Get Mystery Box with random crypto!

††† እንኳን ለጻድቁ አባታችን ቅዱስ አቡፋና እና ቅዱስ እንጦኒ ሐዲስ ሰማዕት ዓመታዊ የዕረፍት በ | ✞ገድለ ቅዱሳን✞

††† እንኳን ለጻድቁ አባታችን ቅዱስ አቡፋና እና ቅዱስ እንጦኒ ሐዲስ ሰማዕት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አባ አቡፋና †††

††† ታላቁ አባ አቡፋና፦
በምድረ ግብጽ ተጋድሏቸውን የፈፀሙ፣
በመዐልት አምስት መቶ ጊዜ በሌሊትም አምስት ጊዜ አቡነ ዘበሰማያትን ይጸልዩ የነበሩ፣
በአርባ ቀን አንድ ጊዜ ብቻ እህል ይቀምሱ የነበሩና ሙሉ ዘመናቸውን በበርሃ በታላቅ ጽሙና የፈፀሙ አባት ናቸው።

ጻድቁ በጣም የሚታወቁት ከማበጡ የተነሳ እጅግ ግዙፍ በነበረ እግራቸው ነው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ስለ መድኃኔ ዓለም ፍቅር አልቀመጥም፤ አልተኛም ብለው ለአሥራ ስምንት ዓመታት በመቆማቸው ነው።

አሥራ ስምንት ዓመት የመቆማቸው ዜናስ እንደምን ነው ቢሉ፦
አንድ ቀን "እኔ ግን ከዚህ ዓለም የምለየው መቼ ይሆን?" ሲሉ አሰቡ። በእርግጥ ይህንን ሐሳብ ብዙ ሰዎች ሊያስቡት ይችላል። ሐሳቡ ጠቃሚም ያልተፈቀደም ነው።
፩. "ጠቃሚ ነው።" ያልኩት አንድ ሰው ሞት እንዳለ ካወቀ ወይም 'መቼ ነው የምሞተው' ብሎ ካሰበ ንስሐ ይገባል፤ ክፋትን ይተዋል ተብሎ ስለሚታመን ነው። ወገኔ ሁሉ እንደ አውሬ ሲባላ፣ ደም ሲያፈስ፣ ክፋትን ሲጐነጉን የሚውል "እሞት ባይ" ሳይሆን "እኖር ባይ" ሆኖ ነውና።
ግን ሞት በቅርቡ እንዳለ በኃያሉ አምላክ ፊት ራቁቱን ለፍርድ እንደሚቀርብ ለወገኔ ማን በነገረው!
፪. "ያልተፈቀደ ነው።" ያልኩት ደግሞ በሁለት ምክንያት ነው።
"ኢትበሉ ለጌሰም (ለነገ አትበሉ።)" የሚል አምላካዊ ቃል ስላለ።
ማቴ. ፮፥፴፬
ሰው (በተለይ ዓለማዊው) የሚሞትበትን ቀን ቢያውቅ አጭር ጊዜ ከሆነ ሽብር ጭንቀት ይበላዋል። ወዲህ ደግሞ ጊዜው ረዥም ቢሆን እንደ ሰብአ ትካት (ማለትም በኖኅ ዘመን እንደ ነበሩ ሰዎች) 'ብዙውን ልዝናናበት (ኃጢአት ልሥራበት')ና ንስሐ እገባለሁ።' ይላልና ነው።

በዚያውም ላይ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ቅዱስ ሰውና የነቢያት አለቃ ቅዱስ ሙሴ የሞቱን ጊዜ ጠይቆ እጅግ መቸገሩን መጥቀሱ በራሱ በቂ ነው። ጌታ "ዓርብ ቀን ትሞታለህ።" ብሎት ለሁለት ዓመታት ዓርብ ዓርብ ሲገነዝ ሲፈታ ኑሯል።

በመጨረሻም ዓርብ ቀን ድንገት መልአከ ሞት መጥቶበታል። ስለዚህ "ወድልዋኒክሙ ንበሩ - ተዘጋጅታችሁ ኑሩ። መባላችንን አስበን ልንኖር ግድ ይለናል።
ማቴ. ፳፬፥፵፬

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ አቡፋና ይህንን የዕረፍታቸውን ነገር ሲያስቡ ቅዱስ መልአክ ተገልጦ "ተርፈከ አሠርቱ ወሰመንቱ - አሥራ ስምንት ቀርቶሃል።" አላቸው። እርሳቸውም "ጌታዬ አሥራ ስምንት ምን?" ሲሉ ቢጠይቁትም ሳይመልስላቸው ተሠወረ።

