Get Mystery Box with random crypto!

††† እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ማትያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †† | ✞ገድለ ቅዱሳን✞

††† እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ ማትያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ሐዋርያው ቅዱስ ማትያስ †††

††† በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ከእመቤታችን በቀር ከቅዱሳን ሐዋርያት የሚበልጥ አልተነሳም:: "ሐዋርያ" ማለት "ፍንው: ልዑክ: የተላከ: የጽድቅ መንገደኛ" እንደ ማለት ነው:: በምሥጢሩ ግን "ባለሟል" ብለው ሊቃውንቱ ተርጉመውታል::
ይህስ እንደምን ነው ቢሉ:-
¤የፍጥረታት ሁሉ ጌታ: የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም ከድንግል ማርያም ተወልዶ: አድጐ: ተጠምቆ: ጾሞ: ከገዳመ ቆረንቶስ ሲመለስ ቀዳሚ ሥራው ያደረገው ደቀ መዛሙርቱን መጥራት ነበር::

ከተከተሉት የ5 ገበያ ሕዝብ መካከል "ወሐረየ እምሰብአ ዚአሁ አሠርተ ወክልኤተ ሐዋርያተ" እንዲል በመጀመሪያ 12ቱን ሐዋርያት መረጠ::

††† እሊህም:-
1.ዼጥሮስ የተባለ ስምኦን
2.እንድርያስ (ወንድሙ)
3.ያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ
4.ዮሐንስ (ወንድሙ)
5.ፊልዾስ
6.በርተሎሜዎስ
7.ቶማስ
8.ማቴዎስ
9.ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ
10.ታዴዎስ (ልብድዮስ)
11.ናትናኤል (ቀናተኛው ስምዖን) እና
12.ማትያስ (በይሁዳ የተተካ) ናቸው:: (ማቴ. 10:1)

††† እነዚህን 12 አርድእቱን ከጠራ በሁዋላ ለ3 ዓመታት ከ3 ወራት ከዋለበት ሲማሩ ይውሉ ነበር:: ሌሊት ደግሞ ምሥጢር ሲያስተረጉሙ ያድሩ ነበር::

ጌታ እንደሚገባ ካስተማራቸው በሁዋላ ከፍ ያለ ኃላፊነትን ሾማቸው:: ለዓለም እረኞች: የእርሱም ባለሟሎች ሆኑ:: እጅግ ብዙ መከራ እንደሚገጥማቸው ነገራቸው:: (ማቴ. 10:16, ዮሐ. 16:33) በዚያው ልክ ክብራቸውንም አከለላቸው:: (ማቴ. 19:28)

ሥልጣናቸው ደግሞ እስከዚህ ድረስ ሆነ:: "በምድር ያሠራችሁት በሰማይ የታሰረ ይሆናል: በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሆናል::" (ማቴ. 18:18) "ይቅር ያላችሁዋቸው ኃጢአታቸው ይቀርላቸዋል: ያላላቹሃቸው ግን አይቀርላቸውም::" (ዮሐ. 20:23)

የመንግስተ ሰማያትን መክፈቻ (ማቴ. 16:19): እረኝነትን (ዮሐ. 21:15) ተቀበሉ:: ጌታ በንጹሕ አንደበቱ ሐዋርያቱን እጅግ ሲያከብራቸው "ጨው: የዓለም ብርሃናት" (ማቴ. 5:13) አላቸው:: ወንድሞቹም ተባሉ:: (ዮሐ. 7:5) ከዚህም በሚበልጥ በሌላ ክብር አከበራቸው::

ከዚህ ሁሉ ነገር በሁዋላ በጌታ ሕማማት ጊዜ ገና ነበሩና አንዳንዶቹ ፈርተው ተበተኑ:: ተመልሰው ግን በጽርሐ ጽዮን ሲጸልዩ ሰንብተው የጌታን ትንሳኤ ተመለከቱ:: እጆቹን: እግሮቹንም ዳስሰው ሐሴትን አደረጉ::

ለ40 ቀናት መጽሐፈ ኪዳንን: ትምሕርተ ኅቡዓት: ሌላም በፍጡር አንደበት የማይነገር ብዙ ምሥጢራትን ተምረው: ጌታ ሊቀ ዽዽስናን ሹሟቸው ዐረገ::

