

ተራራው ሳንወጣ ደግሞ ሜዳው ላይ ልጆቻቸው ቤተ ክርስቲያን ሰርተው ቦታውን አልምተው በሚደንቅ መንገድ ያንን በረሐ ገነት አድርገው ይኖራሉ ።

በዚህ ገዳም ለጻድቁ አባታችን ለአቡነ እንጦንስ የፈለቀላቸው ምንጭ አለ ይህ ምንጭ ብዙ ሰው ሆኖ ሲመጣ በብዛት ይፈሳል ጥቂት ሰው ከመጣ ደግሞ ጥቂት ሆኖ ይፈሳል

በዚህ በረሐ ከዓመት እስከ ዓመት የማይቋረጥ የፈውስ ምንጭ አለ።

ከመቶ በላይ መናንያን ያሉ ሲሆን በዚህ በረሐ የማንንም እርዳታ ሳይፈልጉ ራሳቸውን ረድተው ይኖራሉ በጻድቁ ጸሎት ተጠብቀው ይኖራሉ። በረከታቸው አይለየን።

ጸልዩ በእንተ ሰላም
ስለ ሰላም እንጸልይ
ስለ ሀገራችን እንጸልይ
ስለ ቤተ ክርስቲያናችን እንጸልይ
በረሐብ በስደት ስላሉት እንጸልይ
ሁላችንም ወደ ልባችን ተመልሰን ስለ አንድነታችን እና ስለ ሰላማችን እንጸልይ።

የሰላም አምላክ ለሀገራችንና ለህበችን ሰላምን ይስጥልን

አባ አትናቴዎስ ወልደ ጎርጎርዮስ
ካይሮ አባይ ባህር ማዶ 24/12/2014