Get Mystery Box with random crypto!

#ሁለቱ_ልጃገረዶች #ክፍል_አንድ ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ወደዚህች ምድር ከመምጣታ | ጥበበ ሉቅማን/Luqman Tube ️️️

#ሁለቱ_ልጃገረዶች

#ክፍል_አንድ


ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ወደዚህች ምድር ከመምጣታቸው በፊት ሁለት ወዳጅ የሆኑ ልጃገረዶች መካ ውስጥ ይኖሩ ነበር፡፡ እነዚህ እጅግ ቅርብ የሆነ ወዳጅነት የነበራቸው ልጃገረዶች አሚና እና ኸዲጃ ይባላሉ። መካ የተቆረቆረችው ግብፅን፣ ፍልስጤምን፣ ፋርስን፣ ሜሶፖቶሚያን፣ ህንድንና አፍሪካን በሚያገናኙና የአካባቢው አገራት ቁልፍ የንግድ መዳረ በነበሩ መንገዶች ላይ ነበር፡፡ በወቅቱ ከመላው ዓለም የሚመጡ የተለያዩ ሸቀጦች የሚቀርቡበት ዓመታዊ የገበያ ልውውጥም በዚሁ አካባቢ ይካሄድ
ነበር። እዚያው መካ ውስጥ ደግሞ ሰዎች አንድ ፈጣሪን ብቻ ያመልኩበት ዘንድ በኢብራሂምና እስማኢል የተገነባው ጥንታዊው የአላህ(ሱ.ወ) ቤት ካዕባ ይገኝ ነበር፡፡

ካዕባ በዓለም ውስጥ ከሚገኙት እጅግ ጥንታዊ የሆኑ ህንፃዎች ሁሉ ቀዳሚው በመሆኑ የመላው ዐረብ ህዝብ የኩራት ምንጭ ተደርጎም ይወሰድ ነበር፡፡ ያም ሆኖ ግን ዐረቦች የኢብራሂምን ንፁህ የሆነ እምነት በመዘንጋት እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ጣኦታት አንፀው በዚህ ታሪካዊ የካዕባ ህንፃ ውስጥ በማኖር ያመልኩ ነበር፡፡ እናም ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ህዝብ ሸቀጡን ገበያው ላይ በማቅረብ ለመሸጥና ለራሱ የሚፈልገው ካለ ደግሞ ከሌላው ለመሸመት እንደዚሁም በአላህ ቤት ካዕባ በመገኘት የሐጅ ስረዓተ-ጸሎትን ለመከወን በየዓመቱ ወደመካ ይጎርፍ ነበር፡፡ በዚሁ ወቅት የተለያዩ ገጣሚያን የግጥም ድርሰቶቻቸውን በማንበብ እርስ በእርሳቸው የሚወዳደሩበት ትርኢትም የተለመደ ነበር፡፡ መንገደኛ የታሪክ ተራኪዎችም ከየመጡባቸው አካባቢዎች ያጠናቀሯቸውን አዳዲስ ዜናዎች እንዲሁም ከያኒያን ልዩ ልዩ የጥበብ ክህሎቶቻቸውን ከተለያየ የዓለም ክፍል መካ ላይ ለተሰባሰበው ህዝብ ያቀርቡ ነበር፡፡ በወቅቱ እነዚህን ክዋኔዎች በምታስተናግደው መካ ህይወት ደስ የሚል ነበር፡፡

በዘመኑ የአረብ ማህበረሰብ ዝናንና እውቅናን ለመጎናፀፍ ዘወትር
የሚጠመድበትን የውድድር ህይወት ከግብ ለማድረስ እገዛ ያደርጉልኛል በሚል እምነት ለወንድ ልጆች ይሰጠው የነበረው ቦታ የላቀ፤ ለሴት ልጆች ነበረው ክብርም ሆነ ፍላጎት ደግሞ እጅግ የወረደ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ሚስቶቻቸው ሴት ልጅ በሚወልዱ በአብዛኛዎቹ የዐረብ አባቶች ዘንድበከፍተኛ ሐፍረት መሸማቀቅ አሊያም በብስጭት ቤተሰቡን ማወክ በወቅቱ የተለመደ ሁኔታ ነበር። በዚህም ሳያበቁ አባቶች የሚወለዱ ሴት ልጆቻቸውን ከነህይወታቸው በመቅበር ያስወግዷቸው ነበር፡፡ ያም ሆኖ የዚሁ ማህበረሰብ አባል የሆኑት ሁለቱ ባልንጀራ ልጃገረዶች ግን የገጠማቸው የህይወት እድል የተለየ ሆነ፡፡

ባለፀጋ ከሆኑ የተከበሩ ቤተሰቦች የተገኙት አሚና እና ኸዲጃ በወላጆቻቸው ዘንድ በእጅጉ የሚወደዱ ነበሩ፡፡ እናም በማህበረሰቡ ውስጥ የሚፈፀሙትን መልካምም ሆነ ክፉ ተግባራት በዓይናቸው እየተመለከቱ ነበር ያደጉት፡፡

በወቅቱ ጣኦታትን የሚገዛው ሁሉም የመካ ህዝብ አልነበረም፡፡
ጥንታዊ የእምነት መጽሐፍትን የሚያነቡ ፧ ህግጋቱንም አጥብቀው
የሚተገብሩና ከፍልስጤም፣ከየመንና ከየስሪብ የመጡ ሰዎችም መካ ውስጥ ይኖሩ ነበር፡፡ ከዚህም ሌላ ነብዩላህ ዒሣን የሚከተሉ
ክርስቲያኖችም ከመካ ነዋሪዎች መካከል ነበሩ፡፡ የክርስትና እምነት
መጽሐፍትን ጠንቅቆ ያጠናው አላህን፣ ነብያቱን፣ መላኢካዎቹንና
የመጨረሻውን የፍርድ ቀንን በተመለከተ አያሌ እውቀቶችን ያካበተው የኸዲጃ የአጎት ልጅ ወራቃ ቢን ነውፈል በወቅቱ መካ ውስጥ ይኖር ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር ከመካ ህዝብ መካከል የይሁዳ ወይም የክርስትና እምነት ተከታዮች ሳይሆኑ እንደ ኢብራሂም አንድ አምላክን በመፈለግ ዘወትር ለእርሱ ብቻ የሚፀልዩ ሰዎችም ነበሩ፡፡ እነዚህ ሰዎች "ሐነፊዎች" በሚል
ስያሜ ነበር የሚጠሩት፡፡