ለ10 ቀናት በእመ ብርሃን ሥር ተጠልለው ሲጸልዩና በአንድ ልብ ሲተጉ ሰንብተው መንፈስ ቅዱስ ወረደላቸው:: በአንዴም ከፍርሃት ወደ ድፍረት ተመልሰው ፍጹማን: ብርሃናውያን ሆኑ:: 71 ልሳናትን ነስተው በአንዲት ስብከት ብቻ 3ሺ ነፍሳትን ማረኩ:: (ሐዋ. 2:41)

ቅዱሳን ሐዋርያት በኅብረት ለአንድ ዓመት ያህል በኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ እየተመላለሱ አስተምረው ብዙ እሥራኤላውያንን ወደ ክርስትና ማርከዋል:: ከዚህ በሁዋላ ግን እንደ ትውፊቱ ዓለምን በእጣ ለ12 ተካፈሏት::

ይህ ሲሆን መንፈስ ቅዱስ አብሯቸው ነበርና ለእያንዳንዳቸው እንደሚገባቸው አሕጉረ ስብከቶች ደረሷቸው:: እነርሱም ደቀ መዛሙርቶቻቸውን አስከትለው ለታላቁ መንፈሳዊ ዘመቻ ወረዱ::

በሔዱበት ቦታም ከተኩላ: ከአንበሳና ከነምር ጋር ታገሉ:: በጸጋቸውም አራዊትን (ክፉ ሰዎችን) ወደ በግነት መልሰው ለክርስቶስ አስረከቡ:: በየሃገሩ እየሰበኩ ድውያንን ፈወሱ:: ለምጻሞችን አነጹ:: እውራንን አበሩ:: አንካሶችን አረቱ:: ጐባጦችን አቀኑ:: ሙታንንም አስነሱ:: እልፍ አእላፍ አሕዛብንም ወደ መንጋው ቀላቀሉ::

ስለዚህ ፈንታም ብዙዎቹ በእሳት ተቃጠሉ:: ቆዳቸው ተገፈፈ:: በምጣድ ተጠበሱ:: ደማቸው በምድር ላይ ፈሰሰ:: ከአንድ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በቀር ሁሉም ይህችን ዓለም በሰማዕትነት ተሰናበቱ:: ጨው ሆነው አጣፍጠዋልና: ብርሃንም ሆነው አብርተዋልና እናከብራቸዋለን:: "አባቶቻችን: መምሕሮቻችን: ጌቶቻችንና ሊቆቻችን" እንላቸዋለን::

ቅዱስ ማትያስ ስም አጠራሩ ይክበርና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተሰቦቼ ብሎ ከመረጣቸው 120 ቅዱሳን አንዱ: 3 ዓመት ከ3 ወር ከጌታችን እግር ቁጭ ብሎ የተማረ: በይሁዳ ፈንታ ከ12ቱ ሐዋርያት ይቆጠር ዘንድ መንፈስ ቅዱስ የመረጠው ሐዋርያ ነው::

ቅዱሱ ሐዋርያ በዕጣ በደረሰው ሃገረ ስብከቱና በሌሎቹም ዓለማት ለወንጌል አገልግሎት ብዙ ደክሙዋል:: በተለይ የሰውን ሥጋ ወደሚበሉ ሰዎች ሃገር ገብቶ ወንጌልን ቢሰብክላቸው ዓይኖቹን አውጥተው ከብዙ ስቃይ ጋር ለ30 ቀናት ሣር አብልተውታል::

እሱ ግን በትእግስትና በፈጣሪው ኃይል ድንቅ ተአምር አድርጐ አሳምኖ አጥምቋቸዋል:: ከብዙ ተጋድሎና ቅድስና በሁዋላም በዚሕች ቀን በመልካም ሽምግልና አርፏል::

††† አምላከ ቅዱሳን ሐዋርያት ቸርነቱን ያብዛልን:: በምልጃቸው ከክፉ ጠብቆ ከበረከታቸው ይክፈለን::

††† መጋቢት 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)
2.ቅዱስ አርያኖስ ሰማዕት (በዘመነ ሰማዕታት ብዙ ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረና ጌታ በንስሃ የጠራው)
3.ቅዱስ ዮልዮስ ሊቀ ዻዻሳት

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
2.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
3.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
4.አቡነ ኪሮስ
5.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን

††† ". . . እንዲህም ብለው ጸለዩ:: 'አቤቱ ልብን ሁሉ የምታውቅ አንተ ከእነዚህ ከሁለቱ የመረጥከውን አንዱን ግለጥ?' . . . ዕጣ አጣጣሉአቸው ዕጣውም በማትያስ ላይ ወጣ:: ከዐሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋርም ተቆጠረ::" †††
(ሐዋ. 1:24-26)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††