Get Mystery Box with random crypto!

'ለራሱ ያልተመለሰ' ============ መንገድ ላይ ከፊት ለፊቴ ሁለት ሰዎች እያወሩ ይሄዳሉ። አ | KM Inspiration ለወጣቶች

"ለራሱ ያልተመለሰ"
============
መንገድ ላይ ከፊት ለፊቴ ሁለት ሰዎች እያወሩ ይሄዳሉ። አንደኛው "ራሱን ሊያጠፋ ሞክሮ እንደነበር ታውቃለህ አይደለ? መቼም ለራሱ ያልተመለሰ አንተን የሆነ ነገር ከማድረግ አይመለስም።" ሲል ጆሮዬ ላይ ጥልቅ አለ። በሀሳብ ከአራት አመት በፊት ተመለስኩ።

በሀያዎቹ መጨረሻ ላይ የምትገኝ በግል ድርጅት ውስጥ የምትሰራ ወጣት ከድንገተኛ ክፍል ሪፈር ተደርጋ መጣች። ታሪኳን ስትነግረኝ ከፍተኛ መከፋት ይሰማት ጀመረ። ብቸኝነት፣ ተስፋ መቁረጥ ሁሉም ነገር ማስጠላት እየተሰማት መጣ። መከፋቱ ልትቋቋመው ከምትችለው በላይ ሆነባት። በዛን ቅፅበት ሁኔታው እየተባባሰ እንጂ እየተሻሻለ እንደማይሄድ አሰበች። "ከዚህ ስቃይስ ብሞት ይሻለኛል።" አለች። መርዝ ገዝታ ወደ ቤቷ ተመለሰች። ግራ በተጋባ ስሜት ውስጥ ሆና አንድ ነገር ትዝ አላት። ፓሊሶች ሲመጡ ጎረቤቶቿ ወይም አከራይዋ ተጠርጣሪ ሊሆኑ ይችላሉ። እነሱ ተጠያቂ እንዳይሆኑና ራሷን ማጥፋቷን የሚገልፅ ማስታወሻ ፅፋ አስቀመጠች።

አከራይዋ በበርዋ ሲያልፉ የማግዋራት አይነት ድምፅ ይሰማሉ። ቢያንኳኩ መልስ የለም። ጎረቤት ጠርተው በሯን ሰብረው ሲገቡ ወለሉ ላይ ወድቃለች። አፏ አረፋ ሞልቶታል። ላዳ ጠርተው ድንገተኛ ክፍል ወሰዷት። የድንገተኛ ክፍል ህክምናዋን ስትጨርስ ወደ አእምሮ ህክምና ሪፈር ተባለች። ከወራት የአእምሮ ህክምና በኃላ አልፎአልፎ ካልሆነ ብዙ ጊዜ አትከፋም፤ በስራዋ ደስተኛ ናት። አከራይዋ ሌላ ሰው እንዳይጠየቅ የፃፈችውን ማስታወሻ ተመልክተው ልባቸው ተነክቶ እንደልጃቸው ነው የሚያይዋት። እሷም "ድጋሚ የወለደችኝ እናቴ" ነው የምትላቸው።

አሁን አግብታ ወልዳለች። የራሷ ንግድ አላት። በህይወቷ ደስተኛ ናት።

ራስን ማጥፋት የስነ ልቦና ስቃይን አያጠፋውም። አንድ ሰው ላይ የነበረው ስቃይ በስድስት ሰዎች ውስጥ ልብ ውስጥ እንዲቀጥል ነው የሚያደርገው። በሀገራችን ከ7ሺ ሰዎች በላይ በአመት ራሳቸውን ያጠፋሉ። ይህንን ለመከላከል ሁላችንም አስተዋፅኦ ማድረግ እንችላለን።

ዶ/ር ዮናስ ላቀው

#ውብ_ቀን_ለሁላችንም
@kminspiration