Get Mystery Box with random crypto!

አባ ሕርያቆስ (ዲ. ሕሊና በለለጠ) +++++++++ ጥቅምት ኹለት የአባታችን የአባ ሕርያቆስ ዕረፍ | ✞✞✞ ቅዱሳን ዘ ኢትዮጵያ ✞✞✞

አባ ሕርያቆስ
(ዲ. ሕሊና በለለጠ)
+++++++++
ጥቅምት ኹለት የአባታችን የአባ ሕርያቆስ ዕረፍቱ ነው፡፡ አባ ሕርያቆስ ከጽድቅ ሕይወቱ ባሻገር ለእመቤታችን ባለው ፍቅርና በደረሰው የቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ የሚታወቅ ታላቅ አባት ነው፡፡ በ1994 ዓ.ም. ትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ያሳተመው (አዲስ አበባ) ስንክሳር የጥቅምት ኹለቱ ንባብ “ወበዛቲ ዕለት … ተዝካሮሙ ለሕርያቆስ ወቴክላ ሰማዕት በረከቶሙ ተሀሉ ምስሌነ ለዓለመ ዓለም አሜን” (ትርጉም- በዚህችም ቀን ደግሞ የሕርያቆስና የሰማዕት ቴክላ መታሰቢያቸው ነው በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን፡፡) ከማለት በስተቀር የሚገልፀው ነገር የለም፡፡ ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜን የመሳሰሉት መጻሕፍት ግን ስለ ጻድቁ በጥቂቱ ያትታሉ፡፡

-----የስሙ ትርጓሜ

ሕርያቆስ/ ኅርያቆስ ማለት (የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ) እንደሚገልጠው ኅሩይ/ምርጥ/ ማለት ነው፤ ለሹመት መርጠውታልና ምርጥ ተባለ፡፡
አንድም ረቂቅ ማለት ነው፤ ምሥጢረ ሥላሴን ከኹሉ ይልቅ አምልቶ አስፍቶ ይናገራልና፡፡
አንድም ፀሐይ ማለት ነው፤ አብ ፀሐይ ወልድ ፀሐይ መንፈስ ቅዱስ ፀሐይ እያለ ጽፏልና፡፡
አንድም ብርሃን ማለት ነው፤ የምእመናንን ልቡና በትምህርቱ ብሩህ ያደርጋልና፡፡ ዘአብርሃ መንበረ ማርቆስ በብርሃን እንዲል፡፡
አንድም ንህብ ማለት ነው፤ ንህብ የማይቀስመው አበባ የለም፣ እርሱም የማይጠቅሰው ሊቅ የለምና፡፡

--------ሹመት

ሐዋርያት ስለ ሹመት በሠሩት ቀኖና የተማረና ግብረ ገብ የኾነ እንዲሾም አዝዘዋል፡፡ ኹለቱንም ያስተባበረ ባይኖር ግብረ ገብ የኾነ ነገር ግን ያልተማረ እንዲሾም ሥርዓቱ ያዛል፡፡ ትምህርቱን በጊዜ ሂደት ያመጣዋልና፡፡ በዚኽም መሠረት አባ ሕርያቆስ ያልተማረ ቢኾንም በምግባሩ የተመሠከረለት ግብረ ገብ በመኾኑ ተሾመ፡፡ በዚኽ ሹመትና ሥርዓትን የሚያፀና በመኾኑ ግን በክፋት የሚቀኑበት ብዙዎች ነበሩ፡፡ ያልተማረ በመኾኑም ይንቁታል፡፡ ዕለት ዕለትም አዋርደውት ከሹመቱ ለማስሻር ይጥሩ ነበር፡፡ እርሱ ግን “ወእቀውም ዮም በትሕትና ወበፍቅር” እንዲል እንደጠሉኝ ልጥላቸው እንደናቁኝ ልናቃቸው ሳይል በፍቅርና በትሕትና ጸንቶ ያስተምራቸው ነበር፡፡

