Get Mystery Box with random crypto!

ለመጀመሪያዋ ቋንቋችን፣ ለመጨረሻዋ እናታችን ምስጋናን እናቅርብ!! #ዕግትዋ_ለጽዮን ፤ #ጽዮንን_ክ | ማዕዶት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ

ለመጀመሪያዋ ቋንቋችን፣ ለመጨረሻዋ እናታችን ምስጋናን እናቅርብ!! #ዕግትዋ_ለጽዮን ፤ #ጽዮንን_ክበቡአት!!

ዕድሜያችን ባከነ እየተሳቀቀ፣
ልጅ ሆነን አጓጉቶን ፥ ልጅ ሆነን አለቀ ።

እንደገና መወለድ ቢቻል እንኳ አልፈልግም እንጂ ፤ እንደገና ብወለድ ኖሮ ብዙ የማስተካክላቸው የቤት ሥራዎችና የማካክሳቸው የባከኑ ጊዜያት ነበሩኝ። እጅግ በጣም ብዙ!!

አሁን ግን በተሰጠኝ ዕድሜ እንድሠራበትና ዕድሜ ለንስሐ ፥ ዘመን ለፍስሐ እንዲሆነኝ አምላኬን እለምናለሁ፡፡ እናቴን እመ ብርሃንን እማልላለሁ።

የመልከአ ማርያም ደራሲ ይህን እንዳለ፡-

#ሕይወትዬ_በንዝህላል_እመ_ተሰልጠ_ወኀልቀ፤
#ወስክኒ_ክራማተ_እስከ_እገብር_ጽድቀ፡፡

"እናቴ ማርያም ሆይ ዘመኔ ህይወቴ በዋዛ ፈዛዛ በንዝላልነት አልቋልና መልካም [እስክሠራ] የምሠራበትን፣ ጽድቅ [እስክፈጽም] የምፈጽምበትን ጊዜ፣ ዘመን፣ ዓመት፣ ዕድሜ ጨምሪልኝ" እያልኩ እማጸንሻለሁ።

ጣዕምሽን በአንደበቴ፣ ፍቅርሽን በልቦናዬ፣ ንፅሕናሽን በህሊናዬ፣ ቅድስናሽን በሰውነቴ እንዲስልብኝ፤ እንዲያሳድርብኝ!! አዎ ይሳልብኝ፤ ያሳድርብኝ!! ይበልጡኑ ለውዳሴሽ እንድተጋ ….. ወስክኒ ክራማተ እስከ እገብር ጽድቀ፡፡

ስብሐተ እግዚአብሔር ሌትና ቀን በሚፈስበት በዓል፣ ንግሥተ ሰማይ ወምድር እመ ብርሃን ክብሯ በሚነገርበት፣ ቅዳሴዋ ውዳሴዋ በሚደርስበት በድንግል እናታችን መታሰቢያ ዕለት መወለዴ እጅግ ሲበዛ ያስደስተኛል፡፡

ለእመ ብርሃን የሚገባትን ክብር የሚሰጣትና በምልጃዋ ተማምኖ በእናትነት የሚቀበላት ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ሁሉ ይህን ቀን መመኘቱ ግን አይቀርም፡፡ እኔም በዓለ ጽዮንን ክብሩን ሳስብ ልደቴ በዚሁ ቀን የመሆኑ ደስታዬ ወደር የለውም፡፡ የማከብረው ልደቴን ሳይሆን፤ የእመቤቴን በዓለ ክብር ነውና!!

በዓሉ የሁላችንም ኦርቶዶክሳዊያን ስለሆነ መልካም በዓል እንዲሆንልን እየተመኘሁ፤ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እንደተናገረ፤ ክርስቲያኖች ሁላችን ፦

#ጽዮንን_ክበቡአት_በዙሪያዋም_ተመላለሱ፥
#ግንቦችዋንም_ቍጠሩ_በብርታትዋ_ልባችሁን_አኑሩ፤
#አዳራሽዋን_አስቡ_ለሚመጣው_ትውልድ_ትነግሩ_ዘንድ
#ለዓለምና_ለዘላለም_ይህ_አምላካችን_ነው፥
#እርሱም_ለዘላለም_ይመራናል።

(መዝ.48፥12-14) እያልን ዘር ቀለም ሳንለይ በእናታችን ጽዮን ማርያም ፍቅር አንድ ሆነን እንዘምር። በሃይማኖት አንድነት ቤተሰቦች እንሁን (ገላ.6፥10)።

ዘማሪ ዲ/ን ቴዎድሮስ ዮሴፍም "ማርያም ማርያም" በሚል መዝሙሩ ፦

#በተወለድኩበት_በመጀመሪያው_ቀን፣
#ስምሽን_እየጠራሁ_ወጣሁ_ከማኅፀን፡፡

ሲል እንደተቀኘ፤ ለመጀመሪያዋ ቋንቋችን፣ ለመጨረሻዋ እናታችን ምስጋናን እናቅርብ!!

መልካም በዓል ለሁላችንም

#ዕግትዋ_ለጽዮን ፤ #ጽዮንን_ክበቡአት
ለመጀመሪያዋ ቋንቋችን፣ ለመጨረሻዋ እናታችን ምስጋናን እናቅርብ!!

(በሕዳር ጽዮን ቀን 2013 ዓ.ም)
@lijredeat07
ልጅ ረድኤት አባተ ዘጂንካ ሥላሴ