Get Mystery Box with random crypto!

✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞ ❖መጋቢት ፯ (7) | ✞ገድለ ቅዱሳን✞

✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡
አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖መጋቢት ፯ (7) ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

✞ ሰማዕትነት በቅዱስ ቴዎዶጦስ ሕይወት ✞

+*" ቅዱስ ቴዎዶጦስ "*+

=>በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ጊዜው ለክርስቲያኖች
ሁሉ ፍጹም የመከራ ከመሆኑ የተነሳ "ዘመነ-ሰማዕታት"
ሲባል በወቅቱ ከ47 ሚሊዎን በላይ ክርስቲያኖች
ተጨፍጭፈዋል::

+የዘመኑ ክርስቲያኖች ለመሞት የሚያደርጉትን
እሽቅድምድም እያዩ አሕዛብ "ወፈፌዎች" እያሉ
ይጠሯቸው ነበር:: (ዓለም እንዲህ ናትና!) እብዶቹ
ጤነኞችን "እብድ" ማለታቸውኮ ዛሬም አለ::
(ለነገሩ "ግደልና ጽደቅ" ከሚል መመሪያ በላይ ጤና
ማጣት አይኖርም)

=>ታዲያ በወቅቱ አንድ #ቴዎዶጦስ የሚሉት ወጣት
በምድረ ግብጽ ይኖር ነበር:: ወጣቱ እጅግ ብርቱ
ክርስቲያን ነበርና እንደ ዘመኑ ልማድ ተከሦ በነፍሰ
ገዳዮች ፊት ቀረ:: ክሱ አንድ ብቻ ነው:: "ክርስቶስን
አምልከሃል" የሚል::

+ከሥጋ ሞት ለማምለጥ ደግሞ መንገዱ ያው አንድ ብቻ
ነው:: ፈጣሪውን ክርስቶስን ክዶ ለአሕዛብ አማልክት
(አጋንንት) መገዛት:: #ቅዱስ_ቴዎዶጦስ በገዳዮቹ ፊት
ቆሞ ተናገረ:-
" #እኔ_ክርስቲያን_ክርስቶሳ ዊ_የክርስቶስ_ነኝ:: ምንም
ብታደርጉኝ ከክርስቶስ ፍቅር ልትለዩኝ አትችሉም"(ሮሜ.
8:35) አላቸው::

+እነሱ ግን ነገሩ እውነት አልመሰላቸውምና ሊያሰቃዩት
ጀመሩ::
*ገረፉት
*አቃጠሉት
*ደበደቡት
*ሌላም ሌላም ማሰቃያዎችን በእርሱ ላይ ተጠቀሙ::
የሚገርመው ግን እሱ ሁሉን ሲታገሥ ገዳዮቹ ግን
ደከሙ::

+በመጨረሻም ወደ ገዢው ዘንድ አቅርበው "ብዙ
አሰቃይተነዋል:: ግን ሊሳካልን አልቻለም" በሚል ሰይፍ
(ሞት) ተፈረደበት:: በአደባባይ ሊሰይፉት ሲወስዱት ግን
ትንሽ አዘኑለት መሰል ጨርቅ አምጥተው "ፊትህን ሸፍን"
አሉት:: (ያኔ ትንሽም ቢሆን ሰብአዊነት ሳይኖር አይቀርም)

+ቅዱስ ቴዎዶጦስ ግን ገዳዮቹን በመገረም
እየተመለከታቸው ተናገረ:- "እኛ ክርስቲያኖች ሞትን
አንፈራም:: ሞት ለእኛ ወደ ክርስቶስ መሸገጋገሪያ
ድልድያችን ነውና የምንፈራው ሳይሆን የምንናፍቀው
ነው::" "ኢትፍርሕዎሙ
(አትፍሯቸው)"
(ማቴ. 10:28)

+ይህን ብሎ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ጌታውን አመሰገነ::
ፊቱ ላይ ደስታ እየተነበበ ጨካኞቹ አንገቱን ሰየፉት::
በብርሃን አክሊልም ቅዱሳን መላእክት ከለሉት::
*መሠረታዊው ነገር ቅዱስ ቴዎዶጦስ ለምን አልፈራም?
ነው::

+አጭር መልስ ካስፈለገን ቅዱሱ ያልፈራው ከልቡ
ክርስቶሳዊ በመሆኑ ነው:: ትኩረት እንድንሰጠው
የሚያስፈልገው ግን የሰማዕታት ምስጢራቸው:-
1.በጽኑ የክርስትና መሠረት ላይ መመሥረታቸው
2.ዕለት ዕለት የክርስቶስን ፍቅር መለማመዳቸው
3.ከወሬ (ንግግር) ይልቅ ተግባርን መምረጣቸው
4.በንስሃ ሕይወት መመላለሳቸው
5.ሥጋ ወደሙን የሕይወታቸው ዋና አካል ማድረጋቸው
6.ከእነሱ የቀደሙ ቅዱሳንን ዜና ሕይወት ከልብ
ማንበባቸው
7.በቃለ እግዚአብሔር መታነጻቸው . . . መጠቀስ
የሚችሉ መገለጫዎቻቸው ናቸው::

