Get Mystery Box with random crypto!

“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ትልቅ መልዕክት ያለው አባባል ነው፡፡ በጋራ የሚሰሩ ስራዎች በግል ከ | Lighthouse Training & Consulting PLC

“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ትልቅ መልዕክት ያለው አባባል ነው፡፡ በጋራ የሚሰሩ ስራዎች በግል ከሚሰሩ ስራዎች ይልቅ የላቀ ውጤት ያመጣሉ፡፡ አንድ እጅ ብቻውን አያጨበጭብም፡፡ ሩጫን በመሰለ የግል ጥረትን በከፍተኛ ሁኔታ በሚጠይቅ የውድድር ዘርፍ እንኳን አትሌቶቻችን ሲተባበሩ የሚያስመዘግቡትን አንጸባራቂ ድል እናውቀዋለን፡፡ በየትኛውም አጋጣሚ በጋራ የመስራትን መንፈስ ማዳበር ጠንካራ ያደርጋል፤ የበዛ ፍሬም ያፈራል፡፡ አብረን መብላት ብቻ ሳይሆን አብረን መስራትንም ባህላችን እናድርግ፡፡ ስቴቨን ኮቬይ እንደሚለው “አንድ ሲደመር አንድ ከሁለት በላይ ነው”፡፡

7. መጋዛችሁን ሳሉ (Sharpen the Saw)

ስቴቨን ኮቬይ መጽሐፉ ውስጥ ግሩም አፈ ታሪክ አለ፡፡ አንድ ተጓዥ መንገደኛ በአንድ ጫካ ውስጥ አቋርጦ ሲያልፍ አንድ ምስኪን እንጨት ቆራጭ ላቡ ጠፍ እስከሚል ድረስ ያለምንም እረፍት እንጨት ሲቆርጥ ይመለከታል፡፡ ተጓዡ መንገደኛ ቆም ይልና የመጋዙን መደነዝ አስተውሎ ኑሮ “ወዳጄ! ለምን መጋዝህን ዕረፍት ወስድህ አትስለውም?” ይለዋል፡፡ ልፋ ያለው እንጨት ቆራጭ “አይ ለሱ እንኳን ጊዜ የለኝም” የሚል የዋህ ምላሽ ይሰጠዋል፡፡ ይኼ ምስኪን እንጨት ቆራጭ ዕረፍት ወስዶ መጋዙን ቢስል በተሻለ ቅልጥፍና ብዙ እንጨት መቁረጥ እንደሚችል አልተረዳም፡፡

የተራ ቁጥር ሰባት ልምድ መልዕክት ቀላል እና ግልጽ ነው፡፡ በቂ ዕረፍት ምንጊዜም አድርጉ ነው፡፡ ከስራ በኋላ ራሳችሁን ዘና የማድረግ ልምምዱ ይኑራችሁ፡፡ መዝናናት ለጊዜው ከሚሰጠው ደስታ ባሻገር ለቀጣይ ስራ ያዘጋጃል፡፡ ሁልጊዜም እንደምለው ትልልቅ ኩባንያዎች ወጪ ችለው፣ ወርሃዊ ደሞዝ መክፈላቸውን ሳያቋርጡ ሰራተኞቻቸውን የሚያዝናኑት በጣም ቸር ስለሆኑ አይደለም፡፡ ይልቁንም የተዝናና ሰራተኛ ይበልጥ ውጤታማ እንደሚሆን እና እነሱንም ይበልጥ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ነው፡፡

አንድ አንድ ሰዎች “እኔ መዝናናት አይሆንልኝም” ይላሉ፡፡ “መዝናናት ራሱን የቻለ ችሎታ ነው” ይላል አንድ ሌላ ወዳጄም፡፡ በመሆኑም “እንዴት እንዝናና?” የሚል ጥያቄ ያላችሁ ሰዎች እነዚህን የመዝናኛ አማራጮች እንድትፈትlቸው እጋብዛለሁ፡- ዋና ዋኙ፤ ከወዳጅ ዘመዶቻችሁ ጋር አስደሳች ጊዜ አሳልፉ፤ ዮጋ ስሩ፤ ዳንስ ደንሱ፤ ከከተማ ከተቻለም ከሀገርም ወጣ ብላችሁ ጎብኙ፤ ደስታ ይሰጠኛል ብላችሁ የምታስቡትን የትርፍ ጊዜ የመዝናኛ አማራጭን (Hobby) ሞክሩ፡፡

(በነጋሽ አበበ)

(በጥቂቱ ተሻሽሎ የቀረበ)