Get Mystery Box with random crypto!

††† እንኳን ለጻድቁ አቡነ አሌፍ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። ††† | ✞ገድለ ቅዱሳን✞

††† እንኳን ለጻድቁ አቡነ አሌፍ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አባ አሌፍ †††

††† ጻድቁ ገድላቸውን የፈጸሙት በኢትዮዽያ ቢሆንም ሃገረ ሙላዳቸው የጥንቱ የሮም ግዛት የሆነችው ታናሽ እስያ ናት:: አባ አሌፍ ከዘጠኙ (ተስዓቱ) ቅዱሳን አንዱ ናቸው:: ዘጠኙ ቅዱሳን ተወልደው ያደጉት ምንም በአንድ የሮም ግዛት ሥር ቢሆንም መነሻ ቦታቸው ግን የተለያየ ነው::

ሁሉንም አንድ ያደረጋቸው መንፈስ ቅዱስ በኪነ ጥበቡ ነው:: በምክንያት ደረጃ እንግለጸው ከተባለ ደግሞ የአንድነታቸው ምሥጢር:-
1.የቀናች ሃይማኖታቸው ተዋሕዶ::
2.ዓላማ (የእግዚአብሔር መንግስት) እና
3.ገዳማዊ ሕይወት ነው::

አባ አሌፍን ጨምሮ ሁሉም ቅዱሳን ዘራቸው ከቤተ መንግስት ነው:: እነርሱ ግን ምድራዊውን ክብር ንቀው ሰማያዊውን ክብር ገንዘብ ማድረግን መርጠዋል:: አስቀድመው ቅዱሳት መጻሕፍትን ያጠኑት አበው በተለያየ ጊዜ እየመነኑ ከሮም ግዛት ወደ ግብጽ በርሃዎች ወርደዋል::

በምናኔ ቅድሚያውን አባ ዸንጠሌዎንና አቡነ አረጋዊ ይይዛሉ:: ዘመኑ የተዋሕዶ አማኞች የሚሰደዱበት 5ኛው መቶ ክ/ዘመን ነበርና እምነትን ላለመለወጥ ዘጠኙ ቅዱሳን ስደትን መረጡ::

በወቅቱ ደግሞ ለስደት መጠለያ የምትሆንና ከኢትዮዽያ የተሻለች ሃገር አልነበረችም:: ስለዚህም በ470ዎቹ ዓ/ም አልዓሜዳ በኢትዮዽያ ነግሦ ሳለ ቅዱሳኑ በአረጋዊ መሪነት መጡ::

ንጉሡም ሲጀመር የእግዚአብሔር እንግዳ ስለሆኑ: ሲቀጥል ደግሞ ቅድስናቸውን ተመልክቶ መልካም አቀባበልን አደረገላቸው:: ማረፊያ ትሆናቸውም ዘንድ አክሱም ውስጥ አንዲት ቦታን ወስኖ ሰጣቸው:: ይህች ቦታ ቤተ ቀጢን ትባላለች::
አባ አሌፍና 8ቱ ቅዱሳን ወደ ሃገራችን እንደ ገቡ የመጀመሪያ ሥራቸው ቋንቋን መማር ነበር::

ልሳነ ግዕዝን በወጉ ተምረው እዛው አክሱም አካባቢ ሥራቸውን አንድ አሉ:: በወቅቱ በአቡነ ሰላማ: በአብርሃ ወአጽብሐና በአቡነ ሙሴ ቀዳማዊ የተቀጣጠለው ክርስትና በተወሰነ መንገድ ተቀዛቅዞ ነበርና እነ አባ አሌፍ እንደ ገና አቀጣጠሉት::

ሕዝቡን በራሱ ልሳን ለክርስትና ይነቃቃ ዘንድ ሰበኩት:: የካደውን እየመለሱ: የቀዘቀዘውን እያሟሟቁ ለዓመታት ወንጌልን ሰበኩ:: ቀጣዩ ሥራቸው ደግሞ መጻሕፍትን መተርጐም ሆነ::

