Get Mystery Box with random crypto!

+ ለምን ትቀናለህ? + በዜና አበው ላይ አጋንንት አንድን መነኩሴ ለማሰናከል ሲማከሩ የሚያሳ | ማዕዶት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ

+ ለምን ትቀናለህ? +

በዜና አበው ላይ አጋንንት አንድን መነኩሴ ለማሰናከል ሲማከሩ የሚያሳይ ታሪክ ተጽፎአል፡፡ መነኩሴው ለብዙ ዘመናት በተጋድሎ አሳልፎ ከብቃት የደረሰ መናኝ ነበር፡፡ የአጋንንቱ ጭፍራ በአለቃቸው ተመርተው ይህንን መነኩሴ ለማሳት ዘመቱ፡፡ ተራ በተራ ወደ እርሱ እየሔዱ የፈተና ወጥመዳቸውን ዘረጉበት፡፡ በዝሙት ሊፈትኑት ሞከሩ፡፡ አልተሳካም፡፡ በምግብም ሞከሩ ድል ነሣቸው፡፡ የሚያውቁትን የፈተና ስልት በተለያየ መንገድ እየተገለጹ አንዴ ሰው አንዴ መልአክ እየመሰሉ ሊጥሉት ቢሞክሩም አልቻሉም፡፡

አለቃቸው ይኼን ጊዜ በሉ እኔ የማደርገውን ተመልከቱ አላቸውና መንገደኛ መስሎ ወደ መነኩሴው ቀረበ፡፡ በጆሮው የሆነ ነግሮት ወዲያው ተሰናብቶት ወጣ፡፡ ይህንን ጊዜ አጋንንቱ እያዩት መነኩሴው መንፈሳዊ ገጽታው ተገፍፎ ፊቱ በቁጣና በንዴት ሲለዋወጥ ተመለከቱት፡፡ በዚህም ተደንቀው ምን ብለህ ነው ያሸነፍከው? ብለው አለቃቸውን ጠየቁት፡፡ እርሱም እንዲህ አላቸው፦ ‘ከአንተ ጋር ያደገውና ከአንተ ጋር የተማረው ጓደኛህ እኮ የእስክንድርያ ፓትርያርክ ሆኖ ተሾመ’ ብዬ ነገርኩትና ወጣሁ፡፡ አሁን ልቡ በቅናት እየነደደ ነው አላቸው፡፡ አጋንንቱ በደስታ ጨፈሩ፡፡

ሰይጣን የቅናትን ኃይል ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ መጽሐፈ ቅዳሴ ሞትን ሲገልጸው ‘በሰይጣን ቅናት ወደ ዓለም የገባ’ ይለዋል፡፡ ሰይጣን በሰው ልጅ ጸጋ ቀንቶ አዳምና ሔዋንን በፈጣሪያቸው እንዲቀኑና አምላክ መሆን እንዲመኙ አድርጎ ዓለምን ያመሰቃቀለ ነውና ይህንን መነኩሴ ለመጣል ለሺህ ዓመታት ብዙዎችን ወግቶ የጣለባትን ሰይፉን መዘዘበት፡፡ መነኩሴው የእኩያውን መሾም ሲሰማ ቅናቱን መቋቋም አቃተው::

ቅናት እጅግ ክፉ ኃጢአት ነው፡፡ ሰው ቢዘሙት ቢሰክር በሥጋው ነው:: ቅናት ግን በምታስተውል ነፍሱ ውስጥ የሚበቅል መርዝ ነው፡፡ ቃየልን በየዋህ ወንድሙ ላይ ያስጨከነው ቅናት ነበር፡፡ የአቤል ስኬት ለቃየል ውድቀት መስሎ ስለተሰማው በግፍ ሊገድለው በቃ፡፡

ዮሴፍ የለበሳት ቀለምዋ ብዙ የሆነ ጌጠኛ ቀሚስ በወንድሞቹ ዘንድ የመረረ ጥላቻን አትርፋለት ነበር፡፡ አንዱ አጊጦ አምሮ ሲታይ ቢሞትና ቢገላገሉት ደስ የሚላቸው የዮሴፍ ወንድሞች በየዘመኑ አሉ፡፡

ዮሴፍም አርፎ አልተቀመጠም፡፡ እየሔደ ሕልሙን ይነግራቸው ነበር፡፡ ስለ ሕልሙም የበለጠ ጠሉት ይላል፡፡ ወዳጄ ሕልምህን ዝም ብለህ ለሰዎች አትዝራ፡፡ ሕልም ስልህ ተኝተህ የምታየውን ብቻ ማለቴ አይደለም፡፡ ራእይህን ፣ ተስፋህን ዕቅድህን ሲያውቁ የሚንገበገቡ የዮሴፍ ወንድሞች በየዘመኑ አሉ፡፡ ፍቺው ባይገባቸውም ባልተፈታ ሕልም ይጠሉሃል፡፡ ምንም ነገር ሳታደርግ እንኳን "ለምን አለምከው?" ብለው ጥርስ ይነክሱብሃል፡፡ ዮሴፍ ግን ይኼ ስላልገባው ነገራቸው፡፡ ወዳጄ አንተም ሕልምህን እንደ ዮሴፍ በየዋህነት የምትዘራ ከሆንህ እንግዲህ የዮሴፍ አምላክ ይጠብቅህ፡፡