--------የዕውቀት መገለጥ/የቅዳሴ ማርያም ድርሰት

አባ ሕርያቆስ ተምኔቱ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም ነው፡፡ የእመቤታችን ምስጋና እንደ ባሕር አሸዋ እንደ ሰማይ ኮከብ በዝቶልኝ፣ እንደ ምግብ ተመግቤው፣ እንደ መጠጥ ጠጥቼው፣ እንደ ልብስ ለብሼው እያለ ይመኝ ነበር፡፡
በእርሱ የሚቀኑበት ተንኮለኞች ከዕለታት በአንዱ ቀን በምን ምክንያት እንሻረው ብለው ተማክረው ቀድሶ ማቁረብ አይችልምና ቀድሰህ አቁርበን ብለን በዚህ ምክንያት እንሻረው ብለው ተስማሙና እንዲቀድስ አደረጉት፡፡
አባ ሕርያቆስም ሥርዓቱን ጨርሶ ከፍሬ ቅዳሴው ሲደርስ ተንኮለኞቹ “ከሊቃውንት ቅዳሴ የሚያስቸግረውን እናውጣለት” እያሉ ሲያወጡ ሲያወርዱ የለመኗትን የማትነሳ የነገሯትን የማትረሳ እመቤት ገልጻለት “ጎሥዓ ልብየ ቃለ ሠናየ” ብሎ “ወይእዜኒ ንሰብሖ” እስኪል ድረስ ሰተት አድርጎ ተናግሮታል፡፡
የሚንቁትና የሚጠሉት ሰዎች “ ይኽ የነገሩትን ቀለም እንኳን አከናውኖ መናገር የማይቻለው ዛሬስ እንግዳ ድርሰት እደርሳለሁ ብሎ ያገኘ ያጣውን ይቀባጥር ጀመረ!” ብለው አደነቁበት፤ የሚወዱትና የሚያከብሩት ግን “ከመንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እንዲኽ ያለ ምሥጢር ከእሩቅ ብእሲ ይገኛልን” ብለው አደነቁለት፡፡ ወዲያውም ጽፈን ደጉሰን ልማድ እንያዘው ብለው ወሰኑ፡፡ ተንኮለኞቹ ግን ይኽንንም ስለተቃወሙ እንደ ሀገራችን ልማድ እንያዘው በሚል ተስማሙ፡፡ በሀገራቸው ልማድ እንግዳ ድርሰት የተደረሰ እንደኾነ ጽፈው ደጉሰው ከእሳት ይጥሉታል፣ ከእሳት ሳይቃጠል የወጣ እንደኾነ ከውሃ ይጥሉታል፣ ከውሃ ሳይርስ የወጣ እንደኾነ ከሕሙም ላይ ይጥሉታል፣ ድውይ የፈወሰ እንደኾነ ደገኛ ድርሰት ነው ብለው ይይዙታል፡፡

ይኽንንም የአባ ሕርያቆስን ድርሰት ጽፈው ደጉሰው ከእሳት ላይ ጣሉት ከእሳት ሳይቃጠል ወጣ፤ ከውሃ ጣሉት ሳይርስ ወጣ፤ ከሕሙም ላይ ጣሉት ድውይ ፈወሰ፣ ይልቁንም ሙት አስነሣ፡፡ ከዚኽ በኋላ ደገኛ ድርሰት ነው ብለው ጽፈው ደጉሰው ያዙት፡፡ በጥራዝም (ከ13ቱ ቅዳሴያት ጋር) 14ኛ አድርገው ጠርዘውታል፡፡