ከደቂቃ እስከ ኢዮቤልዩ ብዙ አሥራ ስምንቶች አሉ። እርሳቸው ግን "አሥራ ስምንት ቀን ነው!" ብለው ለጌታ ተሳሉ። ስዕለታቸውም "ከዚህ በኋላ አልቀመጥም።" የሚል ነው። እየጾሙ እየጸለዩ ለአሥራ ስምንት ቀናት ቆሙ። ሞት አልመጣም።

"አሥራ ስምንት ሱባኤ ይሆን!" ብለው አሥራ ስምንት ሱባኤ (መቶ ሃያ ስድስት ቀናት) ቆመው ጸለዩ። አሁንም ሞት አልመጣም። "አይ! አሥራ ስምንት ወር ሊሆን ይችላል።" ብለው ለአሥራ ስምንት ወራት (ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር) ቆመው ተጉ። አሁንም ግን ሞት የውኃ ሽታ ሆኖ ቀረ።

ይህን ጊዜ ግን ወደ ፈጣሪ ለመኑ። "ጌታዬ! ያልከኝ ምን አሥራ ስምንት ነው?"
ቅዱስ መልአኩም መጥቶ "አቡፋና ሆይ! የቀረህ አሥራ ስምንት ዓመት ነውና ጽና።" ብሏቸው ተሰወረ። ልብ በሉልኝ "እስክሞት አልቀመጥም።" ብለው ተስለዋል።

ቅዱሱ ገዳማዊ በቃላቸው የሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያን ነበሩና ለአሥራ ስምንት ዓመታት እንደተተከለ ምሰሶ ቆመው ጸለዩ፣ ጾሙ። እንዲህ ያሉትን ቅዱሳን ሊቃውንት፦
"ሰላም ለከ ጽኑዕ ከመ ዓምድ
ዘኢያንቀለቅሎ ሞገድ።"
(ማዕበለ ዓለም የማያናውጸው ብርቱ ምሰሶ ሆይ! ምስጋና ይገባሃል።) የሚሏቸው።

ስለ ቅዱሱ የተጻፈ አርኬም፦
"ሰላም ለቁመተ አቡፋና ዘአልቦ ኑታጌ
እስከ ተመሰለ እግሩ ከመ እግረ ነጌ።" ይላል። ከመቆም ብዛት አካላቸው ደቆ እግራቸው የዝሆን እግር እስኪመስል ወፍሮ ነበርና።

††† አባ አቡፋና በዘመናቸው ብዙ ተአምራትን ሠርተው በዚህች ቀን አርፈዋል።

††† ቅዱስ እንጦኒ ሐዲስ ሰማዕት †††

††† ቅዱስ እንጦኒ (Anthony) በትውልዱ ከሶርያ ዐረቦች ሲሆን በቀደመ ሕይወቱ ክርስቲያኖችን ያሳድድ፣ ካህናትን ይደበድብ፣ አብያተ ክርስቲያናትንም ያቃጥል ነበር። እግዚአብሔር በንስሐ ሲጠራው ግን ደግ፣ ጻድቅና ምርጥ ዕቃ ሆኖ ተገኘ። በመጨረሻም ከብዙ መከራ በኋላ ለሰማዕትነት በቅቷል።

††† አምላከ ቅዱሳን የወዳጆቹን ትጋት፣ ጽናት፣ ፍቅርና በረከት ያድለን። ከማስተዋልም አያጉድለን።

††† የካቲት ፳፭ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ
፪.ቅዱስ እንጦኒ ሐዲስ ሰማዕት
፫.ቅዱሳን ሰማዕታት አውሳንዮስ፣ ፊልሞናና ሉቅያ ድንግል (የቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ ደቀ መዛሙርት)
፬.ቅዱስ ቶና ዲያቆንና ሰማዕት
፭.ቅዱስ ሚናስ ዘሃገረ ቁስ

††† ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
፪.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
፫.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
፬.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
፭.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)

††† "ኃይል የሰጠኝን ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታችንን አመሰግናለሁ። አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም ምንም ብሆን ይህን አደረገልኝ። ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረትን አገኘሁ።" †††
(፩ጢሞ ፩፥፲፪-፲፫)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††