=>መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ካረገ ከዓመታት በሁዋላ አይሁድ በአንድ ነገር ተቸገሩ:: የክርስቶስን ሐዋርያት እያሳደዱ ቢገድ ሉም ከመስቀሉና ሥጋ ክርስቶስ አርፎበት ከነበረው ጐልጐታ ላይ የሚደረገውን ተአምር ግን መግታት አልተቻላቸውም:: +መቼም ለተንኮል አያርፉምና ቅዱስ መስቀሉን ሽፍቶቹ ከተሰቀሉባቸው ጋር ደርበው አርቀው ቀበሩት:: አካባቢው የጉድፍ መጣያ እንዲሆንም አዋጅ ነገሩ:: ለክፋት ሲሆን ተባባሪው ብዙ ነውና ለ300 ዓመታት ያህል ቆሻሻ ቢጥሉበት ተራራ ሆነ:: +ከዚህ ሁሉ ነገር በሁዋላ እናታችን ቅድስት እሌኒ (ሔለና) በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት: በቅዱስ ኪራኮስ መሪነት: በቅዱስ ሚካኤል ረዳትነት ደመራ አስደምራ: እጣን አጢሳ መካነ መስቀሉን አገኘች:: +መስከረም 17 ቀን የተጀመረው ቁፋሮ መጋቢት 10 ቀን ተጠናቆ: ንጹሕ መስቀሉ ወጥቶ ብርሃን በርቷል: ሙታን ተነስተዋል:: ከ10 ዓመት በሁዋላም የመስቀሉ ቤተ መቅደስ ታንጾ መስከረም 17 ቀን ተቀድሷል:: +ይህ ቅዱስ ዕፀ መስቀልም በደጉ አፄ ዳዊት ዘመን ወደ ሃገራችን መጥቶ: በጻድቁ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ አማካኝነት በደብረ ከርቤ (ግሸን ማርያም) ተለብጦ ተቀምጧል:: =>አምላከ ቅዱሳን በኃይለ መስቀሉ: በሞገሰ መስቀሉ ይጠብቀን:: ከበረከቱ አሳትፎ በዓሉን የሰላም ያድርግልን:: =>መጋቢት 10 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.ቅዱስ ዕፀ መስቀል 2.ቅድስት ዕሌኒ ንግሥት 3.ቅዱስ ኪራኮስ አረጋዊ 4.ቅዱስ መቃርስ ዘኢየሩሳሌም =>ወርሐዊ በዓላት 1.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ 2.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ 3.ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ጻድቅ ንጉሥ 4.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ 5.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ) =>+"+ የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት: ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና . . . መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ:: የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ:: እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን:: +"+ (1ቆሮ. 1:18-23) † ወስብሐት ለእግዚአብሔር † 96 views03:39