ከሃገራቸው ያመጧቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት ተከፋፍለው ወደ ግዕዝ ልሳን ተረጐሟቸው:: በዚህም ለሃገራችን ትልቁን ውለታ ዋሉ:: ይህ ሁሉ ሲሆን እነ አባ አሌፍ የሚመገቡትም ሆነ የሚጸልዩት በማሕበር ነበር:: በመካከላቸውም ፍጹም ፍቅር ነበር:: ጸጋ እግዚአብሔር አልተለያቸውም::

††† የነ አባ አሌፍ ቀጣዩ ተግባራቸው ደግሞ ገዳማዊ ሕይወትን ማስፋፋት ሆነ:: ይህንን ለማድረግ ግን የግድ መለያየት አስፈለጋቸው:: እያንዳንዱም መንፈስ ቅዱስ ወደ መራው ቦታ ሔደ::
*ዸንጠሌዎን በጾማዕት::
*ገሪማ በመደራ::
*ሊቃኖስ በቆናጽል::
*አረጋዊ በዳሞ::
*ጽሕማ በጸድያ::
*ሌሎችም በሌላ ቦታ ገዳማትን መሠረቱ::
*አባ ይምዓታ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ምርጫቸው ገርዓልታ (እዛው ትግራይ) ሆነ::

አባ አሌፍ የተወለዱት አውሎግሶንና አትናስያ ከተባሉ ደጋግ ወላጆች ቂሳርያ ውስጥ በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ጻድቁ በሕጻንነታቸው ወደ አባ እንጦንስ ገዳም ገብተው ከዓመታት ተጋድሎ በሁዋላ ከ8ቱ ጉዋደኞቻቸው ጋር ወደ ኢትዮዽያ የመጡ ሲሆን ከተስዓቱ /9ኙ/ ቅዱሳን አንዱ ናቸው::

በዐፄ አልዓሜዳ ዘመን አክሱም አካባቢ (ቤተ ቀጢን) የሃገራችንን ቋንቋ አጥንተው ቅዱሳት መጻሕፍትን ተርጉመዋል:: ለሕዝቡም የወንጌልን የምሥራች ሠብከዋል::

ከዚያም ገዳም መሥርተው: 500 መነካሳትን ሰብስበው ለ70 ዓመታት በቅድስና ኑረዋል:: ለዘጠኙ ቅዱሳን ሁሉ ስም ያወጡት የዘመኑ ሰዎች ቀድመው ወደ አክሱም ስለ ገቡ ጻድቁን "አሌፍ" ብለዋቸዋል:: በዕብራይስጥኛ "አንደኛ" ማለት ነው:: ጻድቁ ከፈጣሪያቸው የምሕረት ቃል ኪዳን ተቀብለው በዚሕች ቀን አርፈዋል::

††† አምላከ አበው ቅዱሳን በምልጃቸው ይማረን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

††† መጋቢት 11 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አባ አሌፍ ጻድቅ (ከተስዓቱ ቅዱሳን)
2.ቅዱስ ቴዎቄጤኖስ ሰማዕት
3.ቅዱስ ባስሊዖስ (ዻዻስና ሰማዕት)
4.አባ ኤፍሬም ሰማዕት
5.አባ ኤልያስ ሰማዕት

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ያሬድ ካህን
2.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት
3.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
4.ብፁዐን ኢያቄም እና ሐና
5.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ

††† "ከእናንተ አንዱ ከባልንጀራው ጋር ሙግት ቢኖረው በቅዱሳን ፊት በመፋረድ ፋንታ በዓመፀኞች ፊት ሊፋረድ ይደፍራልን? ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን? . . . የትዳር ጉዳይ ይቅርና በመላእክት እንኩዋ እንድንፈርድ አታውቁምን?" †††
(1ቆሮ. 6:1-3)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††