<+>" ዛሬስ "<+>

=>ዓለማችን ከጠበቅነው በላይ ነፍሰ በላነቷ እየጨመረ
ነው:: ዛሬ የክርስትና ጠላቶች ከጉንዳን በዝተዋል::
*የራሳችን ማንነት
*ክርስትናችን በአፋችን ላይ ብቻ መሆኑ
*እረኞችና በጐች መለያየታቸው . . . ሁሉ እኛ ልናርማቸው
የሚገቡ ናቸው::
*አሸባሪዎች
*አሕዛብ
*የመዝናኛው ዓለም
*ሰይጣን አምላኪ ዝነኞች (Celebrities)
*ሚዲያው
*ማሕበራዊ ድረ ገጾችና መሰል ነገሮች ደግሞ
ልንጠነቀቅባቸው የሚገቡና እኛን ውስጥ ለውስጥ
በልተው የፈጁን የሰይጣን መሣሪያዎች ናቸው::

+ስለዚህም ከዛሬ ጀምረን ባለ መታወክ ክርስትናችንን
ከአፋችን ወደ ልባችን: ከብዕራችን ወደ አንጀታችን
እንድናወርደው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አደራ ትላለች::

+ዛሬ ነገሮችን ረስተን ሌሎች አላስፈላጊ ነገሮችን
ከጀመርን እጅግ አሳፋሪ መሆኑ አይቀርም:: በጐውን
ጐዳና ተከትለን በሃይማኖትና በፍቅረ ክርስቶስ ከጸናን ግን
ማንም ቢመጣም ፈጽሞ አንናወጥም::

+ይልቁኑ
"አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን:
ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው::
ስለዚህም ምድር ብትነዋወጥ: ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ
ቢወሰዱ አንፈራም::" (መዝ. 46:1) እያልን ከቅዱስ
ዳዊት ጋር እንዘምራለን::

<< ለዚህ ደግሞ ደመ ሰማዕታት ይርዳን:: በረከታቸው ይድረሰን:: የጌታ ፍቅርም አይለየን >>

+*" ጻድቁ ንጉሥ ቴዎድሮስ "*+

=>በሃገራችን ታሪክ በጣም ተወዳጅ ከነበሩ ነገሥታት
ጻድቁ ቴዎድሮስ ቅድሚያውን ይወስዳል:: በርግጥ
በርካቶቻችን የምናውቀው ስለ ሃገሩ ፍቅር ራሱን የሰዋውን
ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስን (1845-1860) ነው:: በበጎ
ሥራውና በቅድስና ሕይወቱ የተመሠከረለት ግን ዛሬ
የምናስበው ቀዳማዊው ነው::

+ቀዳማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ የደጉ ዐፄ ዳዊት (ግማደ
መስቀሉን ያመጡት) እና የተባረከችው ሚስታቸው ፅዮን
ሞገሳ ልጅና የጻድቁ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ታላቅ ወንድም
ነው:: በኢትዮዽያ ለ3 ዓመታት (ከ1396-1399) ብቻ
ነግሦ እያለ እንደ ንጉሥ ሳይሆን-

*ከጠዋት እስከ ማታ ድሃ እንዳይበደል ፍርድ
እንዳይጉዋደል ይታትር የነበር::
*ጾምና ጸሎትን የሚያዘወትር::
*ወገቡን ታጥቆ ነዳያንን የሚያበላ::
*ለአብያተ ክርስቲያናትም የሚጨነቅ ደግ ሰው ነበር::

+ስለዚህም በሕዝቡ እጅግ ተወዳጅ ነበር:: በነገሠ በ3
ዓመቱ ዐርፎ በዝማሬና በለቅሦ ሥጋውን ተሸክመው
ሲሔዱ ወንዝ ተከፍሎላቸዋል:: ከመቃብሩም ላይ ጸበል
ፈልቁዋል::

=>ዘለዓለም ሥላሴ ደግ መሪና ሰላማዊ ዘመንን ያድሉን::

=>መጋቢት 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ጻድቁ ኢትዮዽያዊ ንጉሥ ዐፄ ቴዎድሮስ
2.ቅዱስ ቴዎዶጦስ ሰማዕት
3.ቅዱስ ፊልሞን ሰማዕት
4.ቅዱስ አብላንዮስ ሰማዕት

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ)
2.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
3.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
4.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
5.አባ ባውላ ገዳማዊ
6.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
7.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)

=>+"+ ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ::
ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና::
ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው::
ስለዚህ ባ ለሥልጣንን የሚቃወም የእግዚአብሔርን
ሥርዓት ይቃወማል:: . . . ለሁሉ እንደሚገባው አስረክቡ::
ግብር ለሚገባው ግብርን: ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን:
መፈራት ለሚገባው መፈራትን: ክብር ለሚገባው ክብርን
ስጡ:: +"+ (ሮሜ. 13:1-8)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>