Get Mystery Box with random crypto!

አንድ ፈረሰኛ ወደ አንድ ከፍተኛ ተራራ ይጓዝ ነበር፡፡ ወደ ተራራው ወገብ ላይ ሲደርስ አንድ ምስኪ | Lighthouse Training & Consulting PLC

አንድ ፈረሰኛ ወደ አንድ ከፍተኛ ተራራ ይጓዝ ነበር፡፡ ወደ ተራራው ወገብ ላይ ሲደርስ አንድ ምስኪንና አንድ እግሩ ሽባ የሆነ ሰው እንዳቅሙ ቋጥኙን እየቧጠጠ ለመውጣት ሲፍጨረጨር ያገኛል፡፡

ፈረሰኛው፤
"ወዳጄ፤ ይህን የሚያህል ተራራ እንዲህ ተንፏቀህ የሚገፋ አይደለም፡፡ ስለዚህ እንደምንም ፈረሴ ላይ ላውጣህና አፈናጥጬ ዳገቱ ጫፍ ላይ ላድርስህ?"

ሰውዬው፤
"እግዚአብሔር የባረከህ ሰው ነህ! ግን ሥጋቴ እንዳላጣብብህ ነው፡፡ ለማፈናጠጥ ይበቃል ብለህ ነውን?"

ፈረሰኛው፤
"እንደምንም ተጣበን እንወጣዋለን እንጂ በዚህ ሁኔታ በፍፁም ጥዬህ ብሄድ ግፍ ይሆንብኛል፡፡ ሰው እንኳ ባይኖር ተራራውም ይታዘበኛል፡፡ ስለዚህ ና ውጣ ግዴለህም፡፡"

ሰውዬው፤
"ፈጣሪ ምስክሬ ነው፤ ለእኔ የተላክ ውድ አዳኝ መልዐክ ነህ፡፡ አምላክ ውለታህን ይክፈልህ!"

ፈረሰኛው ተሸክሞ ፈረሱ ላይ አስቀመጠውና ተራራውን ተያያዙት፡፡ ጥቂት እንደሄዱ ግን፤

ሰውዬው
"ወዳጄ፤ ቅድም እንደፈራሁት በጣም ተጣበናል፡፡ ብወርድልህ ይሻላል፡፡"

ፈረሰኛው፤
"እንደሱማ አይሆንም፡፡ ባይሆን የተወሰነውን ዳገት እኔ በእግሬ ልሞክረው፤ አንተ ፈረሱን ያዝ" አለውና ፈረሱን ሰጥቶት ወረደ፡፡ ሰውየው እየጋለበ ዳገቱን እየወጣ እየራቀ ሄደ፡፡

ፈረሰኛው በእግሩ ዳገቱን ተያያዘው፡፡ ሆኖም ባለፈረሱ እየራቀ ሄደ፡፡ ፈረሰኛው ሥጋት እየገባው በተቻለው ፍጥነት ሊከተለውና ሊጠጋው ቢሞክርም ሰውዬው ፈረሱን ይብስ አፈጠነው፡፡

ፈረሰኛው መጣራት ጀመረ፡፡ ወይ የሚለው ግን አጣ፡፡ ሰውዬው ፈረሱን ይዞ ሊጠፋ መሆኑ ለፈረሰኛው ገባው፡፡

“አንተ ሰው፤ ግዴለም ፈረሱን ይዘኸው ትሄዳለህ፡፡ ግን አንድ ነገር ቆም ብለህ ስማኝ እባክህ፡፡ እንደማልደርስብህ ታውቃለህ፡፡ ጆሮህን ብቻ አውሰኝ?” ሲል ለመነው፡፡

ሰውዬው ርቀቱን በደንብ ካረጋገጠ በኋላ፤
“እሺ ምንድነው ልትነግረኝ የፈለከው?”

ፈረሰኛውም፤
“ወዳጄ፤ መቼም አንድ ቦታ ወርደህ ከሰው መቀላቀልህ አይቀርም፡፡ አደራህን ይሄን አሁን እኔን የሰራኸኝን ነገር ለማንም ሰው እንዳትነግር፡፡ አለበለዚያ ደግ የሚሰራ ሰው ይጠፋል!”

#ምንጭ:- "ታሪክና ምሳሌ" ከክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል