Get Mystery Box with random crypto!

††† እንኳን ለሰማዕታት ቅዱስ እንጣዎስ እና ቅዱስ ያዕቆብ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳ | ሰኞ መርሃ ግብር / ማኅበረ ጽዮን

††† እንኳን ለሰማዕታት ቅዱስ እንጣዎስ እና ቅዱስ ያዕቆብ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ እንጣዎስ አሞራዊ †††

††† ይሕ ቅዱስ በቀደመ ሕይወቱ ክርስቲያኖችን የሚጠላ አስቸጋሪ አረማዊ ነበር:: ሃገሩ #ሶርያ( #ደማስቆ) ሲሆን ግብሩ ጣዖት ማምለክና መስረቅ ነበር:: በቅድስት ቤተ ክርስቲያንና በምዕመናን ላይም ግፍን ፈጽሟል:: በሥጋዊ ጉልበቱ ኃይለኛ ስለ ነበር የተፈራ ነው::

ሁልጊዜ በጠዋት ወደ #ቤተ_ክርስቲያን ይሔዳል:: የሚሔደው ግን ንዋያተ ቅድሳትን ለመዝረፍ: አንድም ካህናትን ለመደብደብ ነበር:: የሚገርመው ግን የወቅቱ ምዕመናንና ካህናት ይህን ሁሉ እያደረገባቸው አይጠሉትም:: ይልቁኑ ይጸልዩለት ነበር እንጂ:: ምክንያቱም ክርስትና ማለት ጠላትን መውደድ ነውና:: (ማቴ. 7)

የእግዚአብሔር ትዕግስትና የምዕመናን ጸሎት ተደምሮው አንድ ቀን ፍሬ አፈራ:: እንጣዎስ እንደ ለመደው ለክፉ ሥራ ወደ #ቅዱስ_ቴዎድሮስ ቤተ ክርስቲያን ይሔዳል:: ከዚያም እንደ ደረሰ ወደ ውስጥ ገብቶ: የሚማታውን ተማቶ: የሚዘርፈውንም ዘርፎ: የተረፉትን ንዋያተ ቅድሳት በእሳት አቃጠላቸው::

#እግዚአብሔር ከዚህም በላይ ታጋሽ ነውና አላጠፋውም:: "ዘኢይፈቅድ ለኃጥእ ሞቶ" እንዲል የኃጢአተኛውን መመለስ እንጂ መሞቱን አይፈልግም:: ለዚያም ነው ዛሬ ይሔ ሁሉ ግፍ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየተሠራ እግዚአብሔር እንደማያይ ዝም የሚለው:: ለሁሉም ቀን አለውና በፈረደ ቀን ግን በፊቱ የሚቆም አይኖርም::

እንጣዎስ ግን የሠራውን ሠርቶ እወጣለሁ ሲል አልተሳካለትም:: ከበሩ አካባቢ ሲደርስ: ከወደ ሰማይ አካባቢ ድምጽ ሰምቶ ቀና ሲል መላእክት እንደሱ ዓይነት ኃጢአተኞችን አሰልፈው በጦርና በቀስት ሲወጉአቸው ተመለከተ::

ድንገት ግን ከመላእክቱ አንዱ ዘወር ብሎ አንድ ቀስት ወደ እንጣዎስ ወረወረ (ተኮሰ):: ቀስቷ አካሉ ውስጥ ገብታለችና እንጣዎስ መሬት ላይ ወድቆ ለሞት ደረሰ:: ላበቱ በግንባሩ ላይ በጭንቅ እየፈሰሰ ጮኸ::

"ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ማረኝ? ራራልኝ? ይቅር በለኝ? በድፍረት ባለ ማወቅም በድየሃለሁ:: ይቅር በለኝና ላምልክህ: ስምህንም ልሸከም" ሲል በጭንቀት ውስጥ ሆኖ አሰምቶ ጸለየ:: በዚያ የነበሩ ምዕመናን ማን: በምን እንደ ወጋው ባያውቁም ባዩት ነገር ግን እጅግ ደስ አላቸው:: እነርሱም የፈለጉትና የጸለዩለት ነገር ይሔው ነበርና::

ወዲያው ግን እንጣዎስ ከሞት ጫፍ ተመልሶ ተነሳ:: መጀመሪያ በቦታው የነበሩ ካህናትና ምዕመናንን "ይቅር በሉኝ?" አለ:: ቀጥሎም ወደ ዻዻስ ዘንድ ሔዶ "አጥምቀኝ" ሲል ጠየቀ:: እርሱ በሚጠመቅበት ቀን ብዙ አሕዛብና ክርስቲያኖች ተሰብስበው ነበር::

