Get Mystery Box with random crypto!

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ††† ††† እንኩዋን ለታላቁ ሰማዕ | ✞ገድለ ቅዱሳን✞

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን †††

††† እንኩዋን ለታላቁ ሰማዕት "ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ †††

+*" ቅዱስ ቴዎድሮስ ዘሮም "*+

=>ሰማዕትነት በክርስትና ለሃይማኖት የሚከፈል የመጨረሻው ዋጋ (መስዋዕትነት) ነው:: ሰው ለፈጣሪው ሰውነቱን ሊያስገዛ: ሃብት ንብረቱን ሊሰጥ ይችላል:: ከስጦታ በላይ ታላቅ ስጦታ ግን ራስን አሳልፎ መስጠት ነው::

+ራስን መስጠት በትዳርም ሆነ በምናኔ ውስጥ ይቻላል:: የመጨረሻ ደረጃው ግን ሰማዕትነት ነው:: "አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዝ ዓለም: ወተዓገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግስተ ሰማያት" እንዳለው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ሰማዕትነት ማለት መራራውን ሞት ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲሉ መታገስ ነው::

+እርሱ ቅሉ መድኃኒታችን ክርስቶስ የሰማይና የምድር ጌታ ሲሆን ኃፍረተ መስቀልን ታግሦ ሙቶልን የለ! በዓለም ያሉ ብዙ እምነቶች ስለ መግደል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስተምራሉ:: ክርስትና ግን መሞትን እንጂ መግደልን የሚመለከት ሕግ የለውም::

+እርሱ ባለቤቱ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ: የሚረግሟችሁን መርቁ: ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ" ብሎናልና:: (ማቴ. 5:44) ነገር ግን ዕለት ዕለት ራሳችንን በሃይማኖትና በምግባር ካልኮተኮትነው ክርስትና በአንድ ጀምበር ፍጹም የሚኮንበት እምነት አይደለምና በፈተና መውደቅ ይመጣል::

+በተለይ የዘመኑ ክርስቲያን ወጣቶች ልናስተውል ይገባናል:: የቀደሙ ወጣት ሰማዕታት ዜና የሚነገረን እንድንጸና ነውና::

=>ቅዱስ ቴዎድሮስ በዘመነ ሰማዕታት (በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን) በቀድሞው የሮም ግዛት ውስጥ ከተነሱ ታላላቅ ሰማዕታት አንዱ ነው:: በወቅቱ መሪ የነበረው ክሀዲው መክስምያኖስ "ክርስቶስን ክደህ ለጣኦት ስገድና በከተማዋ ላይ እሾምሃለሁ" ቢለው "ለእኔ ሃብቴም ሹመቴም የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው" በማለቱ ንጉሡ ተቆጥቶ በብረት ዘንግ አስደበደበው::

+በመንኮራኩር አበራየው:: ለአናብስት ጣለው:: አካላቱን ቆራረጠው:: በእሳትም አቃጠለው:: ቅዱስ ቴዎድሮስ ስቃዮችን ስለ ቀናች ሃይማኖት ሲል በትዕግስት ተቀበለ:: በፍፃሜውም አንገቱን በሰይፍ ተመትቶ 3 አክሊላት ወርደውለታል::

+ከፈጣሪው ዘንድም ነጭ መንፈሳዊ ፈረስና ቃል ኪዳን ተቀብሏል:: ስሙን የጠራ: መታሠቢያውን ያደረገ ዋጋው አይጠፋበትም:: (ማቴ. 10:41)

=>አምላከ ቅዱሳን ከቅዱሱ ሰማዕት በረከት ይክፈለን:: አይተወን:: አይጣለን:: ጾሞ ለማበርከትም ያብቃን::

=>የካቲት 28 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት)
2."6,304" ሰማዕታት (በቅ/ቴዎድሮስ አምላክ አምነው ሰማዕትነት የተቀበሉ)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.አማኑኤል ቸር አምላካችን
2.ቅዱሳን አበው (አብርሃም: ይስሐቅና ያዕቆብ)
3.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
4.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ

=>+"+ እግዚአብሔር ለኛ የሰማዕትነትን ሥራ ይሰጠን ዘንድ ቅዱሳን ስለሚሆኑ ሰማዕታት እንማልዳለን:: +"+
(ሥርዓተ ቅዳሴ ቁ. 73)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>