Get Mystery Box with random crypto!

ብቸኛ ሰው የለም፡፡ ኤልያስ ሽታኹን * * * * * | ከጥበብ እልፍኝ

ብቸኛ ሰው የለም፡፡
ኤልያስ ሽታኹን
* * * * * *

ይሄ ሁሉ ሰው ስለብቸኝነት
የተዘፈነ የሚሰማው
የተገጠመ የሚያነበው
የተሳለ የሚቃርመው
ወዶ ይመስልሀል?
ከሰው ጋር የጠመመ በምንም ላይቀና
ከብቸኝነት ውሰጥ ምን ደስታ አለና?
ምንም:፡
ብቻ እንዲሁ
ከአብሮነት ስቃይ
ዕንባ ያላባባይ
በአብሮነት ተዛዝሎ
ከመክረም ተቋስሎ
እያለ አሸሸ
ስንቱ ራሱን ዋሸ?
ወዶ ይመስለሀል?
ከአድማስ እስከ አድማስ
ሰው ሀዘኑ ሲማስ
እንዲያው ከራሴ ጋር ልሁነው ልንደደው
ብቸኝነት ዜማን
ለሀገሩ በሙሉ ማነው ያስለመደው?

እንጂ
ዘር የሌለው
የሰው ደም ያልሳበው
ሳቅን ፍንጣቂ
የዕንባውን ጭማቂ
የሚያይለት ያጣ
ብቸኝነት ዕጣ
ብሶት ቆፈን ወርሶት
በየጥቃቅኑ ሆድ አንጀቱን ብሶት
ገና ፈገግ ሲል
ጠፍንጎ እየያዘው ብቸኝነት ከፍንጅ
ብቻውን ተፈጥሮ
ብቻውን የሞት የታለ የሰው ልጅ?

ብቸኛ ሚባለው
ወይ እኛ የተውነው
ቢወርደን ዕንባውን
ወይ እኛን ትተውን
እንደሆን ነውና
ብናበጥር ዘሩን
አውጥተን ብናየው ከሀዘኑ ቀለም
የተተወ እንጂ ብቸኛ ሰው የለም፡፡



➤ከወደዱት በቅንነት ይቀላቀሉን!

@liulzemaryam
@liulzemaryam
@liulzemaryam