የተቀደሰው ከ33ቱ የእመቤታችን በዓላት በአንዱ ቀን ነው፡፡ የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ አባ ሕርያቆስ ምሥጢር ባይገለጥለት ኖሮ በዕለቱ ቅዳሴ ሐዋርያትን ወይም ቅዳሴ እግዚእን ይቀድስ እንደነበር ይጠቁመናል፡፡ ቅዳሴ እግዚእ “እምድንግል ተወሊዶ ከመ ፈቃደከ ይፈጽም” ብሎ ድንግልን ያነሣታልና፡፡
አባ ሕርያቆስ ተሹሞ ሳለ ብዙ ድርሳን እንደደረሰና ብዙ ተግሳጽ እንደጻፈ የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ ይገልጻል፡፡

---------ከቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊና ከቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያዊ ጋር

ቅዱስ ያሬድ ማይ ኪራህ መደበይ ታብር በሚባል ቦታ ይኖር ነበር፡፡ እመቤታችን ኤፍሬምን ከሶርያ አባ ሕርያቆስን ከብህንሳ በደመና ጠቅሳ ያሬድ ካለበት ቦታ አመጣቻቸውና “አንተ(ኤፍሬም) ውዳሴዬን አንተ(ሕርያቆስ) ቅዳሴዬን ነግራችሁት እርሱ(ያሬድ) በዜማ ያድርስ” ብላቸው፣ እነርሱም ለቅዱስ ያሬድ ነግረውት በዜማ አድርሶታል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ከዚኽ ጋር አያይዞ የቀሩትን 13ቱን ቅዳሴያት ኹሉ በዜማ ደርሷል፡፡

--------እመቤታችን የምትወደው ምስጋና

አንድ ባሕታዊ እመቤታችንን “ከምስጋናሽ ኹሉ ማንን ትወጃለሽ?” ብሎ ቢጠይቃት “ልጄ ዳዊትን፣ አቡነ ዘበሰማያትን ቢደግሙለት እንዲወድ እኔም ውዳሴዬን ቅዳሴዬን ቢደግሙልኝ እወዳለሁ” ብላዋለች፡፡

----------.ብህንሳ የት ናት?

ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ ስለ ብህንሳ የሚከተለውን ብሏል፡-
“ብህንሳ ቅድመ ትሰመይ አርጋድያ ወድኅረ መኑፍ ይላል፡፡ ብዙ ጊዜ ስመ ተፋልሶ አግኝቷታል፡፡ በፊት አርጋድያ ኋላም መኑፍ ተብላለች፤ ዛሬም ብህንሳ ትባላለች፤ ሴትና ወንድ ያልተለየባት ገዳም ናት እንደ ዘጌ እንደ ቆራጣ እንደ ቀንጠፋሜ፤”

ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ የባሕር ማዶ ድርሰት መኾኑን በሚጠቁም መልኩ ቅዱስ ያሬድ ከባሕር ወዲኽ እንዳመጣልንና ከተከዜ ወዲኽ ደግሞ ሳሙኤል ትውልደ ጌዴዎን ዘገበዘ አክሱም እንዳመጣው ይገልጻል፡፡ ስለዚህ ቢንያስ እንደ ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ ኢትዮጵያ ውስጥ አይደለችም።

Kyriakos of bhainsa ስለተባለ ሰው Wikipedia ቢገልጽም ዝርዝር መረጃን አላገኘሁም። Bhainsa የምትባል ከተማ ግን በሕንድ እንምደትገኝ ይገልጻል።

በዚኽ ዙሪያ ጥናት ያደረጋችኹ ወይም ተጨማሪ ያነበባችሁና የተማራችሁ እስኪ ሐሳባችሁን ወዲኽ በሉ፤ ፍላጎቱ፣ አቅሙና ጽናቱ ያላችሁም በጥልቅ መርምሩና ግለጡልን፡፡

የአባታችን የአባ ሕርያቆስ ምልጃ አይለየን፤ እመቤታችን ፍቅሯን በረከቷንና የምስጋናዋን ምሥጢር በልቡናችን ታሳድርልን ዘንድ በረድዔቱ ይባርከን፡፡

ጥቅምት 2፣ 2007 ዓ.ም.