ቅናት እጅግ ከባድ ነው፡፡ እረኛው ዳዊት ጎልያድን የገደለ ዕለት የተዘፈነለት መዘዘኛ ዘፈንም ነበረ፡፡ ‘ሳኦል ሺህ ገደለ ዳዊት እልፍ ገደለ’ ብለው ዘፈኑለት፡፡ ይህች ዘፈን በሳኦል ጆሮ ስትደርስ ዳዊት ላይ ብዙ ጦር አስወረወረች፡፡ ሳኦሎች ሌላ ሰው ከእነርሱ በላይ ሲመሰገን የሰሙ ዕለት በቅናት ታውረው ገበታ ላይ ሳይቀር ሰይፍ ይመዛሉ፡፡

የጠፋው ልጅ ወንድምን አስበው፡፡ (ሉቃ 15:20) ወንድሙ ከጠፋበት ተመልሶ ደስታ ሲደረግ እርሱ ግን ከፍቶት ውጪ ቁጭ አለ፡፡ ወዳጄ ቅናት ከቤተ ክርስቲያንና ከእግዚአብሔር መንግሥት ያስወጣል፡፡ የሌላው ስኬት ካበሳጨህ እንደጠፋው ልጅ ወንድም ውጪ ቁጭ ብለህ አፈር እየጫርክ ‘እምቢየው አልገባም’ እያልክ እያልጎመጎምክ ትቀራለህ፡፡

ክርስቶስ ላይ አይሁድ ያቀረቡት ትችት ሁሉ ለሕግ ከመቆርቆር ሳይሆን ከቅናት ነበር፡፡ ጲላጦስ እንኳን ‘በቅናት አሳልፈው እንደሠጡት ያውቅ ነበር’ ይላል፡፡ አንዳንዴ ሰዎች ቅናታቸውን በሌላ ነገር እንደ አይሁድ ሸፍነው ትችት ያቀርባሉ፡፡ ለእግዚአብሔር ሕግ እንደተቆረቆሩ ፣ ለሥርዓቱ እንዳዘኑ መስለው ውስጣቸው ያለውን ቅናትና ጥላቻ ያንጸባርቃሉ፡፡

የሰንበት መሻር ፣ ለቄሣር ግብር መከፈል ፣ የመቅደሱ በሦስት ቀን ፈርሶ መሠራት እንዳንገበገባቸው እርር እያሉ ቢናገሩም እውነታው ግን ቅናት ነው፡፡ ‘የቤትህ ቅናት በላኝ’ እንዳለው ጌታ በየዘመኑ የሰዎች ቅናት ብዙ ንጹሐንን ትበላለች፡፡

ወዳጄ በሌላው ትቀና እንደሆን አሁኑኑ ከዚህ ውስጥን በልቶ ከሚጨርስ ካንሰር ራስህን አድን፡፡

ራስህን ከሌሎች ጋር አታወዳድር፡፡ በምድር ላይ እግዚአብሔር የፈጠረው አንተን የሚመስል ሌላ ሰው የለም፡፡ ካንተ ቀድሞም በትክክል አንተን የሆነ ሰው አልተፈጠረም ለወደፊትም አይፈጠርም፡፡ እግዚአብሔር ቀድሞ ያልሠራው ደግሞም የማይሠራው ምርጥ ዕቃው ነህና ራስህን ከሌላ ጋር አታወዳድር፡፡

ለአንተ ብቻ የሠጠው ጸጋ አለና ሌሎችን መመልከት ትተህ ውስጥህ ያለውን ውድ ማንነት ቆፍረህ አውጣ፡፡ ያንተ ሕይወት ቁልፍ የተቀበረው አንተው ውስጥ ነው፡፡ ሌሎችን ረስተህ ወደ ራስህ ጠልቀህ ግባ፡፡ መብለጥ ከፈለግህም አሁን ያለውን ራስህን ብለጠውና ሌላ ትልቅ አንተን ሁን፡፡

በቅናት እንዳትቃጠል ሌሎችን ሰዎችንም ውደዳቸው፡፡ ከወደድሃቸው ‘ፍቅር አይቀናም’ና የእነርሱ ስኬት የደስታህ ምንጭ ይሆናል፡፡ የቅናት ስሜት ሲሰማህም ‘ቀናተኛ ልቤን ፈውስልኝ’ ብለህ ለምነው፡፡

‘በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን’ ሮሜ 13፡13

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
አለታ ወንዶ ኢትዮጵያ
ጥር 5 2013 ዓ.ም.

መነሻ ሃሳብ:- የአንድ በቅናት ጦስ ሊያበሩ ሲችሉ ብዙ ዋጋ የከፈሉ ቤተሰቦች ታሪክ