Get Mystery Box with random crypto!

†††እንኳን ለታላቁ ሊቅና ጻድቅ ቅዱስ አንስጣስዮስ እና አቡነ ዓምደ ሥላሴ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል | ✞ገድለ ቅዱሳን✞

†††እንኳን ለታላቁ ሊቅና ጻድቅ ቅዱስ አንስጣስዮስ እና አቡነ ዓምደ ሥላሴ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ አንስጣስዮስ ሊቅ †††

††† ቅዱስ አንስጣስዮስ በ4ኛው ክ/ዘመን የተነሳ ሶርያዊ የነገረ መለኮት ሊቅ: ገዳማዊ ጻድቅና የመንበረ አንጾኪያ ሊቀ ዻዻሳት ነበር:: ቅዱሱ ርጉም አርዮስን ካወገዙ 318ቱ ቅዱሳን ሊቃውንት አንዱ ነው:: በወቅቱ ታላላቅ ሊቃነ ዻዻሳት ሱባኤውንና ጉባኤውን የመሩ ሲሆን አንዱ ይህ ቅዱስ ነው::

ከ 5 ዓመታት በሁዋላም ብዙ ድርሳናትን ጽፎ: ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ፈጽሞ በ330 ዓ/ም አርፏል:: ያረፈው ግን አርዮሳውያን ባቀረቡት ክስ በሃሰት ተመስክሮበት በግፍ ተሰዶ ነው:: ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ስለ ውለታው የውዳሴ ድርሳን ጽፎለታል::

††† አቡነ ዓምደ ሥላሴ †††

††† እኒህ ታላቅ ጻድቅ ሐዋርያዊ አባት አቡነ ዓምደ ሥላሴ የትውልድ ሃገራቸው ጎጃም ሲሆን የተወለዱት በዚሁ ዕለት (የካቲት 27) ነው:: ጻድቁ በአጼ ሱስንዮስ (በ17ኛው መቶ ክ/ዘ) የነበሩ ድንቅ ሠሪ : ተአምረኛና ገዳማዊ አባት ናቸው::

የካቲት 16 ቀን መንኩሰው ወደ ተጋድሎ ገብተዋል:: በዋልድባ በነበራቸው ቆይታም እመቤቴ ኪዳነ ምሕረት የካቲት 16 ቀን እንድትከበር ማድረጋቸውም ይነገራል:: ጻድቁ በሌሎች ገዳማትም የነበሩ ሲሆን ዛሬም ድረስ ረድኤታቸው የሚደረግበት : ስማቸው የሚጠራበት ገዳም ግን ማኅበረ ሥላሴ ይባላል::

ገዳሙ የሚገኘው በሃገራችን ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ : በመተማ በርሃ ውስጥ ነው:: ይህንን ቅዱስ ገዳም የመሠረቱትም ራሳቸው አባ ዓምደ ሥላሴ ናቸው:: ገዳሙ ዛሬም ብዙ ምሑራንና መናንያን ያሉበት : በደህና ሁኔታም የሚገኝ ነው:: ግን በርሃውን የኔ ብጤ ደካማ ሰው የሚችለው አይደለም::

ስለ ጻድቁ ዓምደ ሥላሴ ከሚነገሩ ታሪኮች ቅድሚያውን የሚይዘው የተዋሕዶ ጠበቃነታቸው ነው:: በ1603 ዓ/ም ዼጥሮስ (ፔድሮ) ፓኤዝ የሚባል ካቶሊካዊ እሾህ ወደ ሃገራችን ገብቶ ነበርና ንጉሡን ሱስንዮስን አባብሎ ተዋሕዶን አስካዳቸው:: ነገሩ ውስጥ ለውስጥ ሲበስል ቆይቶ በ1609 ዓ/ም በመገለጡ እነ ራስ ዮልዮስ ለሃይማኖታቸው ጠዳ ላይ ተዋግተው ግንቦት 6 ቀን ተሰው::

ይህ ነገር ሲሰማ ወንድ ሴት : ትልቅ ትንሽ ሳይመረጥ በገጠሩም : በከተማውም : በገዳሙም ያሉት ሁሉ የተዋሕዶ ልጆች መንቀሳቀስ ጀመሩ:: 7 ዓመታት እንዲህ አልፈው በ1616 ዓ/ም ግጭቱ በይፋ ተጀመረ::

"ተዋሕዶን ካልካዳችሁ" በሚል በቀን እስከ 8,000 ሰው በሰይፍ ታረደ:: ይህን ያደረጉት ደግሞ አልፎንሱ ሜንዴዝ : ንጉሡ ሱስንዮስና ጀሌዎቻቸው ነበሩ::

በጊዜውም ከቤተ መንግሥት እነ ንግሥት ወልድ ሰዓላ (የሱስንዮስ ሚስት) : ከጻድቃን አበው ዘርዓ ቡሩክ ዘግሺ : ሐራ ድንግል ዘደራ : ምዕመነ ድንግል ዘጩጊ : ዓምደ ሥላሴ ዘማኅበረ ሥላሴ . . . ከቅዱሳት እነ ፍቅርተ ክርስቶስ : ወለተ ዼጥሮስ : ወለተ ዻውሎስ : እኅተ ዼጥሮስ . . . ለሃይማኖታቸው ተዋሕዶ ጥብቅና ቆመው ሕዝቡን አስተማሩ:: መከራም ተቀበሉ::

ብዙ ኢትዮዽያውያን የመከራ ጽዋን ተጐንጭተው ለክብር ከበቁ በሁዋላ የእግዚአብሔር ፍርድ ተገለጠ:: በጻድቃኑ እነ አባ ዓምደ ሥላሴ ሐዘን ንጉሡ ታመመ:: ምላሱ ተጐልጉሎ ወጣ::

በዚህ ጊዜ አቤቶ ፋሲለደስ ለአባ ዓምደ ሥላሴና ለሌሎቹ ቅዱሳን "አባቴን አድኑልኝ! ተዋሕዶም ትመለስ" አላቸው:: ጻድቁም ከባልንጀሮቻቸው ጋር ጸልየው ንጉሡን አዳኑት:: በፈንታውም ይህንን አሳወጁ::

††† ፋሲል ይንገሥ!
ሃይማኖት (ተዋሕዶ) ይመለስ!
የሮም ሃይማኖት ይፍለስ! †††

ከዚህ በሁዋላ በ1624 ዓ/ም ፋሲል ሲነግሥ አባ ዓምደ ሥላሴ ለገዳማቸው ብዙ ቦታ አስከልለው : በተጋድሎ ኑረው በዚህች ቀን ዐርፈዋል::

††† አምላከ ቅዱሳን በቀናችው እምነት ተዋሕዶ ሁላችንም እስከ ፍጻሜ ዘመናችን ያጽናን:: ከበረከተ ቅዱሳንም ይክፈለን::

††† የካቲት 27 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አባ አንስጣስዮስ ርቱዓ ሃይማኖት (ዘአንጾኪያ)
2.አቡነ ዓምደ ሥላሴ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.የጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በዓለ ስቅለት
2.አቡነ መብዐ ፅዮን ጻድቅ
3.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)
4.ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
5.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
6.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
7.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት

††† "የተጠራችሁለት ለዚህ ነው:: ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏልና:: እርሱም ኃጢአት አላደረገም:: ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም:: ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም:: መከራንም ሲቀበል አልዛተም . . . እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ::" †††
(1ዼጥ. 2:21-25)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††