Get Mystery Box with random crypto!

መጋቢት 4 (ድርሳነ መስቀል) ✞✞✞ እንኩዋን ለታላቁ ነቢይ : ጠቢብና የእሠራኤል ንጉሥ 'ቅዱ | ✞ገድለ ቅዱሳን✞

መጋቢት 4 (ድርሳነ መስቀል)

✞✞✞ እንኩዋን ለታላቁ ነቢይ : ጠቢብና የእሠራኤል ንጉሥ "ቅዱስ ሰሎሞን" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+*" #ቅዱስ_ሰሎሞን ንጉሠ እሥራኤል "*+

=>መፍቀሬ ጥበብ::
¤ጠቢበ ጠቢባን::
¤ንጉሠ እሥራኤል::
¤ነቢየ ጽድቅ::
¤መስተሣልም (ሰላማዊ) . . . እየተባለ የሚጠራው ቅዱስ ሰሎሞን የታላቁ ነቢይና ንጉሥ ልበ አምላክ #ቅዱስ_ዳዊት እና የቅድስት #ቤርሳቤህ (#ቤትስባ) ልጅ ነው:: ከ3ሺ ዓመታት በፊት የተወለደው ቅዱስ ሰሎሞን እስከ 12 ዓመቱ ድረስ በቤተ መንግሥት ከአባቱ ጋር አድጉዋል::

+ቅዱስ ዳዊት 70 ዘመን በሞላው ጊዜ የአካሉን መድከም አይቶ : አዶንያስ በጉልበት እነግሣለሁ ቢልም አልተሳካለትም:: #እግዚአብሔር ሰሎሞንን መርጧልና ገና በ12 ዓመቱ ነገሠ:: ልበ አምላክ አባቱ ዳዊት ነፍሱ ከሥጋው ከመለየቷ በፊት መከረው:: "ልጄ ሆይ! ልብህን ስጠኝ:: ፈጣሪህንም አምልክ" አለው::

+ቅዱስ ሰሎሞን እንደ ነገሠ በገባዖን ለእግዚአብሔር መስዋዕትን አቀረበ:: ጌታም ተገልጾ "ምን ትፈልጋለህ?" አለው:: ሰሎሞንም ልክ እንደ አባቱ ማስተዋልን : ልቡናን ለመነ:: በዚህም ጌታ ደስ ስለተሰኘ "አልቦ እምቅድሜከ : ወአልቦ እምድኅሬከ - ከአንተም በፊት : ከአንተም በሁዋላ እንዳንተ ያለ ጠቢብና ባለጠጋ ሰው የለም : አይኖርም" ብሎት ተሠወረ:: ቅዱስ ሰሎሞን ለ40 ዓመታት በእሥራኤል ላይ ነገሠ::

+ግሩም በሆነ ፍትሑ : በልዩ ጥበቡ ዓለም ተገዛለት:: እግዚአብሔር የመረጣት የእኛዋ #ንግስተ_ሳባ / #አዜብ / #ማክዳም ትፈትነው ዘንድ ሒዳ ምኒልክን (#እብነ_መለክን) ጸነሰች:: በሁዋላም #ታቦተ_ጽዮንና #ሥርዓተ_ኦሪት መጣልን:: ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን #ድንግል_ማርያም ከእነሱ ዘር እንደምትወለድ ነግሮት ነበርና ያበጀሁ መስሎት ሴቶችን አብዝቶ ነበር::

+ነገር ግን:-
¤አንደኛ ሰው (ሥጋ ለባሽ) ነውና::
¤ሁለተኛ ደግሞ ከብዙ ሴቶች መካከል ከአንዷ #እመ_ብርሃን ትገኛለች መስሎት ነበር:: ነገሩ መንገድ ስቶበት ከአሕዛብ (ከፈርዖን ልጅ) ጋር በመወዳጀቱ ለጣዖት አሰገደችው:: እግዚአብሔር እጅግ አዘነ::

+በራዕይ ተገልጦ "ስለ ወዳጄ ስለ #ዳዊት ስል በአንተ ላይ ክፉን አላደርግም" አለው:: ታላቁ ነቢይ ሰሎሞን ይህንን ሲሰማ ወደ ልቡ ተመለሰ:: ማቅ ለብሶ : አመድ ነስንሶ በፍጹም ልቡ አለቀሰ:: ንስሃ ገባ:: መፍቀሬ ንስሃ ጌታችንም ንስሃውን ተቀበለው::

+የይቅርታው መገለጫም ተወዳዳሪ የሌላቸውን 5 መጻሕፍት ገለጠለት:: ተናገራቸው:: ጻፋቸው:: እሊሕም:-

1.መጽሐፈ ጥበብ
2.መጽሐፈ ተግሣጽ
3.መጽሐፈ መክብብ
4.መጽሐፈ ምሳሌ
5.መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ናቸው::

+ቅዱስ ሰሎሞን ልዩ የሆነውን #ቤተ_መቅደስ በመስራቱም ይደነቃል:: ደጉ ንጉሥ : ጠቢብና ነቢይ ሰሎሞን በዚህች ዕለት በ52 ዓመቱ ዐርፎ ወደ ፈጣሪው ሔዷል:: (እንደ ድርሳነ መስቀል ኢትዮጵያዊ ትውፊት)

=>ከመፍቀሬ ጥበብ ቅዱስ ሰሎሞን በረከት ይክፈለን፡፡
=>መጋቢት4 የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት።
1.መፍቀሬ ጥበብ ቅዱስ ሰሎሞን

=>ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጉዋድ (ወንጌላዊው)
2.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
3.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
4.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ (ሰማዕት)

=>+"+ የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ:: ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ : ፀሐይ : ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ . . . አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ : ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ::
ሰባኪው:- "ከንቱ : ከንቱ : ሁሉ ከንቱ ነው" ይላል:: +"+ (መክ. 12:1-9)

   <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>