Get Mystery Box with random crypto!

ሰላም ለእናንተ ይሁን እንዴት ናችሁ አሜሪካን ካንሳስ ሲቲ ነዋሪ የሆነችው ሳራ ዳርሊን | ከዚም ከዚያ ጉዞ ወደ መልካምነት!

ሰላም ለእናንተ ይሁን እንዴት ናችሁ

አሜሪካን ካንሳስ ሲቲ ነዋሪ የሆነችው ሳራ ዳርሊንግ ከስራ ወጥታ ወደ መኖሪያዋ በማቅናት ላይ ሳለች አንድ በዕድሜ ጠና ያሉ ሽማግሌ ከመንገድ ዳር ቁጭ ብለው ሲለምኑ ትመለከታለች።

ሳራ ወደ ሽማግሌው በመጠጋት ቦርሳዋን ከፍታ የተወሰኑ ዶላሮችን ሽማግሌው ከጎናቸው ባስቀመጡት የፕላስቲክ ኩባያ ውስጥ አኑራ ጉዞዋን ትቀጥላለች።

ሳራ ከምንግዜውም በላይ በህይወቷ ደስተኛ ነበረች፤ ከምትወደውና ከምታፈቅረው ጓደኛዋ ጋር በትዳር ለመጣመር የቀናት ዕድሜ ቀርቷቸዋል።

ለእሷ ከፍተኛ ክብርና ፍቅር ያለው ፍቅረኛዋ እጅግ ውድ የሆነ ዳይመንድ የቃል ኪዳን ቀለበት ገዝቶ በጉልበቱ ተንበርክኮ የታገቢኛለሽ ጥያቄ ካቀረበላት እና በደስታ እሺ ካለችው ጊዜ አንስቶ ህይወቷ በሀሴት ተሞልቷል።

ምሽት ላይ እንደተለመደው በስስት የምታየውን የዳይመንድ ቀለበት ስማ ለመተኛት ቦርሳዋን ከፈተችው፤ በድንጋጤ ደርቃ ቀረች፤ ቀለበቱ በቦታው አልነበረም።

ቦርሳዋን የከፈተችው መንገድ ዳር ቁጭ ብለው ለሚለምኑት ሽማግሌ ገንዘብ ለመስጠት ብቻ እንደነበር አስታውሳ የሽማግሌው ገንዘብ መሰብሰቢያ ኩባያ ውስጥ ቀለበቱን አብሮ እንደገባባት ጠረጠረች።

ለእጮኛዋ ስልክ በመደወል ሁኔታውን አጫወተችው፤ እጮኛዋም ሲከንፈ መጣ።
ተያይዘው በልመና ወደ ሚተዳደረው ሽማግሌ ቦታ ሄዱ፤ ሽማግሌው ግን በቦታው አልነበሩም።

"በእርግጥ ውድ የሆነ ቀለበት አግኝቶ እንዴት ተመልሶ በቦታው ሊቀመጥ ይችላል" የእጮኛዋ ግምት ነበር።

በቀጣዩ ቀንም በተመሳሳይ ከእጮኛዋ ጋር ሽማግሌው ተቀምጠው ወደ ሚለምኑበት ቦታ ሄዱ፤ አሁንም አልነበሩም። "በቃ ጦስሽን ይውሰድ ከእንግዲህ እርምሽን አውጪ" ነበር የእጮኛዋ መልስ።

በሦስተኛው ቀንም ሳራ ለእጮኛዋ ደውላ ወደ ሽማግሌው ቦታ እንዲሄዱ ጠየቀችው። እጮኛዋ በመገረም "6 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ቀለበት ችግረኛ እና በረንዳ የሚያድር ሰው እጅ ገብቶ አገኘዋለሁ ብለሽ እንዴት ታስቢያለሽ?" ነበር ያላት። ሳራም "በቃ የዛሬን ብቻ እንየው፤ ሰውየው ከሌለ እርሜን አወጣለሁ" አለችው።

እጮኛዋም የሳራን ፍላጎት ለመሙላት ተስማምቶ ጉዞዋቸውን አቀ፤ ሽማግሌው በቦታው ተቀምጦ ሲለምን አገኙት።
ሳራ በደስታ ተዋጠ፤ አላውቅሽም ብሎ እንዳይሸመጥጠኝ የሚል ስጋት እንደዋጣት ወደ ሽማግሌው ተጠጋች።

አባት ያስታውሱኛል? በማለት ጠየቀች። ሽማግሌው ቢል ሬይ ሀሪስ ይባላ፤ ቀና ብሎ ተመልክቷት "አላወቅኩሽም ልጄ" ሲል መለሰላት።

ሳራም "ከ3 ቀን በፊት ከቦርሳዬ ገንዘብ አውጥቼ ሳስቀምጥ ሌላ ዕቃ አብሬ አኑሬ ነበር ?" ስትል ጠየቀቻቸው?

"የጣት ቀለበት ነው?" አሉ ሽማግሌው።

"አዎን አባት!" አለች ሳራ።

ቢል ቀለበቱን ጠቅልሎ ካስቀመጠበት ኪሱ በማውጣት "አንድ ቀን እንደምትመለሺ አውቅ ነበር" በማለት ከሰጣት ብኋላ "ቀለበቱን ያገኘሁት ዕለት ትክክለኛ ወይም አርቴፊሻል ቀለበት መሆኑን ለማወቅ ወደ ጌጣጌጥ ሱቅ ወስጄው ነበር፤ እነሱም ትክክለኛ መሆኑን ነግረው $4,000 ዶላር ሊገዙኝ ጠይቀውኝ ነበር። በእርግጥ ኑሮውን በበረንዳ ለሚያሳልፍና በልመና ለሚተዳደር 4ሺህ ዶላር ከፍተኛ ገንዘብ ነው። ነገር ግን እኔን ለመርዳት ብላ በስህተት ቀለበት የጣለችን ሴት ንብረት መንካት አልፈለግኩም። በመሆኑም በጥንቃቄ አኑሬው የአንቺን መምጣት ስጠባበቅ ነበር።" ሲል መለሰላት።

ሳራ ዳርሊንግ እና እጮኛዋ የመልካሙን ቢል ሬይ ሀሪስ ታሪክ ከታች ቀለበቷን ሲሰጣት ከሚታየው ምስል ጋር በማያያዝ በሶሻል ሚዲያ (Facebook) ለጠፉት፤ ከታሪኩም ጎን ለጎን የእርዳታ ማሰባሰቢያ ጎፈንድሚ አካውንት ከፈቱ። በቢል ሬይ ቀናነት እጅጉን የተደሰቱ አያሌ ግለሶቦች የዕርዳታ እጃቸውን ይዘረጉ ጀመ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ 260,000$ ዶላር ተሰበሰበለት።

በአሁን ሰዓት ቢል ከበረንዳ አዳሪነት ወጥቶ የቤት ባለቤት ነው፤ ተጨማሪ የመጦሪያ ገንዘብም አገኘ።

ወድቆ የተገኘ ሁሉ አይወሰድም። በተለይ በኢትዮጵያን ባህል ነውር ነው። ባለቤቱ ጠፋብኝ ብሎ ሊመጣ ይችላልና ልክ እንደ አደራ እቃ በጥንቃቄ አስቀምጦ ፈላጊው እስኪመጣ መጠበቅ ያስፈልጋል። በትንሹ ስትታመን፤ ፈጣሪ ደሞ በብዙ ይሰጥሀል።

ምንጭ :- ከፌስቡክ

መልካም ቀን፤ ቸር ያሰማን፤ ቸር ያውለን

@Kezimkezia