እርሱ በከተማዋ ዝነኛ ነበር:: ሥርዓቱ ሁሉ ተደርሶ ቅዱሱ ወደ ውሃ ገንዳው ሲገባ ሁሉ እያዩ የብርሃን ምሰሶ ከሰማይ ወረደ:: ይህንን በገሃድ የተመለከቱ ከ10,000 በላይ አሕዛብ ወዲያውኑ በክርስቶስ አምነው አብረውት ተጠምቀዋል::

ቅዱስ እንጣዎስ ከዚህ በሁዋላ ምስጉን ክርስቲያን ሆነ:: ስለ ቀደመ ሕይወቱ ፈንታ ጾምን: ጸሎትን: ፍቅርን: ምጽዋትን ገንዘብ አደረገ:: ሕይወቱም ለብዙ ሰዎች መስታውት ሆነ:: #እመቤታችን ድንግል ማርያምንም ይወዳት ነበርና ወደ ቅዱሳን ማሕበር ( #ኢየሩሳሌም) ወስዳው በሥጋዊ አንደበት ተከናውኖ ሊነገር የማይቻል ምሥጢርን ገልጣለታለች::

እነዚህን የቅድስና ጊዜያት በስኬት ያሳለፈው ቅዱስ እንጣዎስ መጨረሻው ሰማዕትነት ሆነ::
አረማውያን ወገኖቹና ቀድሞ የሚያውቁት ወደ ቀደመ ክፋትና ክህደት እንዲመለስ ጠየቁት:: "አይሆንም" አላቸው:: በአደባባይ ለፍርድ አቅርበው ደሙ እስኪፈስ ገረፉት::

ጥርሶቹን በሙሉ በድንጋይ አረገፏቸው:: ደሙና ጥርሶቹ መሬት ላይ ተዘሩ:: ነገር ግን ይሕ ስቃይ ቅዱሱን ከፍቅረ ክርስቶስ ሊለየው አልቻለም:: አሕዛብም ተስፋ ቆርጠው በዚህች ቀን ገድለውታል:: ቅዱስ እንጣዎስም ከሁዋለኛው ዘመን #ሰማዕታት እንደ አንዱ ተቆጥሯል::

††† ቅዱስ ያዕቆብ ግብጻዊ †††

††† ቅዱስ ያዕቆብ ተወልዶ ያደገው #መኑፍ (ግብጽ) ውስጥ ሲሆን ዘመኑም 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ወላጆቹ የተባረኩ ናቸውና እርሱ ሳይወለድ የነበሯቸውን 3 ሴቶች ልጆች "ተማሩ" ብለው ወደ ገዳም ቢያስገቧቸው በዚያው መንነው ቀሩባቸው::

በዚህ ሲያዝኑ #ቅዱስ_ያዕቆብ ተወልዶላቸዋል:: እነርሱም በቃለ እግዚአብሔርና በጥበብ አሳድገውታል:: ትንሽ ከፍ ሲል በአካባቢው ከነበረ አንድ ቅዱስ ሽማግሌ ጋር ተደብቀው ገድልን ይሠሩ ነበር:: ሁሌም መልካም ምግባራትን ከመፈጸም ባለፈ ሙሉውን ሌሊት ባሕር ውስጥ ሰጥመው ይጸልዩ ነበር::

ዘመነ ሰማዕታት በመጣ ጊዜም 2ቱ ተመካክረው ስመ ክርስቶስን በገሃድ ሰብከዋል:: በዚህ ምክንያት ቅዱሱን ሽማግሌ ወዲያው ሲገድሉት ቅዱስ ያዕቆብን ግን ብዙ አሰቃይተውታል:: በመጨረሻም በዚህች ቀን ተሰይፎ የክብርን አክሊል ተቀብሏል::

††† አምላከ ሰማዕታት ቤተ ክርስቲያንን ከመከራ ይጠብቅልን:: ከበረከታቸውም ያሳትፈን::

††† ነሐሴ 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል
2.ቅዱስ እንጣዎስ አሞራዊ (ሰማዕት)
3.ቅዱስ ያዕቆብ ግብጻዊ (ሰማዕት)
4.ቅዱስ አክራጥስ ሰማዕት
5.አባ እለእስክንድሮስ ዘቁስጥንጥንያ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
2.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
3.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
4.አባ ገሪማ ዘመደራ
5.አባ ዸላሞን ፈላሢ
6.አባ ለትጹን የዋህ
7.ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ (ዘደሴተ ቆዽሮስ)

††† "ኃጢአተኞችን ሊያድን #ክርስቶስ_ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው:: ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ:: ስለዚህ ግን የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ::" †††
(1ጢሞ. 1:15)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††